Thursday, June 20, 2013

የግንቦት7 ሊቀመንበር ዶ.ር ብርሀኑ ነጋ ፣ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ እና ሌሎችም ምሥክርነት ሰጡ


ሰኔ ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- የአፍሪካ ጉዳዮች ሃላፊ ዶናልድ ያማማቶ፣ በአፍሪካ የዩሴ አይ ዲ ዳይሬክተር ኤሪል ጋስት፣ በአፍሪካ  ጉዳዮች ተመራማሪ  ዶ/ር ፒተር ፓሀም፣ የግንቦት7 ሊቀመንበር ዶ.ር ብርሀኑ ነጋ ፣ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዳይሬክተር  አቶ ኦባንግ ሜቶና የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአሜሪካ ተወካይ  ሚስተር አዶቲ አኪዌ እና ሌሎችም ታዋቂ ምሁራን ፖለቲከኞች የተሳተፉበት ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ አምባሳደር ያማማቶ እና ዶ/ር ጋስት ኢትዮጵያ በመስቀለኛ መንገድ ላይ እንድምትገኝ ገልጸዋል።
የኢህአዴግ መንግስት የኢኮኖሚ እድገት ማምጣቱን የገለጹት አምባሳደር ያማማቶና ሚስተር ጋስ፣  በሌላ በኩል ግን መንግስት ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብቶች ረገጣ በመፈጸሙ የአገሪቱን መጻኢ እድል አደጋ ላይ ጥሎታል ብለዋል።
ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ፣ አቶ ኦባንግ ሜቶ እና ሚ/ር አክዌ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን፣ ዶ/ር ብርሀኑ ከአቶ መለስ ሞት በሁዋላ ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ በመለስ ጊዜ እንደነበረው ምናልባትም ከዚያ በበሳ ሁኔታ አስከፊ እየሆነ መሄዱን ገልጸዋል። የኢህአዴግ ባለስልጣናት ከፍተኛ ገንዘብ የዘረፉ እና ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የፈጸሙ በመሆናቸው እንጠየቃለን በሚል ፍርሀት ስልጣን በቀላሉ ለመልቀቅ እንደማይፈልጉ ዶ/ር ብርሀኑ አክለዋል።
ዶ/ር ብርሀኑ መንግስትን በሀይል ለማውረድ የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች እየተጠናከሩ መሄዳቸውን፣ አገሪቱ ወደ አልተፈለገ ግጭት ከማምራቷ በፊት የአሜሪካ መንግስት አሁን የሚከተለውን ፖሊስ ቆም ብሎ እንዲፈትሽ አሳስበዋል።
አቶ ኦባንግ ሜቶ በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን አሜሪካ ነጻ ታወጣናለች ብለው እንደማይጠብቁ፣ የራሳቸውን መብት በራሳቸው ለማስከበር እንደሚችሉ ገልጸው፣ አሜሪካ ከአምባገነኑና ዘረኛው የህወሀት መንግስት ጋር የምታደርገውን ግንኙነት እንደገና እንድትፈትሽ ጠይቀዋል።
የውይይቱ ሊቀመንበር የተከበሩ ሚስተር ክሪስ ስሚዝ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በዝርዝር ለተሰብሳቢው አቅርበዋል።

Ethiopia’s opposition vows sustained national protests against the ruling party


June 20, 2013

by Associated Press

ADDIS ABABA, Ethiopia — Ethiopia’s main opposition party says it will launch what it said will be a sustained national campaign against the country’s ruling party.The Unity for Democracy and Justice Party
The announcement Thursday follows a peaceful demonstration on June 2. It was the first public protest since 2005 when security forces killed hundreds of protesters in postelection violence.
The Unity for Democracy and Justice Party said the country is heading toward “absolute dictatorship” under the ruling party, which has been in control since 1991.
The party said it would hold rallies to pressure the government to remove the anti-terrorism law. It will also call for the respect of human and democratic rights and will demand the release of jailed dissidents, journalists and political leaders.
The protests are the first show of disapproval against Prime Minister Hailemariam Desalegn.
Copyright 2013 The Associated Press. All rights reserved. This material may not be published, broadcast, rewritten or redistributed.

ቀን የጎደለብን ስደተኞች ቀን!!



Boat_loaded_with_Ethiopian_and_Somali_immigrants_in_the_Gulf_of_Aden_yemen
ዛሬ የስደተኞች ቀን መሆኑን ወዳጄ ሰሚር ፌስ ቡክ ላይ ባጋራን ማስታወሻ እና የአልጀዚራ ድረ ገፅ ማስፈንጠሪያ አስታወስኩ፡፡ አንዳንዱ ቀን “እንኳን አደረሳችሁ” ተባብሎ ቢቻል ጠላ ተጠምቆ ድፎ ዳቦ ተደፍቶ እና ዶሮ ወጥ ተወጥውጦ ያከብሩታል፡፡ አንዳንዱ ቀን ደግሞ በሀዘን “ምን ይሻላል ምን ይበጃል” የሚለውን እያንጎራጎሩ ያከብሩታል፡፡ ታድያ “ቀን የጎደለብን ስደተኞች ቀን” በተለይ ለእኛ ኢትዮጵያያን የሀዘን ቀናችን አይደለምን!?
የአልጀዚራ ድረ ገፅ፤ በግብጽ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን የተጋረጠባቸውን ስጋት ያስነብባል፡፡ ግብፃዊያን ሆዬ፤ “ከአባይ ትነኩ እና ደማችሁን ነው የምንጠጣው” አይነት ዛቻ ኢትዮጵያውያን ላይ እየዛቱባቸው እንደሆነ አልጀዚራ ነገረኝ፡፡
ግብፃዊያኑ የሚያደርጉትን ሲያሳጣቸው እንጂ እነዚህ ዜጎች ላይ የፈለጉትን ያህል መጥፎ ነገር ቢያደርሱ የኢትዮጵያ መንግስት ምንም ግድ አይሰጠውም፡፡ መንግስታችን እንደ ሰካራም አባት ነው፡፡ ውጪ ስንደበደብ እንዴት ተመትተህ ትመጣለህ… ብሎ መልሶ ይደበድበናል እንጂ ልጆቼን ለምን ነካችሁ ብሎ ጥያቄ እንኳ አይጠይቅም፡፡
አሁን በቅርቡ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትራችን ዶክተር ቴውድሮስ አድሃኖም ከግብፅ ውጪ ጉዳይ  ሚኒስትር ጋር መሃመድ ከሪም ጋር አባይን አስመልክቶ ውይይት መጀመራቸውን ሰምተናል፡፡ ዶክተርየው በውይይታቸው፤ የዜጎቻችንን ነገር አደራ ሲሉ አልሰማንም፡፡ ምናልባት ብዙ ጥቃት ብዙ ጉዳት ከደረሰ በኋላ ወደፊት ዶክመንተሪ ሰርተው ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር ሆነው ያለቅሱልን ይሆናል፡፡
የሆነ ሆኖ ዛሬ ቀን የጎደለብን የኛ የስደተኞች ቀን ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ምክንያቶች በየቀኑ እንሰደዳለን፤ በተለይ መንግግስታችን “ውጡልኝ ከዚህ ቤት” እያለን እና ኑሮ ሮሮ እየሆነብን ቁጭ ብሎ ከመታመም እየሄዱ መሞት ይሻላል ብለን በባህር በየብሱ የምንሰደድ ብዙ ነን!
ድሮ ድሮ አረቦች ወደ እኛ ሀገር ይሰደዱ ነበር፡፡ ተሰደውም ሚጢጢ ሱቅ ከፍተው አላፊ አግዳሚውን ጋሼ እያሉ፤ እነርሱም “ጋሼ ባለሱቁ” ተብለው፤ ኑሯቸውን ይገፉ ነበር፡፡ አሁንም ጭምር በየሰፈሩ “አረቦ ሱቅ” የሚባሉ ቤቶች የዚህ ታሪክ ዱካ ናቸው፡፡ ዛሬ እነዛው አረቦች ወይም ልጆቻቸው በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ተገጣጥሞ ቢሰፋ ከሀገር የሚሰፋ መሬት ለግላቸው ተሰጥቷቸው እያረሱ እየበሉ ነው፡፡
የእኛ እህቶች ደግሞ በአሁኑ ወቅት፤ በአረብ ሀገራት ለስራ ብለው ተሰደው በሚደርስባቸው ሴራ፤ የስነ ልቦና እና የአካል ጉዳት አንዳንዴም እስከ ሞት የሚያደርስ ጥቃት እያጋጠማቸው ለሀገራቸው መሬት እንኳ ሳይበቁ በየሜዳው እየቀሩ በሰው ሀገር ጭካኔ እየተበሉ ነው፡፡ የአረብ ሀገር ባለሀብቶችን የሚንከባከበው መንግስታችን በአረብ ሀገራት የሚጉላሉ ዜጎቹን ጉዳይ ዶክመንተሪ ፊልም ከመስራት ያለፈ “አባከና” ሲላቸው አላየንም፡፡
በኬኒያ፣ በታንዛኒያ፣ በየመን፣ በሶማሌ፣ በሱዳን በሁሉም አቅጣጫ ኢትዮጵያውያን እየተሰደዱ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ በሀገር ውስጥም አልደላቸውም በስደቱም አልተመቻቸውም፡፡
“እንደው የእኔን ነገር ዝም ነው ዝም ነው
ውጪም አልተመቸኝ ቤቴም ንዝንዝ ነው”
እንዳለችው ሴትዮ በሀገር ውስጥም በውጪም አበሳችንን እያየን ነው፡፡ ይህንን አበሳችንን ቀለል የሚያደርግልን ማን ይሆን!? አናውቅም! ዝም ብለን ግን ተስፋ እናደርጋለን…
አንድ ቀን ሁሉም ጥሩ ይሆናል፡፡
አንድ ቀን ሀገራችን ለሁላችንም የምትበቃ ትሆናለች!
እስከዛው ድረስ ግን፤ ቀኑ እስኪሞላ የስደኞችን ቀን እኛ ስናከብረው “ቀን የጎደለብን…” የሚለውን ከፊት ለፊቱ ጨምረን “ቀን የጎደለብን ስደተኞች ቀን” ብለን ነው ማለት ነው !






Tuesday, June 18, 2013

የአባይ ጉዳይ የዛፍ ላይ እንቅልፍ የሆነባት ግብጽ እና ለስልጣን ጸብ ጫሪው ህውሃት!


June 18, 2013

የአባይ ጉዳይ ለግብጽ የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው። ዛፍ ላይ ሆነህ እንቅልፍ ይወስድሃል? ሸለብ እንኳን ያደርግሻል ዛፍ ላይ ሆነሽ? እነደዚያ ነው የአባይ ጉዳይ ለግብጽ። ይኽ እንቅልፍ ማጣት እና ስጋት ዛሬ የጀመረ አይደለም። ባጭሩ ልተርክ። ሪቻርድ ፓንክረስት በግብጽ የተገኙ መረጃዎችን መሰረት በማድረግ ክርስቶስ ከመወለዱ ከ3 ሺ አመቶች በፊት ጀመሮ የግብጽ ነጋዴዎች በእግራቸው የአባይን ወንዝ ዳርቻ ተከትለው እንዲሁም በቀይ ባህር በነፋስ በሚገፉ ጀልባዎች ዛሬ ኢትዮጵያ (ያኔ የፐንት ግዛት) በሚባለው ግዛት ውስጥ ከሚኖረው ህዝብ ጋር የንግድ ልውውጥ ማድረጋቸውን እና ግዛቱን ምድረ ታ-ኔትጄሩ (Land Ta-Netjeru) ማለትም “ምድረ አማልዕክት” እንደሚሉት እና “የመጀመሪያ አገራችን ነው” ይሉም እንደነበር የኢትዮጵያውያን ድንበር-መሬቶች (The Ethiopian Borderlands) በሚለው መጽሐፉ ዘርዘር አድርጎ ጽፏል። የቅርቡን ብንመለከት ደግሞ በተለይ ከ1813 ዓ. ም. ጀመሮ ግብጽ የኢትዮጵያ ባለቤትነቷን በጦርነት ለማረጋገጥ የዮሐንስን ኢትዮጵያ ከሱዳን ቀላቅላ ለመግዛት በአራት አቅጣጫዎች ወረራዎች ከፍታ ሳይሳካለት ወደ መጣችበት መመለሷን ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ “ዐፄ ዮሐንስ እና የኢትዮጵያ አንድነት በሚለው መጽሐፉ በሰፊው ተርኳል። በኃይለስላሴ እና በደርግ ዘመንም ለኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች የጦር መሳሪያ እና ስልጠና በማቀነባበር፣ ገንዘብ በመለገስ፣ በመካከለኛው ምስራቅ አረብ አገሮችን በማስተባበር፣ የአማርኛ ስርጭት ሬዲዮ በመክፈት ድጋፍ ማድረጓን እናውቃለን። ህውሃት ከተጠቃሚዎቹ ተቃዋሚዎች ውስጥ አንዱ ነው። በአባይ ጉዳይ ከጥንት ጀምሮ ግብጽ ከስጋት ነፃ የሆነ እንቅልፍ የለታም። ዛሬም ሆነ ወደፊት ግብጽ የሰላሙን መንገድ ትታ የጸበኛነቱን መንገድ ከመረጠች እንቅልፍ አይኖራትም። ይኽን የግብጽ ጭነቀት እና ስጋት ህውሃት ጠንቅቆ ያውቃል። ስለዚህ ግንቦት 20 ቀን ጸብ ጫረ። ላብራራ።
የጥናቱን ውጤት ተቀበለችውም አልተቀበለችው ስለ አባይ ጉዳይ በጥናት ላይ የተሰማራው ኤክስፐርቶች ቡድን ሪፖርት እየጠበቀች ሳለች ድንገት ግንቦት 20 ቀን 2005 ዓ. ም. ህውሃት የአባይ ወንዝ የፍሰት አቅጣጫ መቀየሩን ሰበር ዜና ተሰራጨ። የኢትዮጵያ ሽብርተኛው ኢ.ት.ቭ. አስተጋባ። ዜናው ግብጽ ደረሰ። ከጥንት ጀምሮ የአባይ ጉዳይ የዛፍ ላይ እንቅልፍ የሆነባት ግብጽ ተደናገጠች። አምባገነኑ ሞርሲ ከገበባት የውስጥ ችግር ለማምለጥ የህውሃትን ቁስቆሳ ተጠቀመ። አካራሪ የግብጽ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ጋበዞ ‘እኔ ሳልሞት ግብጽ አትጠማም’ አለ። ያጀቡት አክራሪዎችም ‘ግፋ’፣ ‘በርታ’፣ ‘አይዞህ ከጎንህ ነን’ አሉት። ይኽ ምክክራቸው ዜና ሆኖ አደባባይ ወጣ። ህውሃት ሁካታውን ያልጫረ መስሎ ለኢትዮጵያ ህዝብ ግብጽ ልትወጋህ ነው የሚል ፕሮፖጋንዳ ጀመረ። የቀድሞ አባቶቻችን ድሎች ሳይቀሩ እየተጠቀሱ የቀረርቶ ድምጽ በአዲስ አበባ እየጎላ መጣ። አልባራዳይን የመሰሉት የግብጽ ዴሞክራሲ ኃይሎች የግብጽን መንግስት ወቀሱ። የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ኃይሎችም ቀረርቶው ገደብ ይበጅለት አሉ። የኢትዮ-ግብጽ የጦርነት ሁካታ አነሳሱ ይኽን ይመስል ነበር። ህውሃት የማያስፈልግ ጸብ ጭሯል።
ለመሆኑ ለምን የአባይ ወንዝ አቅጣጫ ግንቦት 20 ቀን ተቀየረ? ዜናውስ ለምን ግንቦት 20 ቀን አደባባይ ወጣ? ለዚኽ ጥያቄ አቶ በረከት ስሞዖን ሰኔ 7 ቀን ግድም 2005 የሰጠውን መግለጫ እንመልከት፥ የአባይ ወንዝ አቅጣጫ ግንቦት 20 ቀን የተቀየረው በአጋጣሚ እንጂ ህውሃት ሰልጣን ከጨበጠበት ቀን ጋር እንዲገጣጠም ሆን ተብሎ የተደረገ እንዳልሆነ ሊያስተባብል ሞክሯል። ይኽ የበረከት ስሞዖን ማስተባበያ በሽብርተኛው ኢ.ቲ.ቭ. እና በኢሳት ተዘግቧል። የአቶ በረከትን መቀላመድ ወደ ጎን አድርገን እውነቱን ሃቁን እንመልከት። የአባይ ወንዝ ፍሳሽ አቅጣጫ ግንቦት 20 ቀን እንዲቀየር ያስደረገው ህውሃት ነው። ዜናው ግብጽ እንዲደርስ ያደረገውም ህውሃት ነው። ግቡም ስልጣን ነው። ላብራራ! (1ኛ) የተለየ አሳቢ እና ከድኽነት ነፃ አውጪህ እኔ ህውሃት ነኝ የሚል መልዕክት ለኢትዮጵያ ህዝብ ለማስተላለፍ እንዲችል ሆን ብሎ የአባይ ፍሳሽ የተቀየረበትን ቀን ስልጣን ከጨበጠበት ግንቦት 20 ቀን ጋር አገጣጠመው። የዚኽ እርምጃ ፖለቲካዊ ግብ ህዝቡ እንዲያመልክበት እና ስልጣኑ እንዲጠናከር ነው። ግድብ መገንባት አይደለም ግቡ። በተጨማሪ (2ኛ) የአባይ ጉዳይ የዛፍ ላይ እንቅልፍ ለሆነባት ግብጽ የአባይ ፍሳሽ አቅጣጫ መቀየር ዜና የጦርነት ፖለቲካ ውስጥ እንደሚያስገባት ጠንቅቆ ስለሚያውቅ በምላሹ የኢትዮጵያን ህዝብ በአገር ወዳድነት ስሜት አሳውሮ በሚፈልገው የፖለቲካ አቅጣጫ ለማስጓዝ አስልቶ ነበር። የዚኽም ፖለቲካ ስሌት ግቡ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ ኃይሎች ለመምታት እና ስልጣኑን ለማጠናከር ነበር። በአገር ከሃዲነት እና በሽብርተኛነት ሽፋን። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ኃይሎች ፈጥነው ስላጋለጡት የኢትዮጵያን ህዝብ በአባይ ስሜት አሳውሮ የዴሞክራሲ ኃይሉን ለመምታት የሚያስችለው ጊዜ ሳያገኝ ቀረ። ከሸፈበት።
ህውሃት ከግድቡ ይልቅ ስልጣኑ እንደሚበልጥበት ለአንዲት ደቂቃ እንኳን መዘንጋት አያስፈልግም። ወደፊትም ሌሎች ጸቦች ሊጭር እና ከዚያ ግብጽ ልትወጋን ነው ይልሃል። የዴሞክራሲ ኃይሎች የነፃነት ሰላማዊ ትግላቸውን አጠናክረው በመቀጠል እራሳቸውን ከህውሃት ማጭበርበር እና ጥቃት መጠበቅ አለባቸው።
ግርማ ሞገስ (girmamoges1@gmail.com)
ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2005 ዓ.ም. (Tuesday, June 18, 2013)

Monday, June 17, 2013

የቢሮ ኃላፊው በሙስና ላይ ምስክር ሳይሆኑ ተገደሉ


June 17, 2013


ብዙ ሳይታወቅ የተገደሉ ተስፋዬዎች አሉ”
በነበራቸው የስራ ሃላፊነት በድብቅ መረጃ ሲያሰባስቡ ቆይተው ለመንግስት ካጋለጡ በኋላ ራሳቸውን ደብቀው የነበሩት አቶ ተስፋዬ ኢሬሣ ምሳ እየተመገቡ ህይወታቸው ማለፉ ተሰማ። አቶ ተስፋዬ ሰኞ ለጸረ ሙስና ኮሚሽን የምስክርነት ቃላቸውን ለመስጠት ከኮሚሽነር አሊ ሱሌማን ጋር ቀጠሮ ይዘው ነበር።
Allegations of Corruption Emerge Against Federal Government Examiners
Former Gambella Regional President, Mr. Omot Obang Olom
በቅርቡ ወደ ፌደራል መንግስት የተዛወሩት የጋምቤላ የቀድሞ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ኡሞት ኦባንግ፣ ከ83 ሚሊዮን ብር በላይ አላግባብ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን፣ እንዲሁም በክልሉ የሚፈጸሙትን የተጭበረበሩ የበጀት አፈጻጸሞችንና ምዝበራዎችን የሚያጋልጡ ሰነዶችን በሚስጥር በማደራጀት ለኢህአዴግ ያቀረቡት አቶ ተስፋዬ አሟሟታቸው አነጋጋሪ ሆኗል።
አቶ ተስፋዬ ኢሬሳ ከፍተኛ ምስጢር ያላቸውን ሰነዶች በመያዝ ከመታሰራቸው በፊት መሰወራቸውን፤ “የቢሮ ሃላፊው ይዘው የተሰወሩት መረጃ አቶ ኦሞት የፈረሙባቸው ከፍተኛ የገንዘብ ሰነዶችና ሙስና የተከናወነባቸው የኮንስትራክሽንና የተለያዩ መረጃዎች ናቸው። መረጃዎቹ አንድ ቀን ህዝብ ፍርዱን ይሰጥ ዘንድ ይፋ ይሆናሉ” በሚል ጎልጉል ምንጮቹን ጠቅሶ በ (ጥቅምት 19፤2005/October 29, 2012) መዘገቡ ይታወሳል
ቀደም ሲል የጋምቤላ የፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ከላይ የተጠቀሰውን የሙስና ወንጀል በማጋለጣቸው ጋምቤላ መኖር ሳይችሉ ቀርተው ራሳቸውን ሸሽገው ለመኖር ተገደው እንደነበር የሚያውቋቸው ለጎልጉል አስረድተዋል።
“አቶ ተስፋዬ ሙስናን በማጋለጣቸው በፍርሃቻ ራሳቸውን ደብቀው ሊኖሩ አይገባም” በማለት ኢህአዴግ ከለላ እንደሚሰጣቸው ቃል በገባላቸው መሰረት ከተሸሸጉበት የወጡት አቶ ተስፋዬ ሰንጋተራ ትንሳዔ ሆቴል ከጋምቤላ ልጆች ጋር መገናኘት ይጀምራሉ።

ባለፈው ሳምንት ከፌዴራል የጸረ ሙስና ኮሚሽነር አሊ ሱሌማን ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ ከያዙ በኋላ ኮሚሽነሩ በድንገት ለለቅሶ ወደ ጎንደር በመሄዳቸው ቀጠሮው ለሳምንት ይራዘማል። ለሰኞ (ሰኔ10፤2005) አዲስ ቀጠሮ ይይዛሉ።
በስልክ ያነጋገርናቸው ትንሳዔ ሆቴል አካባቢ እንደነበሩና ለጉዳዩ ቅርበት እንዳላቸው የሚገልጹ የጋምቤላ ተወላጅ የስራ ሃላፊ እንዳሉት አቶ ኦሞት ኦባንግ ለአቶ ተስፋዬ ስልክ ደውለው ነበር። አቶ ተስፋዬ ህይወታቸው ከማለፉ ሁለት ቀን በፊት የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ኦሞት በስልክ ተማጽንዖ አቅርበው ነበር።
አቶ ኦሞት “እውነት ነው ጸረ ሙስና ኮሚሽን ቀጠሮ የያዝከው?” በማለት ይጠይቃሉ
“አዎ! እውነት ነው” በማለት አቶ ተስፋዬ መልስ ይሰጣሉ።
አቶ ኦሞት መልሰው “እንግዲያውስ ጸረ ሙስና ኮሚሽን ከመግባትህና ከማነጋገርህ በፊት ሁለታችን መገናኘት አለብን። የምንነጋገረው ነገር አለ” የሚል ጥያቄ ያቀርባሉ። አቶ ተስፋዬ ስለ ስልክ ልውውጡ እንደነገሯቸው የተናገሩት እኚሁ ሰው፣ አቶ ኦሞት በስልክ ደጋግመው በመደወል ያቀረቡትን የ”እንነጋገር” ጥያቄ አቶ ተስፋዬ አልቀበልም ይላሉ።
ጋምቤላ ስራቸውን ለቀው ራሳቸውን ደብቀው የኖሩት በእርሳቸው ምክንያት መሆኑን፣ ፍትህ እንደሚፈልጉ፣ አሁን ለመነጋገር ጊዜው እንዳልሆነ፣ ዘርዝረው ለአቶ ኦሞት መናገራቸውን ያወሱት የጎልጉል ምንጭ፣ ጥያቄያቸው ውድቅ የተደረገባቸው አቶ ኦሞት በንዴት ተዛልፈው ነበር።
ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው እንግዲህ አቶ ተስፋዬ ትንሳዔ ሆቴል ሰዎችን በመላላክና በመታዘዝ ከሚኖር አንድ የጋምቤላ ሰው /አቶ ተስፋዬ የሚረዱት በምግባር ጉዳይ የሚታማና ጸበኛ የሚባል ሰው ነው/ አብረው ተቀምጠው ምሳ እየበሉ ሳለ አቶ ተስፋዬ አረፋ ይደፍቃቸዋል። ወዲያው ከተቀመጡበት ተንሸራተው መሬት ይወድቃሉ። ቀጥሎም ሰውነታቸው ይዝልና ኮማ ውስጥ ይገባሉ። ከአፋቸው እየተዝለገለገ የሚወጣው ፈሳሽ በመጨመሩና የተለያየ ርዳታ ቢደረግላቸውም ሊተርፉ ስላልቻሉ ሆስፒታል ተወስደው ህይወታቸው ማለፉ ተረጋግጧል።
አቶ ተስፋዬ ሆስፒታል ከመድረሳቸው በፊት እንደሞቱ የሚናገሩት የጎልጉል ምንጭ አሟሟታቸው ከመርዝ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተናግረዋል። አቶ ተስፋዬ በሙስና ወንጀል ላይ ያሰባሱትን መረጃ ለተለያዩ አካላት የበተኑ ስለሆነ እሳቸውን በመግደል ማድበስበስ እንደማይቻል አስታውቀዋል። አቶ ተስፋዬ ሙስና ካጋለጡ በኋላ መሰወራቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው። በተያያዘ በጋምቤላ ኢንቨስትመንት ላይ ከተሰማሩ ባለሃብቶች ውስጥ ከ70በመቶ በላይ የሆኑት የህወሓት የቀድሞ ታጋዮች የነበሩና የክልል አንድ ተወላጆች መሆናቸው የአቶ ተስፋዬን አሟሟት ይበልጥ ውስብስብ እንዳደረገው አስተያየት እየተሰጠ ነው፡፡
የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ “የአቶ ተስፋዬ ሞት አሳዛኝና አስደንጋጭ ነው። ብዙ ሳይታወቅ የተገደሉ ተስፋዬዎች አሉ” በማለት ስለ አቶ ተስፋዬ ሞትና አሟሟት መረጃ እንደደረሳቸው አስታውቀዋል።
“አቶ ተስፋዬ ለእውነት ሲል ሞቷል። ኢህአዴግ ውስጥ በርካታ የወንጀል መረጃ ያላቸው ወገኖች አሉ። እንዲህ ያሉ ዜጎች በየትኛውም ዘመን አይረሱም። የቀን ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ስማቸውና ታሪካቸው ከጨዋነታቸው ጋር ተመልሶ ህያው ይሆናል። ሌቦችና ነፍሰገዳዮች ወደ ህግ ሲያመሩ፣ እንደ አቶ ተስፋዬ አይነቶቹ የመጪው ትውልድ ታላቅ ምሳሌ ሆነው እየተወደሱ ህያው ሆነው ይኖራሉ” የሚል አስተያየት የሰጡት አቶ ኦባንግ፤ አቶ ተስፋዬ ያሰባሰቧቸው የሙስናና ተመሳሳይ ወንጀሎች ማሳያ ሰነዶች እጃቸው ላይ ስላለ አቶ ተስፋዬን በመግደልና በማስገደል ወንጀል ማድበስበስ እንደማይቻል ተናግረዋል።
የአቶ ተስፋዬ የቀብር ስነስርዓት ጋምቤላ መፈጸሙን ለመረዳት ተችሏል። ቤተሰቦቻቸውን በማግኘት ሆስፒታሉ ስለ አሟሟታቸው የሰጠውን አስተያየት ጠይቀን ለመረዳት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካልንም።

Friday, June 14, 2013

Over 400 names of traders, officials, whose accounts were frozen, made public ESAT News June 14, 2013


The Ethiopian Federal High Court on a letter written on May 21, 2013, number 134048, has ordered that the bank accounts, monies and cars of 429 government officials, businesspeople  and their family members be frozen and impounded.


The 429 people include suspects of corruption who are currently imprisoned and their family members. One of the frozen accounts is of investor Nega Gebregziabher and his families, Ephrem Nega Gebregziabher, Henok Nega Gebregziabher, Yetbarek Nega Gebregziabher, Selam Nega Gebregziabher, and Rahel Nega Gebregziabher. The bank accounts of Markneh Alemayehu, Chief Prosecutor of the Ethiopian Revenue and Customs Authority (ERCA), and his family members such as Yonatan Markneh Alemayehu, Elshadaye Markneh Alemayehu, Balgeti Alemayehu Wedano, Bafne Alemayehu Wedabo, Ayele Alemayehu Wedabo, Berhanu Alemayehu Wedabo, Abera Alemayehu Wedabo and Tigrest Alemayehu Wedabo, have also been frozen.

Similarly, the bank account of Siye Abraha, the incumbent’s former military chief and now an opposition, and the accounts of his brothers and sisters; Heluf Abraha Hagos, Asmelash Abraha Hagos, Asefa Abraha Hagos, Woldeselasie Abraha Hagos and Temnit Abraha Hagos, have all been frozen.

The list of the names of the 429 people, whose accounts have been frozen, can be viewed here http://goo.gl/ObypL

Monday, June 10, 2013

የአባይ ኢትዮ-ግብጽ ጦርነት ወይንስ የነፃነት ትግላችን!



ግርማ ሞገስ (girmamoges1@gmail.com)
ሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2005 ዓ.ም. (Monday, June 10, 2013)
አምባገነኖች ስልጣናቸውን ለማጠባበቅ አጋጣሚውን ሁሉ ይጠቀማሉ። ሰሞኑን የአባይን ግድብ አስታከው አምባገነኖቹ ህውሃት/ኢህአዴግ እና የግብጽ መንግስት መምታት የጀመሩት የጦርነት ከበሮም ከዚህ የተለየ አይደለም። የህዝባቸውን ብሄራዊ ክብር ስሜት ተቆጣጥረው የዲሞክራሲ ኃይሎችን ለማዳከም እና ስልጣናቸውን ለመጠጋገን የሚያደርጉት ድራማ ነው። ኢትዮ-ግብጽ ጦርነት አይቀሬ አይደለም። የግብጽ ዴሞክራሲ ኃይሎች ወደ ጦርነት አይሄዱም። የኢትዮጵያ ሰላማዊ ትግል ወታደር አይኑን ከነፃነት ትግሉ መንቀል የለበትም።
የአባይ ወንዝ የሚጓዝበትን ሽምጥ ሸለቋማ ክፍል የአዲሱ ግድብ አካል ቢደረግ ግድቡ ሰፊ ቦታ እንዳይዝ፣ ውሃው ለጸሐይ ብዙ ተጋልጦ እንዳይተን እና መጠኑ እንዳይቀንስ ይረዳል። የግድብ ግንባታ ወጪም ይቀንሳል። ይኽን ተፈጻሚ ለማድረግ ደግሞ የአባይን ወንዝ ለጊዜው አቅጣጫውን ማስቀየር ያስፈልጋል። ይኽ የግድብ ግንባታ ምህንድስና ሀ ሁ ነው። በዚህ እርምጃም የመጀመሪያዋ ተጠቃሚ ግብጽ እንጂ ኢትዮጵያ አይደለችም። ይኼን ሃቅ የግብጽ መሃንዲሶች ያውቁታል። አክራሪው የሞርሲ መንግስት ሳይቀር በልቦናው ያውቀዋል። ግብጽ የምትጠቀመው ከኢትዮጵያ ጋር ከመወዳጀት እንጂ ጸበኛ በመሆን እንዳልሆነ አለም ያውቀዋል። በቅርብ አልባራዳይ በአደባባይ ወጥቶ የግብጽ መንግስት ኢትዮጵያን ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል ያለውም ለዚኽ ነው። ኢትዮ-ግብጽ ጦርነት የለም። የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሰራዊት ከነፃነት ትግሉ መዘናጋት የለበትም።
የውሃው መጠንም አይቀንስም። ላብራራ። ከውሃ ኃይል (Energy) የኤሊክትሪክ ኃይል (Energy) ማመንጨት ቴክኖሎጂ ጥንታዊ በመሆኑ በሰፊው የሚታወቅ ጉዳይ ነው። ከአባይ ወንዝ ውሃ ኃይል (Energy) 5ሺ አራት መቶ ሜጋዋት ኤሊክትሪክ ኃይል (Energy) ማመንጨትም ውስብስብነት የለውም። ግብጽም ከአስዋን ግድብ የምታመነጨው 2 ሺ አንድ መቶ ሜጋዋትም የሚጠቀመው ዘዴ ተመሳሳይ ነው። በግድብ ሲሰበሰብ በውስጡ የታመቀ የውሃ ኃይል (Energy) ይገነባል። ውሃው ከግድቡ ሲለቀቅ ደግሞ አምቆት በነበረው ኃይል መዘውሮችን እየመታ የኤሌክትሪክ ኃይል ይሰጣል። መዘውሮችን የመታው ውሃ የት ሄደ? ወደ ሱዳን ከዚያ ወደ ግብጽ። የውሃው መጠን አይቀንስም። ይኼን ቴክኖሎጂ የግብጽ መሃንዲሶች እና ሳይንስትስቶች ያውቁታል። ይኽን ሃቅ የሙባረክን መንግስት በሰላማዊ ትግል ከስልጣን ካስወገዱ በኋላ በገፍ ኢትዮጵያን የጎበኙት የግብጽ ዴሞክራሲ ኃይሎችም ያውቁታል። ይኼን ቴክኖሎጂ የተባበሩት መንግስታት ያውቀዋል። የአፍሪካ ህብረት ያውቀዋል። የሞርሲ መንግስት እና የግብጽ አክራሪዎች ሁካታ መፍትሄው ዲፕሎማሲ ነው። ኢትዮ-ግብጽ ጦርነት የለም። የኢትዮጵያ ሰላማዊ ትግል ሰራዊት በህውሃት ጦርነት ድራማ መዘናጋት የለበትም። ለነፃነት የሚያደርገውን ትግል በጽናት አጠናክሮ መቀጠል አለበት።

ስለየትኛው ‘ውል’ ነው የምታወራው? ትምህርት የቀመሰው የኢትዮጵያ የዛሬ እና የነገ ትውልድ እንደማይቀበለው የግብጽ ፕሬዘዳንት ሳይቀር ልቦናው ያውቀዋል። የ‘ውሉ’ ሰነድ ይተጻፈው በኢንግሊዝ ሲሆን ግቡ የግብጽን እና የሱዳን ህዝብ እንዳይጠማ ማድረግ ሳይሆን በዚያን ዘመን በኢንግሊዝ አገር ተስፋፍቶ የነበረው የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ በጥጥ እጥረት እንዳይጠማ ማድረግ ነበር። እንግሊዝ በቅኝ ገዢነት በምታስተዳድራቸው ግብጽ እና ሱዳን ሰፊ የጥጥ እርሻ ነበራት። ቅኝ አገዛዝ ለዘላለም የሚኖር መስሏት የጥጥ እርሻዋ እንዳይጠማ የጻፈችው ሰነድ ነበር። የዛሬው አለም መሪ ነኝ ባይዋ አሜሪካም ብትሆን የውሉን መናኛነት ታውቀዋለች። ሁለቱ በአፍሪካ ቁልፍ ሸሪኮቿ በአባይ ወንዝ የተነሳ ጦርነት እንዲሄዱ እና በአፍሪካ ቀንድ ሽብርተኛነት እንዲያገረሽ አትሻም አሜሪካ። ኢትዮ-ግብጽ ጦርነት የለም። የኢትዮጵያ ነፃነት ሰራዊት በህውሃት የጦርነት ከበሮ መታለል የለበትም።
የህውሃት/ኢህአዴግ መንግስት የህዝብ ድጋፍ እና ክብር ማግኘት ከፈለገ የጦርነት ከበሮ ከመምታት ፈንታ እሁድ ግንቦት 25 ቀን 2005 ዓመተ ምህረት ሰማያዊ ፓርቲ በጠራው ሰላማዊ ሰልፍ የተገኘው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ኃይል ለጠየቃቸው ጥያቄዎች አዎንታዊ መልስ መስጠት አለበት። ዐርብ ዐርብ ሳያሰልሱ ከአንድ አመት በላይ መብታቸው እንዲከበር ለሚጠይቁት ሙስሊም ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን አዎንታዊ መልስ መስጠት አለበት። በማን አልብኝነት የዘጋቸውን ፍኖተ ነፃነት፣ ፍትህ እና ሌሎች ጋዜጦች እንዲታተሙ ማድረግ አለበት። ከሬድዋን እና ሽመልስ ከማል ከመሳሰሉ ተራ አድርባዮች እራሱን ማጽዳት አለበት። ነፃ ምክር ነው!

የኢትዮ-ግብጽ ጦርነት አይቀሬ ነው ቢባል እንኳን የመለስ ዜናዊ ራዕይ ጠባቂው ህውሃት/ኢህአዴግ እምነት ተጥሎበት ጦርነቱን ብቻውን እንዲመራ መፈቀድ የለብንም። አድነት ፓርቲ፣ ሰማያዊ ፓርቲ፣ መኢአድ፣ የቀሩት የመድረክ አባል ድርጅቶች እና የቀድሞ ታዋቂ አገር ወዳድ የጦር መኮንኖች ከመንግስት ጋር በእኩልነት በጣምራ የሚመሩት የኢትዮ-ግብጽ ጦርነት ኮምሽን ማቋቋም የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ህውሃት ተዓማኒ አይደለም።