Thursday, August 7, 2014

በአራዳ ምድብ ችሎት ሐብታሙ አያሌው ዳንኤል ሺበሺና የሺዋስ አሰፋ


Augest7/2014
አራዳ ፍርድ ቤት ዛሬ እንዲህ ሆነ

ዛሬ ከቀኑ 8፡00 በአራዳ ምድብ ችሎት ሐብታሙ አያሌው ዳንኤል ሺበሺና የሺዋስ አሰፋ እንደሚቀርቡ በመነገሩ ብዛት ያላቸው ሰዎች ቀደም ብለው በፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ ተገኝተው ነበር፡፡ፖሊስ በፍርድ ቤቱ የተሰጠውን የቀጠሮ ሰዓት አክብሮ እስረኞቹን ማቅረብ በመቻሉ ላይ ብዙዎች ስጋት የነበራቸው ቢሆንም አልተሳሳቱም፡፡
መደበኛው የስራ ሰዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ከፍተኛ ታጣቂ ሃይል የፍርድ ቤቱን ቅጥረ ግቢ ተቆጣጠረው ከደቂቃዎች በኋላም አንድ ማንነቱን ቀደም ብለን ለማወቅ ያልቻልነው ቀጠን ያለ ወጣት እጆቹን ታስሮ ወደ ችሎት ገባ፡፡በኋላ ላይ ማረጋገጥ እንደቻልኩት ወጣቱ ዘላለም የሚባል ሲሆን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማስተርስ መርሀ ግብር ተማሪ ነበር፡፡ፖሊስ በተመሳሳይ መልኩ እነ ሐብታሙን በያዘበት ዕለት በቁጥጥር ስር መዋሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በመለጠቅም ዳንኤል ሺበሺ ሁለት እጆቹ በካቴና ታስረው ነጠላ ጫማ ፣ጥቁር ሱሪና ቱታ ጃኬት ተላብሶ ወደ ውስጥ ዘለቀ፡፡
ከጺሙ ማደግ በስተቀር ዳንኤል ፊትና አካል ላይ ምንም አይነት ለውጥ አይታይም፡፡ስሙን እየጠሩና በእጆቻቸው እያጨበጨቡ አድናቆታቸውን ለሚገልጹለት ሰዎች ጥርሱን ብልጭ እያደረገ አጸፌታውን ከመመለስ ውጪ ምንም አልተናገረም፡፡
የዳንኤልን ችሎት ለመከታተል ጋዜጠኞችና ቤተሰቦቹ ጥያቄ አቅርበው አይቻልም የሚል ተሰጥቷቸው የነበረ ቢሆንም ጉዳዩን የተመለከቱት ሴት ዳኛ ቤተሰቡ እንዲገባ በማዘዛቸው ባለቤቱ ችሎቱን ተከታትላለች፡፡

የዳንኤል ጉዳይ እየታየ በነበረበት ሰዓት የሺዋስ አሰፋን የያዘችው መኪና ፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ ደረሰች፡፡ለደቂቃዎች ያህልም የሺዋስ በመኪናው ውስጥ እንዲቆይ ተደረገ፡፡ዳንኤልና ዘላለም እንደጨረሱና ግቢውን እንዲለቁ ከተደረጉ በኋላ የሺዋስ እንዲገባ ተደረገ፡፡ሙሉ ነጣ ያለ ቱታ ያጠለቀው የሺዋስ ግቢው ውስጥ እንደገባ ደመቅ ያለ ጭብጨባና በርታ የሚሉ መልእክቶች ጎረፉለት፡፡ፖሊሶች በጭብጨባውና በመልእክቶቹ ደስተኞች አለመሆናቸውን ቢገልጹም ከውስጥ ፈንቅለው የሚወጡ ስሜቶችን በቁጣና ማስፈራሪያ ሊያስቆሙ እንደማይችሉ የተረዱ ይመስሉ ነበር፡፡

የሺዋስ እንደሁልገዜው ዘና ያለና የተረጋጋ ነው፡፡ፈገግታውን በመርጨትና ሰላምታ በመለገስ የታሰሩ እጆቹን እያወዛዘወዘ ችሎት ገባ፡፡የሺዋስ የውስጥ ጉዳዩን ከውኖ እንደጨረሰም በተመሳሳይ የወዳጆቹና የትግል አጋሮቹ ጭብጨባና አድናቆት ታጅቦ ግቢውን ለቀቀ፡፡
በመጨረሻም ሐብታሙ አያሌው ወደ ውስጥ እንዲገባ ተደረገ፣ ሐብታሙ እግሮቹ ግቢውን እንደረገጡ ተሰብስበው ለጠበቁት ሰዎች ጥልቅ ፈገግታውን በመለገስ ሰላምታ አቅርቧል፡፡‹‹እንወድሃለን፣አይዞን››የሚሉ ቃላት ከደማቅ ጭብጨባ ጋር በግቢው አስተጋቡ፣ አጃቢዎቹም ፈጠን እንዲል እየወተወቱት ችሎት አስገቡት፡፡

ከወጣት ዘላለም በስተቀር በዕለቱ ችሎት ጠበቃ ተማምና ገበየሁ ታሳሪዎቹን ወክለው ቀርበዋል፡፡ሀብታሙ በመጣበት አጀብ ግቢውን እንዲለቅ ከተደረገ በኋላ ሁለቱ ጠበቆች ‹‹ተለዋጭ ቀጠሮ ለነሀሴ 26/2006 መሰጠቱን አውስተዋል፡፡ፖሊስ በዛሬው ችሎት በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምንም አይነት ማስረጃ አለማቅረቡን መረጃ ለማሰባሰብ እንዲረዳው የጠየቀው ቀን እንደተሰጠውም አብራርተዋል፡
ምንጭ፦ ዘ- ሐበሻ


Wednesday, August 6, 2014

አፍሪካ እየተመነደገች ነው ሲሉ ፕ/ት አቦማ ተናገሩ

ከ40 በላይ አፍሪካ መሪዎችን በአንድ ጊዜ ጋብዘው በማነጋገር ላይ ያሉት የአሜሪካው መሪ ፕ/ት ባራክ ኦባማ አፍሪካ እያደገችና ጠንካራ

አህጉር እየሆነች መሆኑን ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም እንደነበረው ሳይሆን አፍሪካ በአለም ላይ ተጽእኖ ፈጣሪ መሆን መጀመሩዋን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
የአፍሪካ ስኬት ከወጣት ህዝቦቿ ጋር የተያያዘ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ አክለዋል። አሜሪካ በአፍሪካ የጸጥታ ስራ ለመስራትና ለኢንቨስትመንት 14 ቢሊዮን ዶላር መመደቡዋን አስታውቀዋል። ይህ ገንዘብ ቻይና በአፍሪካ ኢንቨስት ካደረገቸው ጋር ሲተያይ እጅግ አነስተኛ መሆኑን ተንታኞች ይናገራሉ። የአሜሪካ ዋና ፍላጎት ቻይና በአፍሪካ ላይ እየፈጠረችው ያለውን ተጽእኖ መቀነስ መሆኑን የሚገልጹት ተንታኞች፣ አሜሪካ ለረጅም ጊዜ ይዛ የቆየችውን” የዲሞክራሲና የሰብአዊ መብቶች” መስፈርትን ወደ ጎን በማለት ከአንባገነን የአፍሪካ መሪዎች ጋር ቀረቤታ መፍጠሩዋ፣ በቀሪው የአፍሪካ ህዝብ ዘንድ ሊያስጠላት እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ።
ቻይና በአፍሪካ ከፍተኛ ኢነቨስትመንት ቢኖራትም፣ የህዝብ ተቀባይነት እንደሌላት ለዚህም ዋና ምክንያቱ በሙስና ከተዘፈቁትና ከአንባገነን መሪዎች ጋር የፈጠረችው ግንኙነት ነው ይላሉ። ፕ/ት ኦባማ በመጨረሻው ጉባኤ በመልካም አስተዳደር እና በጸጥታ ዙሪያ ከአፍሪካ መሪዎች ጋር እንደሚመክሩ ተነግሯል፡፡
ምንጭ፦ ኢሳት/August 6,2014

የአንድነት ፓርቲ የወረዳ 23 ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ መኳንንት ብርሀኑ በደህንነት ኃይሎች ጉዳት ደረሰባቸው

Aug 06, 2014

የአንድነት ፓርቲ የወረዳ 23 ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ መኳንንት ብርሀኑ በትላንትናው ዕለት ከጠዋቱ በ3:00 ሰዓት 3 የደህንነት ሀይሎች ቤቴ ድረስ መጥተው ከቤትህ እናስለቅቅሀለን በማለት ግብግብ ፈጥረው ግንባሬ ላይና እጄ ላይ ጉዳት አድርሰውብኛል ሲሉ ለፍኖተ ነፃነት ገልጸዋል።
በሰላማዊ መንገድ እየታገለ ያለውን ፓርቲያችንን እንደዚህ አይነት አፀያፊ ድርጊት የገዢው ፓርቲ ባሰማራቸው የደህንነት ሀይሎች እየተፈጸመ ያለ ሲሆን፣ ድብደባውና እንግልቱ ቢቀጥልም በሰላማዊ መንገድ ትግላችንን ከማድረግ የሚያቆመን የለም በማለት አቶ መኳንንት ብርሀኑ ለፍኖተ ነፃነት ገልፀዋል።።

Tuesday, August 5, 2014

የዋሽንግተኑን የአፍሪቃ መሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያውያን ተቃወሙ


"ኦባማ ዝምታው ይብቃ"
ethio us


ኢትዮጵያውንና ኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን በዛሬው እለት በዋሽንግተን ዲሲ የተከፈተውንና በዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ከአፍሪቃ መሪዎች ጋር የሚያደርጉትን ጉባኤ በመቃወም አደባባይ ወጥተዋል።
“በኢትዮጵያ የሚታየው የሰብዓዊ መብት ረገጣ እንዲቆም አዎንታዊና ተጨባጭ ግፊት በማድረግ ፋንታ፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶቹን አራማጆች በመደገፍ ሁኔታው ይበልጥ እንዲባባስ እያደረገ ነው፤” ሲሉ ከተለያዩ የዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች የመጡ መሆናቸውን ያስታወቁት የሰልፉ ተሳታፊዎች የኦባማን አስተዳደር ኮንነዋል።
ስብሰባውን አስመልክቶ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ወደ ርዕሰ-ብሔርነቱ በዘለቁ ወቅት ሃገራቸው ከነበረችበት የምጣኔ ኃብት ድቀት አሁን እያገገመች በመሆኗ ትኩረታቸውን ለአፍሪካ እየሰጡ መሆኑን የሚያሳዩ ክንዋኔዎችን እያደረጉ ነው በማለት ቀድሞ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሣደር የነበሩትና የጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር ዴቪድ ሺን መናገራቸውን ያሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ዘግቦ ነበር፡፡
ከሱዳኑ ፕሬዚዳንት በስተቀር ያልተጋበዙት መሪዎች አለመጋበዝ ትክክለኛ ውሣኔ ነው ብለው እንደማያስቡም ተናግረዋል – አምባሳደር ሺን፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የመጭው ሣምንት የአፍሪካ መሪዎች የዋሺንግተን ጉባዔ ይህንን ጉባዔ የረጥነው ከአፍሪካ ጋር ያለንን ግንኙነት ለማሳደግ መወሰናችንን መልዕክት ለማስተላለፍ ነው ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ የሥልታዊ ግንኙቶች የብሄራዊ ፀጥታ ምክትል አማካሪ ቤን ሮድስ ተናግረዋል፡፡
ሚስተር ሮድስ፣ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ እና የዩናይትድ ስቴትስ የብሔራዊ ፀጥታ ምክር ቤት የልማትና የዴሞክራሲ ከፍተኛ ዳይሬክተር ጌል ስሚዝ ጉባዔውን አስመልክቶ ከትናንት በስተያ ምሽት ላይ ከጋዜጠኞች ጋር ባካሄዱት የአንድ ሰዓት የስልክ ቃለ-ምልልስ የመጭውን ሣምንት ጉባዔ ይዘትና አካሄድ አብራርተዋል፡፡
የተቃውሞ ሰልፉን በተመለከተ በድምጽ የተጠናቀረውን ለማዳመጥ እዚህ  ወይም እዚህኛው ላይ ይጫኑ::

Monday, August 4, 2014

አንድ መቶ ሰባ አምስት ኪሎ ወርቅ ከሃገር ሊወጣ ሲል ቢያዝም በሳሞራ የኑስ ትእዛዝ እንዲያልፍ ተደርጓል።





  • 661
    Share
የጄኔራል ሳሞራ የኑስ እንደሆነ የሚጠረጠረው አንድ መቶ ሰባ አምስት ኪሎ ወርቅ ከአገር ሊወጣ ሲል ተይዞ የነበረ ቢሆንም በጄኔራሉ ትእዛዝ ከአገር እንዲወጣ መደረጉን የአየር መንገዱ የደህንነት ምንጮች ጠቁመዋል። ይህ በሁለት ካርቶን ታሽጎ በበረራ ቁጥር 600 እና 612 ወደ ዱባይ ሊሻገር ሲል በቁጥጥር ስር የዋለው ወርቅ በጊዜው ባለንብረቱ ተፈልገው ባለመገኘታቸው እንዲቆይ ቢደረግም ጄኔራል ሳሞራ የኑስ ቦታው ድረስ አሽከሮቹን በመላክ እንዲለቀቅ እና እንዲያልፍ/እንዲጫን የተደረገ መሆኑ ታውቋል።

ይህ የሃገር ሃብት የሆነን ወርቅ የወያኔ ባለስልጣናት ካለምንም ገደብ በማሸሽ እና በመዝረፍ ላይ የተሰማሩ ሲሆን ፒያሳ አከባቢ በሚገኘው በአፍሪካ ወርቅ ቤት ሽፋን እንዳልካቸው እና ዳንኤል በሚባሉ ስሞች በሚሊዮን ዶላሮች የሚገመት የወርቅ መጠን ከአገር በማስወጣት እና እንዲሁም የውጪ ወርቆችን ካለምንም የቀረጥ ክፍያ ወደ ሃገር ውስጥ በማስገባት ስራ ላይ መሰማራታቸው በተጨማሪም ሃገሪቷ የምታገኛቸው የውጪ ምንዛሬዎች በጥሬው እየታሸጉ ከሃገር እንደሚወጡ ታውቋል።
ምንጭ፦ ሚኒሊክ ሳልሳዊ

ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ መሪዎች አሜሪካ ከመግባታቸው በፊት የኢቦላ ቫይረስ እንደሚመረመሩ ተገለጸ

እዚህ ሰሜን አሜሪካ ከነገ ጀምሮ በሚደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ የሚሳተፉ ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የአፍሪካ
መሪዎች ስብሰባው ውስጥ ከመግባታቸው አስቀድሞ ከኢቦላ ቫይረስ ነፃ መሆናቸውን ምርመራ እንደሚያደርጉ ፕሬዚዳንት
ባራክ ኦባማ አስታወቁ።
ከ729 ሰዎች በላይን የገደለውና በርካቶችን በቫይረሱ ተጠቂ ያደረገው ኢቦላ በአሁኑ ወቅት የታማሚዎች ቁጥር ከ 1 ሺህ 200
በላይ እንደሚሆንና ቫይረሱም ከአገራቱ አልፎ በስፋት በመሰራጨት የአህጉሪቷ ብሎም የዓለም ስጋት ሊሆን እንደሚችል
ባለሙያዎች የሰጡትን አስተያየት በመጥቀስ ሲኤን ኤን መዘገቡ አይዘነጋም።
በጊኒ፣ በሴራሊዮን እና ላይቤሪያ በርካቶችን እየፈጀ ያለውና የአፍሪካም ትልቁ ስጋት እንደሆነ የሚነገርለት ይኸው በሽታ ወደ
ስሜን አሜሪካ እንዳይሰራጭ መንግስታቸው በሰፊው እየሰራ እንደሚገኝ ያስታወቁት ባራክ ኦባማ ይህ ለ3 ቀናት በዋሽንግተን
ዲሲ የሚደረገው በዚህ ትልቅ ስብሰባ ላይ ከ50 በላይ የአፍሪካ መሪዎች የሚገኙ ሲሆን ሁሉም የኢቦላ ምርመራ እንደሚያደርጉ
ገልጸዋል። ይህ ሰሚት (ስብሰባ) ነገ ኦገስት 4 ተከፍቶ ኦገስት 6 ቀን 2014
ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሲዲሲ የተባለው የአሜሪካ የጤና ተቋም ባለፈው ሰኞ በሰጠው መግለጫ፣ በአገሪቱ ይህ ነው የሚባል
የኢቦላ ወረርሽኝ ስጋት እንደሌለ አረጋግጧል፡፡ ይህም ሆኖ ግን በሽታው አደገኛ በመሆኑ መጠንቀቅ ይበጃል ብሏል ተቋሙ፡፡
በሽታው ከተከሰተባቸው የአፍሪካ አገራት የሚመጡ መንገደኞችን ወደ አሜሪካ አለማስገባት ሁነኛ መከላከያ መላ ነው ይላሉ-
የሲዲሲ ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት ዶ/ር ማርቲ ሴትሮን፡፡ በቅርቡ ከእነዚያ አገራት የመጡና የኢቦላ ምልክቶች የተሰሟቸው
ሰዎችም፣ ዛሬ ነገ ሳይሉ በአፋጣኝ ወደ ህክምና መሄድ እንደሚኖርባቸው ዶክተሩ መክረዋል፡፡ በአገራቱ የሚኖሩ ዜጎችም፣
የበሽታውን መተላለፊያ መንገዶች ጠንቅቀው በመረዳት ራሳቸውን እንዲጠብቁ ተናግረዋል፡፡

Sunday, August 3, 2014

ሠራዊቱ የህዝብ ወገንተኛነቱን የሚያስመሰክርበት ግዜ እየመጣ ነው

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የቀደመው ትውልድ ከቱርክ ኤምፓየር፤ ከግብፅ እና ከደረቡሽ፤ ከጣሊያን ወራሪ፤ ከሶማሊያ ተስፋፊ ኃይል እና ከሌሎችም የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ተዋግቶ አገሪቷን ለአሁኑ ትውልድ ለማቆየት ትልቅ መስዋዕትነት ከፍሏል። በተለይ ነፍጥ አንግቦ የተሠለፈው ኃይል የከፈለው የህይወት መሥዋዕትነት የሚረሳ አይደለም። አገራችን ኢትዮጵያ ለዛሬው ትውልድ የቆየችው ከራሱ ይልቅ ለአገርና ለወገን የሚያስብ ትውልድ በመኖሩ መሆኑ የሚያከራክረን ጉዳይ አይሆንም።

የአገር መከላከያ ሠራዊት እና የአገር ደህንነት ኃይል የቆመው አገርን ከጥቃት ለመከላከል ነው። አገር በጠላት እጅ ወድቃ በወገን ላይ ስቃይ እንዳይደርስ፤ ህዝቡም አገር አልባ እንዳይሆን መጠበቅ የአገሪቷ የሠራዊትና የደህንነት ኃይል ዋና ተግባር ነበር። ህወሃት መራሹ መንግስት አገሪቷን ከተቆጣጠረ ዘመን ጀምሮ በኢትዮጵያ ሥም የቆመው ሠራዊት እና የደህንነት ኃይል ተግባሩ ሌላ ሁኗል።
በዚህ ዘመን ሠራዊቱና የደህንነት ኃይሉ የአገርን ብሄራዊ ደህንነት የሚጠብቅ ሳይሆን ህወሃት የተባለውን ዘረኛና ዘራፊውን ቡድን የሚጠብቅ ኃይል መሆንን እንዲመርጥ ሁኖ አገርን ከጠላት የመከላከል ተግባሩን ረስቷል። ይህን ኃይል የሚመሩትም ደማቸውንና አጥንታቸውን ቆጥረው ከአንድ መንደር/ጎሣ የተሰባሰቡ እና ካርታ ይዘው የቆሙበትን ሥፍራ እንኳን ለመለየት የማይችሉ መሃይማን መሆናቸው አገሪቷ ያለችበትን አደጋ ከሚያመላክቱ ምልክቶች መካከል አንዱ ነው። ህወሃቶች የደርግ ሠራዊት እያሉ ሊሳለቁበት የሚሞክሩት የቀድሞው የአገሪቷ መከላከያ ኃይል ሲመራ የነበረው አውሮፓና አሜሪካን ድረስ ተጉዘው በተማሩ፤ ማዕረጋቸውም የዓለም ዓቀፉን ደረጃ የጠበቀ፤ አገሪቷን ወክለው አደባባይ ቢወጡ የሚያኮሩ እንደነበረ የታወቀ ነው። የሹመታቸው መሠረትም ደምና አጥንት ሳይሆን እውቀታቸው፤ ችሎታቸውና ወታዳራዊ ብቃታቸው ነበረ።በህወሃት የሚመራውን ሠራዊትና የደህንነት ኃይል የሚመሩት ቡድኖች ከቀድሞዎቹ ሥርዓት የጦር መሪዎች ጋር ሲወዳደሩ የጫማቸውን ጠፍር እንኳ ለመፍታት የሚታጩ አይሆኑም።ግዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል እንደሚባለው ሆነና ጨካኞችና ነፍሰ ገዳዮች በወንበሩ ቁጭ ብለው የአገሪቷን ውድቀት እያፋጠኑት ይገኛሉ።
ዛሬ ህወሃቶች በወንበሩ ቁጭ ብለዋል። እነዚህ ከጭካኔ በቀር እንጥፍጣፊ የአገር ፍቅር የሌላቸው ቡድኖች አቋቋምን ያሉት ሠራዊትና የደህንነት ኃይልም አገሩንና ወገኑን ከመጠበቅ ይልቅ የገዛ ወገኑን የሚያሸበር ቡድን እንዲሆን ተደርጓል። ሠራዊቱ እና የደህንነት ኃይሉ ለአገርና ለትውልድ እንዲያስብ ሳይሆን የጥቂት ዘረኞችን ዕድሜ ለማራዘም ዘብ የቆመ ኃይል እንዲሆንም ሁኗል። ህወሃት እየፈጠረ ያለው ሠራዊትና የደህንነት ኃይል በጀግና ማዕረግ አገሩንና ህዝቡን ከጥቃት ተከላክሎ በህዝቡ ተከብሮና ተወዶ እንዲኖር ሳይሆን በጭካኔው ታውቆ እና የወገኑን ፍቅር አጥቶ በስነ ልቦና ቀውስ ውስጥ የሚኖርን ኃይል ነው። እንዲህም ሁኖ በመቀረፁ ግደል ሲባል ገስግሶ ሂዶ የገዛ ወገኑን ይገድላል። አፍርስ ሲባል ፈጥኖ በብዙ ድካምና ወጪ የተገነባውን የወገኑን መኖሪያ ቤት ያፈርሳል። እሠር ሲባል ህፃን ከአዛውንት ሳይለይ ያገኘውን ሁሉ ወደ ወይኒ ቤት ያግዛል። በእንዲህ ሁኔታ ከወገኑ ተለይቶ፤ በወገኑ ላይ ዘምቶ፤ ወገኑን ወግቶ፤ ወገኑን አሥሮና አሰቃይቶ ራሡም እንደገና በክፉ ድርጊቱ ታሥሮ እንዲኖር ሁኗል።
ህወሃት የፈጠራችሁ እና በአገር መከላከያ እና ደህንነት ኃይል ሥም ቁማችሁ በወገኖቻችሁ ላይ እንድትዘመቱ የተደረጋችሁ የሠራዊቱና የደህንነት ኃይሎች አድምጡ። አሁን አገራችን ባለችበት ሁኔታ ለኢትዮጵያና ለህዝቧ ዋነኛው ጠላት ህወሃት ነው። ህወሃት የዘረኞችና የዘራፊዎች ስብሰብ ነው። የዘረኝነታቸው መገለጫ ብዙ ነው። የሚያዙህ ጄኔራል ተብየዎች ደማቸውን ቆጥረው የተጫኑብህ መሆናቸውን ተመለከት። እነዚህ ጄኔራሎች አገሪቷን ከተቆጣጠሩ ዘመን ጀምሮ ያካበቱትን የሃብት ብዛት ተመልከት። ሁሉም በሚሊዮን የሚቆጠር ሃብት ባለቤት ናቸው። ልጆቻቸው በአውሮፓና በአሜሪካን ይማራሉ። ሚስቶቻቸው አውሮፓና አሜሪካን እየሄዱ እንዲወልዱ ይደረጋል።ይሄን ለምን ያደርጋሉ ቢባል እየገዙ ያሉት አገር የራሳቸው አገር ስለመሆኗ ብርቱ ጥርጣሬ ስላላቸው ነው። ህዝቧንም እንደ ወገኖቻቸው ለማየት ሥር የሰደደ ጥላቻማላቸው። አንተ እና ወገኖችህ ግን ከሙታን ትንሽ ከፍ ብላችሁ፤ ከሚኖሩት እገር ሥር ተረግጣችሁ የህወሃቶች አኗኗሪ ሁናችሁ የመከራውን ዘመን ትቆጥራላችሁ። በድህነት የሚወቅሯችሁ እንሷቸው ይሄና አስባችሁ፤ ያንን ተናገረችሁ እያሉ በዓለም ላይ በተከለከለ የቶርቸር ዓይነት እንድትሰቃዩ ትደረጋላችሁ። ይህ የጠላት ተግባር ነው።አሁን ባለንበት ዘመንም የኢትጵያ ዋነኛው ጠላት ህወሃት መሆኑን ያለምንም ጥርጣሬ ማመን ይኖርባችኋል።
ህወሃትን ጠላት የሚያድረገው ምንድ ነው ?
ህወሃቶች ወደ ስልጣን ከመጡ ዘመን ጀምሮ ሁለት ሚሊዮን አማራ ጠፍቷል። ይሄ ሁሉ አማራ የት እንደገባ ህወሃት እስከ አሁን አልተናገረም። ይሄ ዘረኛ ቡድን አገሪቷን ከተቆጣጠረ ዘመን ጀምሮ በዜጎች መካከል ሊኖር የሚገባው መተማመን ጠፍቷል። በዚህም ምክንያት ዜጎች ከኖሩበት ሥፍራ እየተነቀሉ ሜዳ ላይ እንዲወድቁ ሁኗል። ይሄ ዘራፊ ቡድን አገሪቷን ከተቆጣጠረ ግዜ ጀምሮ ከአገሪቷ ውስጥ በስምንት ዓመታት ውስጥ ብቻ ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተዘርፎ በውጪ አገራት ባንኮች ውስጥ ተደብቋል። ይህ ቡድን ስልጣኑን ከተቆጣጠረ ዘመን ጀምሮ ከአገሪቷ በሚሰደዱ ምሁራን፤ ጋዜጠኞች፤ የኃይማኖት አባቶች እና በሌሎች ዜጎች ቁጥር ኢትዮጵያን የሚያክል አልተገኘም። ህወሃት የተባለው ዘረኛ እና ዘራፊ ቡድን አገሪቷን ከተቆጣጠረ በኋላ አባቶች በደምና አጥንታቸው ያቆዩት ድንበር እየፈረሰ እና ኢትዮጵያዊያን እየተፈናቀሉ ሜዳ ላይ ተጥለው መሬቱ ለባእዳን እየተሰጠ ነው። ይሄ ቡድን አገሪቷን ከተቆጣጠረ ዘመን ጀምሮ ድሃ ሜዳ ላይ ተጥሎ የድሃውን መሬት ህወሃቶች እየነጠቁ ባለሃብት ነን ብለዋል። ይሄ ቡድን አገሪቷን ከተቆጣጠረ ዘመን ጀምሮ ሃሳብን በነፃ መግለፅ አሸባሪነት ሁኗል። ህወሃትን መንቀፍ በሞት የሚያሰቀጣ ወንጀል እስከመሆን ደርሷል። ኢትዮጵያ ይህን በሚመስለው ጠላት እጅ ተይዛለች።
ኢትዮጵያን ከዚህ ጠላት እጅ ለማላቀቅ የሠራዊቱና የአገር ደህንነት ኃይሉ ከፍተኛ ሚና መጫወት አለበት። ከህወሃት የበለጠ ጠላት ኢትዮጵያ የላትም፤ በታሪኳም እንዲህ ዓይነት ጠላት አይታ አታውቅም። ይህን ጠላት ወደ ከርሰ መቃብሩ የሚከት የለውጥ ባቡር እየገሰገሰ ነው። ይሄን የለወጥ ባቡር ፈፅሞ ማቆም አይቻልም። ህወሃቶች የለውጡ ባቡር በፍጥነት እየገሰገሰ እንደሆነ እያዩት ነው። በዚህም አንዳንዶቹ የዘረፉትን ሃብት ይዘው እየሸሹ ነው። ሌሎቹም የሚያደርጉትን አጥተው በዜጎች ላይ በስቃይ ላይ ስቃይ እያበዙ ነው። የሠራዊቱና የደህንነቱ ኃይል የኢትዮጵያዊያን ጠላት መሆንን ከመረጡ ዘረኞች ጎራ ራሱን ለይቶ የህዝብ ልጅ፤ የአገር ጥላ ከለላ መሆኑን አሁኑኑ ማሳየት መጀመር ይጠበቅበታል። የአገር መከላከያ አባል ስትሆን አገርህን ከጠላት ለመከላከል እንጂ ከጠላት ጋር አብረህ የገዛ ወገንህን ስቃይ ለማብዛት አይደለም። ከጠላት ጋር መወገንን ከመረጥክ ግን የተነሳው የለውጥ ባቡር አንተንም ጨፍልቆ እና ታሪክህን ከዘረኞችና ከዘራፊዎች ጎራ ፅፎ እንደሚያልፍ ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ አይኑርህ።
የእኛ እምነት ግን ከህወሃቶች ጎን ቁመህ ወንድሞችህን ትወጋለህ የሚል አይደለም። ህወሃቶች ለአንት ወንድምም ጋሻም መከታም የሚሆኑ አይደሉም። በአሁን ሠዓት የህወሃቶች ጭንቀት የዘረፉትን ሃብት የሚያሸሹበትን ሥፍራ የማግኘት ነው እንጂ የአንተ ደህንነት አይደለም። ህወሃቶችን እንቅልፍ የሚነሳቸው የሠሯቸው ትላልቅ ህንፃዎች ፍፃሜ እንጂ የኢትዮጵያዊያኑ በሠላም የመኖር ጉዳይ አይደለም። ህወሃቶች የሚሞቱለትም ሆነ የሚኖሩለት አንድ እና አንድ ምክንያት ዘርፈው ያካባቱት ሃብት እንጂ ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንዳልሆነች የታወቀ ነው። አንተ የሠራዊቱ አባል ግን የእነዚህን ዘረኞችና ዘራፊ ህወሃቶችን እድሜ ለማራዘም የምትሞተውና የምትገድለው ለምንድ ነው? የእነርሱን እድሜ ለማራዘም ብለህ ብትሞት ለህወሃቶች ወግኖ ኢትዮጵያዊያንን ሲወጋ ሞተ ተብለህ መሳለቂያ ሆነህ መቅረትህን አታውቅምን ?
እኛ ግን እንዲህ እንልሃለን ለአገርህ መሞት ክብር ነው። ለአገር መሞት ማለትም በዚያች አገር ውስጥ ለፍትህ፤ ለህግ የበላይነት፤ ለነፃነት፤ ለእኩልነት እና ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ራስን አሳልፎ መስጠት ማለት ነው።በዚህ ሞትህ ማንም ማንንም ሳይጫን፤ ማንም ማንንም ሳይሸከም መኖር የሚቻልባት አገር ተፈጥራ እኩልነት ሲሰፍን የአንት ስም በአገሪቷ እስከ ዘላለሙ ሲታወስ ይኖራል። ልጆችህና ልጅ ልጆችህ በአንተ ሥራ ኮርተውና አንገታቸውን ቀና አድርገው የሚሄዱ ይሆናሉ። ለዚህ ዘላቂ ክብር ብለህ ብትሞት ሞትህ የክብር ሞት ይሆናል። የሣሞራንና የጓደኞቹን የሥልጣን ጥም ለማርካት ብለህ ብትገልና ብትሞት ግን አሟሟትህ ከንቱ ይሆናል። ለነፃነት፤ ለእኩልነት እና ለህግ የበላይነት ብለው የተነሱ ነፁሃን ዜጎችን ለመግደል የታጠከውን ነፍጥ ብታነሳ ፍፃሜህ ከንቱ ሁኖ እንደሚቀር አትጠራጠር። የምትሞትለትም ሆነ የምትኖርለት ዋናው ቁም ነገር ሊሆን የሚገባው በህወሃቶች የተጣመመውን ፍትህ ለማቃናት፤ ወገኖችህና አንተ የተነጠቃችሁትን ነፃነት ለመቀዳጀት፤ እውነተኛ ዴሞክራሲዊ ሥርዓት በአገርህ እንዲሠፍን፤ ጥቂት ዘረኞች ብዙሃኑን ተጭነው፤ ብዙሃኑም እነዚህ ጥቂት ዘረኞችን ተሸክመው የሚኖሩበት ሥርዓት እንዲያበቃ ሊሆን ይገባዋል። ለእነዚህ ድንቅ ሃሳቦች ብለህ ብትሰዋ መስዋዕትነትህ የጀግና መሥዋዕትነት ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱ መሰዋዕትነት ለአገርና ለወገን የሚሰጥ ውድ እና ታላቅ ስጦታ ነው። ይሄን ውድ እና ታላቅ ስጦታ የሰጠ ደግሞ በታሪክ ማህደራት ውስጥ ስሙ ለዘላለም ሲታወስ ይኖራልና የለወጡን ባቡር እንድትሳፈር እንመክርሃለን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!!