Friday, August 29, 2014

በድርጅቶች ውህደትና ቅንጅት አገርን ማዳን!!!


ኢትዮጵያዊያንን በዘር እና በሀይማኖት ለያይቶን እርስ በርስ እያጋጨን በመግዛት ላይ ያለውን ወያኔን ለማሸነፍ እና ከምትኩም ከራሷ ጋር የታረቀች፤ ፍትህ የሰፈነባት፤ እኩልነት የተረጋገጠባት እና በኃያላን አገሮች እርጥባን ሳይሆን በራሷ አቅም የምትተማመን ጠንካራ ሀገር እንድትኖረን የነፃነትና የዲሞክራሲ ኃይሎት መተባበር እንዳለባቸው ሲነገርና ሲወተወት ቆይቷል። ይሁን እንጂ በህወሓት የከፋፍለህ ግዛው ፓሊሲ እና በፓለቲካ ባህላችን ኋላቀርነት ምክንያት እስካሁን የተደረጉ የትብብር ጥረቶች የተፈለገውን ውጤት ሳያስገኙ ቀርተዋል።

ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ ቀድሞ የተደረጉት ጥረቶች የተጠበቀውን ውጤት አለማስገኘት ተስፋ ሳያቆርጠን ከእያንዳንዱ ጥረት ልምድ እየወሰደን የኢትዮጵያዊያን አንድነት እስኪረጋገጥ ድረስ አዳዲስ የትብብር ጥረቶችን ማድረግ ያለብን መሆኑ ያምናል። በዚህም መሠረት የትብብር መርህ ነድፎ ትግል ውስጥ ካሉ ሁሉም የፓለቲካ ድርጅቶች ጋር ሲነጋገር እና ሲደራደር ቆይቷል። እንደሚታወቀው የንቅናቄዓችን አበይት የትብብር መርሆች ሁለት ናቸው። መርህ አንድ፣ ለውጥ እንዲመጣ የምንታገለው ኢትዮጵያ በምትባል አገር ውስጥ መሆኑ ማመን ነው። መርህ ሁለት ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም እርከኖች የመንግሥት ሥልጣን መያዝ የሚገባው በሕዝብ ነፃ ምርጫ ብቻ መሆኑን መቀበል ናቸው።
በምድር ላይ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ ኃይሎች መካከል የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር እና የአማራ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ ሁለቱንም መርሆዎች የሚያሟሉ ናቸው። እነዚህ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ከንቅናቄዓችን የተለየ አቋም የላቸውም። በአለፉት ሁለት ዓመታት ድርጅቶቹ ተቀራርበው እንዲሠሩ በመደረጉ ከአመራር አልፎ አባላት መካከል መልካም ወዳጅነት መመሥረት ተችሏል። የነፃነት ትግላችን የደረሰበት ደረጃ እና የድርጅቶቹም ቅርርብ በመገምገም ሶስቱ ድርጅቶች ማለትም የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር፣ የግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄና እና የአማራ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ መዋሃዳቸው ትግሉን ያራምዳል ተብሎ ታምኖበታል። በዚህም መሠረት ሶስቱ ድርጅቶች ለመዋሃድ ተስማምተን ስምምነታቸንን ይፋ አድርገናል። ድርጅቶቹን የማዋሃድ ዝርዝር ሥራም ተጀምሯል።
ከስትራቴጄ አንፃር የትብብር ጥረታችን በዚህ አያበቃም። በዓላማ የምንቀራረብ ሆኖ የአደረጃጀት ልዩነት ያለን የዲሞክራሲ ኃይሎች ጋር በጥምረት እየሠራን ድርጅቶቻችን ይበልጥ ለማቀራረብ ጥረት እያደረግን ነው። በዚህ ረገድ ግንባር ቀደም ተጠቃሹ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) ነው። ንቅናቄዓችን ከትህዴን ጋር ከፍተኛ በሆነ መቀራረብና መተማመን ይሠራል። ይህ መቀራረብና መተማመን ጎልብቶ አንድ የጋራ አመራር የሚፈጥርበት ጊዜ እንዲቀርብ ጥረት እናደርጋለን። ምድር ላይ ከሚገኙ ሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች ጋርም በመደጋገፍ እንሠራለን። በመጨረሻም ተግባራዊ እንቅስቃሴ ላይ ካሉ ማናቸውም ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ጋር ለመወያየት ዝግጁዎች መሆናችንን ደግመን እናረጋግጣለን። ልዩነቶቻችን ማጥበብ እንኳን ባንችል የምንተባበርባቸው መንገዶች ይኖራሉ ብለን እናምናለን።
የጦር ኃይሉንና የስለላ መዋቅሩን ዘረኛ በሆነ መንገድ የገባውንና የኢትዮጵያን ሀብት በመዝረፍ የደረጀው ህወሓትን ለማሸነፍ ትብብር ወሳኝ ጉዳይ ነው። ከወያኔ አገዛዝ ውድቀት በኋላ ወደ ተረጋጋ ሰላምና ልማት ፊታችንን የምናዞር መሆናችን ዋስትና የሚሰጠን በአንድ እዝ የሚመራ የአገር አድን ሠራዊት ማደራጀት ስንችል ነው። የአሁኑ ውህደት የዚህ አገር አገር አድን ሠራዊት ጥንስስ ሊሆን ይችላል ብለን እናምናለን።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከወያኔ በኋላ የሚመጣው ምን እንደሆነ ባለማወቅ ሥጋት ውስጥ ሊገባ አይገባም። በዋና ዋና የአገሪቱ የፓለቲካ ድርጅቶች ውህደት እና ቅንጅት የተዋቀረ በአንድ ማዕከላዊ አመራር ሥር የሆነ አገር አድን ሠራዊት በተቻለ ፍጥነት ሊገነባ ይገባል።
ሶስቱ ድርጅቶች ለማድረግ በወሰነው ውህደት የዚህ የአገር አድን ሠራዊት ምሥረታን ጀምረናል። ስለኢትዮጵያ እና ሕዝቧ ወይም በኢትዮጵያ ውስጥ ላለ ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ደህንነት ያገባናል የምትሉ ወገኖቻችን ሁሉ በዚህ አገር አድን ሠራዊት ምሥረታ ላይ እንድንነጋገር አበክረን እንጠይቃለን።
የኢትዮጵያ ሕዝብም የትብብሩ መንፈስ አገርን የማዳን ግብ ያለመ መሆኑን በመገንዘብ ከተባበረው ድርጅት ጎን እንዲቆም ጥሪ እናደርጋለን። የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ጉዳይ የሚያገባው ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንዲቀላቀለንና እንዲያግዘን ጥሪዓችንን እናቀርባለን።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

Thursday, August 28, 2014

13 የኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣኖች እና የጦር መኮንኖች በስዊዲን አለም አቀፍ የጦር ፍርድ ቤት ክስ ተመሰረተባቸው



አስራ ሶስት የኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣኖች እና የጦር መኮንኖች በስዊዲን ሀገር በሚገኘው አለም አቀፍ የጦር ፍርድ ቤት በስዊዲን ከፍተኛ ጠበቆች ክስ ተመሰረተባቸው። እነዚህ ተከሳሾች በግድያ፣ አስገድዶ በመድፈር፣ በስቃይ እንዲሁም ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ማሰርና ማሰቃየት እና በሌሎች ተመሳሳይ ወንጀሎች ክስ ተመስርቶባቸዋል። ክሱንም አለም አቀፍ የወንጀል ምርመራ ፓሊስ መረከቡ ታውቋል። ጉዳት ለደረሰባቸው ኢትዮጵያውያንም የአንድ መቶ ሰላሳ ሚሊዮን የስዊዲን ክሮነት ካሳ ተጠይቆባቸዋል። ክስ የተመሰረተባቸው ተከሳሾች ስም ዝርዝር እንደሚከተለው ቀርቧል።
የክስ መዝገቡ ሲቀርብ

1    አቶ አርከበ እቁባይ
2    አቶ አባዱላ ገመዳ
3    አቶ በረከት ሰምኦን
4    አቶ ሳሞራ የኑስ
5    አቶ አባይ ፀሀዬ
6    አቶ ጌታቸው አሰፋ
7   ሌ/ጀነራል ታደሰ ወረደ
8   አቶ ሀሰን ሽፋ
9   አቶ ሙሉጌታ በርሄ
10 አቶ ነጋ በርሄ
11  አቶ ወርቅነህ ገበየሁ
12 ኮማንደር ሰመረ እና አንድ ስማቸው ያልተገለፀ ሰው ይገኙበታል። ዜናውን ለመስማት ሊንኩን ይጫኑ
http://ethsat.com/video/esat-breaking-news-charges-against-ethiopian-officials/

Monday, August 25, 2014

ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል


ፕ/መስፍን ወልደ ማርያም
August 24, 2014

ጉልበት አራዊት የሚተዳደሩበት ሕግ ነው፤ ሕገ አራዊት የሚባለው አራዊት የሚተዳደሩበት ጉልበት ነው፤ በአራዊት ዓለም ማናቸውም ነገር በጉልበት ያልቃል፤ በሰዎችም መሀከል ጉልበት አድራጊ-ፈጣሪ ሆኖ ጎልቶ ሲወጣ የአእምሮንና የኅሊናን መዳከም ወይም ጭራሹኑ አለመኖር ያመለክታል፤ ጉልበት አለን በማለት፣ ወይም ተመችቶናል በማለት፣ ወይም ጠያቂ የለብንም በማለት የማንኛውንም ሰው ሰብአዊ መብቱንና ሰብአዊ ክብሩን መግፈፍ ሦስት ነገሮችን ያመለክታል፤ አንደኛ ጉልበት እንጂ አእምሮና ኅሊና እንደሌለ፣ ሁለተኛ ጉልበት እንጂ ሕግ እንደማይከበር፣ ሦስተኛ በአንተ ላይ እንዲያደርጉብህ የማትፈልገውን አንተም በሰዎች ላይ አታድርግ የሚለውን ሕግ መጣስን ያሳያል፤ በመጨረሻም፣ ዘግይቶም ቢሆን በራስ ላይ ቅሌትን መጋበዝን ያስከትላል፤ የሌላውን ሰውነት ስናረክስ ሰውነትን በጠቅላላው ማርከሳችን ነው፤ ሰውነትን በጠቅላላው ስናረክስ ራሳችንን ከነጉልበታችን ማርከሳችን ነው፤ ራሳችንን፣ ሰውነታችንን ካረከስን በኋላ ዋጋ የለንም፤ ለራሳችን ዋጋ ከሌለን ለሌለች ሰዎችም ዋጋ አንሰጥም፤ ያኔ ክፉ በሽታ ይይዘናል፤ እግራችን ስር በወደቀ ሰው ስቃይ የምንደሰትና የምንስቅ፣ የምንፈነድቅ እንሆናለን፤ ያን ጊዜ የለየለት በሽተኛ ሆነናል።

professor mesfin 6
ይሄ በሽታ ያቃዣል፤ ከሰው ሁሉ በላይ ያሉ ያስመስላል፤ አግሩ ስር የወደቀው አንድ ሰው የሰው ልጅ በሙሉ ይመስለዋል፤ በሽተኛነቱን ስለማያውቅ በሽታው ከሰው በላይ ያደረገው ይመስለዋል፤ እንዲህ ዓይነቱ በሽተኛ በሕግ አሰከባሪነት ሥራ ውስጥ ሲገባ ሕግ የአንድ ማኅበረሰብ ትምክህትና መከታ በመሆን ፋንታ የበሽተኞች በትር ይሆናል፤ በደርግ ዘመን የአራት ኪሎው ግርማ የሠራውን እናውቃለን፤ ዛሬ ደግሞ ልዩ ግርማዎች አሉ፤ መልካቸውን ከካሜራው ጀርባ ደብቀው በሰው ስቃይና አበሳ በሳቅ እየተንከተከቱ ጀብዱዋቸውን በቴሌቪዥን የሚደረድሩ ጀግኖች መጥተዋል፤ መሣሪያ ይዞ መሣሪያ ባልያዘ ሰው ላይ ጀግና መስሎ ለመታየት የሚሠራው ጨዋታ ራስን ክፉኛ ከማጋለጥ በቀር ሌላ ፋይዳ የለውም።


በኢትዮጵያዊ ሰውነት ላይ ማናቸውንም ከሕግና ከሰብአዊነት ውጭ የሆነ ሙከራ ለማድረግ የውጭ አገር ሰዎች ዕድሉን ይፈልጉት ይሆናል፤ ለነሱ ሰዎች ስላልሆን ሰብአዊነት አይሰማቸውም፤ ከአገራቸው ሕግም ውጭ በመሆናቸው በሕግ አይገዙም፤ ዋናው ውጤት ግን ለኢትዮጵያ ሕግ አስከባሪዎች የሚያስተምሩት ግዴለሽነት ነው፤ መታሰር በብዙ ምክንያቶች ይመጣል፤ ስለዚህ በሠለጠነው ዓለም የተለያዩ እስረኞች በተለያየ ሁኔታ ይጠበቃሉ፤ አንዳንዶቹ እንዲያውም በቤታቸው ውስጥ እየተጠበቁ ይቆያሉ፤ ኢትዮጵያ በራስዋ ሥልጣኔ በምትተዳደርበት ዘመን መሳፍንትና መኳንንት የሚታሰሩት በወርቅ ወይም በብር ሰንሰለት ነበር፤ ግዞትም፣ የቁም እስርም ነበር፤ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ እስረኞች ሁሉ እኩል ናቸው፤ በቃሊቲ ለየት ያለ አያያዝ የሚታየው ለሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች ብቻ ነው።

ጉልበትን በጉልበት እቋቋማለሁ የሚል ሰው ሲሸነፍ አያስደንቅም፤ አዲስም አይደለም፤በአለፉት አርባ ዓመታት እየተሸነፉ ከትግሉ ሜዳ ወጥተው በተለያዩ የምዕራባውያን አገሮች የሙጢኝ ብለው የተቀመጡ አሉ፤ በተባበሩት መንግሥታት ደንብ የሙጢኝ ማለት መብት ነው፤ ይህንን መብት መጣስ የመንግሥተ ሰማያትን በር መድፈር ነው፤ በጎንደር የአደባባይ ኢየሱስን ቤተ ክርስቲያን በር መድፈር ነው፤ በአዲስ አበባ የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን በር መድፈር ነው፤ በአዲስ አበባ የአንዋር መስጊድን በር መድፈር ነው፤ ወደመሬት ስንወርድም የሙጢኝ የተባለው አገርን መንግሥት መድፈር ነው፤ የተባበሩት መንግሥታት ደንብን መጣስ ነው፤ ለነገሩ የመንግሥተ ሰማያትን በር መድፈር ከተቻለ ሌላው ምን ያቅታል!

የሙጢኝ ያለን ሰው በአፈና መያዝና ወደአገር ማስገባት አንድ ችግር ነው፤ ይህ የጉልበተኛነት መገለጫው ነው፤ ሁለተኛው ችግር የተያዘው ሰው መብቱና ክብሩ ሳይጓደልበት ማስረጃዎችን ሰብስቦ ለነጻ ፍርድ ቤት አለማቅረቡ ነው፤ በቴሌቪዥን እንደታየው አካላዊ ጉዳት እንደደረሰበት ባይታወቅም፣ ጥልቅ መንፈሳዊ ጉዳት እንደደረሰበት ይታያል፤ በብዙ አገሮች ሕጎች አንድ ሰው ራሱን እንዲወነጅል አይገደድም፤ ሕጋዊ ምርመራም በቴሌቪዥን በአደባባይ አይካሄድም።

ስለዚህም በተጠርጣሪው ላይ የተደረገው ሁሉ ሕጋዊ አይደለም፤ በነጻ ፍርድ ቤት ቢቀርብም በቴሌቪዥን የተናገረው ሁሉ ቢያስታውሰውም በማስረጃነት የሚያገለግል አይመስለኝም፤ ስለዚህም ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል።
ከአፍሪካ አህጉር ወጥቶ የቀይ ባሕርን አቋርጦ አንድ ሰው፣ ገና ወደፊት ክፉ ሊሠራ ይችላል በሚል ሂሳብ በጉልበት አፍኖ ማምጣት የብዙ ነፍሶች ዕዳን ተሸክመው በኢጣልያ ኤምባሲ የሙጢኝ ብለው ተደላድለው የተቀመጡትን የደርግ አባሎች ማስታወስ ግዴታ ይሆናል፤ አድርጋችኋል የተባሉትን ሰዎች የሙጢኝ የማለት መብት አክብሮ አስበሃል የተባለውን ሰው የሙጢኝ የማለት መብት መጣስ ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል።

ከፖሊቲካና ከምናምኑ፣ ጉልበተኛነትንም ከማረጋገጡ በላይ ሌላ ትልቅ ነገር አለ፤ አገር የሚባል ነገር አለ፤ ይህ በአንድ ግለሰብ ላይ የተገኘ ጊዜያዊ ድል የአገርን ከብር የሚያጎድፍና የሚያቀል ይሆናል፤ የአንድ አገርን የመንግሥት ሥልጣን የያዘ አካል አንድ ግለሰብን በአደባባይ ከሕግ ውጭ ለማጥቃት ሲሞክር የራሱን ክብር ዝቅ ያደረግበታል፤ ስለዚህም ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል።

በእኔ ዕድሜ ሰው በአደባባይ ሲገረፍ አይቻለሁ፤ ሰው ተሰቅሎ አይቻለሁ፤ የዚያን ዘመን የእውቀት ደረጃ የዚያን ዘመን የሰው ልጆች የመንፈስ እድገት ደረጃ ያመለክታል፤ የእውቀትም የመንፈስም ደረጃ በጣም ዝቅተኛ ነበረ ማለት ነው፤ ስለዚህም ይህንን ያደረጉትን ዛሬ አንወቅሳቸውም ይሆናል፤ የታሪካችን ጉድፍ መሆኑን ግን ልንፍቀው አንችልም፤ ስለዚህም ሌላ ጉድፍ እየጨመርንበት ታሪካችንን ማቆሸሹ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ይበልጣል።

ቅጣት በሕግና በሥርዓት ይደረግ ማለት ያጠፋ ሰው አይቀጣ ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ምንም አቅም የሌለውን ሰው ይዞ በአደባባይ ማሰቃየትና ማዋረድ አገርንና ሕዝብን ማዋረድ ነው፤ የሰብአዊነትንም የሕጋዊነትንም ሚዛኖች ይሰባብራል።

አብርሃ ደስታ ሃብታሙ አያሌዉና እና ኤርትራ – ግርማ ካሳ

«ራሱን ግንቦት 7 ብሎ ከሚጠራ ድርጅት ጋር እና ከድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች በመገናኘት ፤ እንዲሁም ከባንክ በትዕዛዝ ብር በመቀበል የግንቦት 7 ተልዕኮና አላማ ለመፈፀም፤ ቁጥራቸው ከ60 በላይ የሆኑ ግለሰቦችን ለዚህ ጥፋት እንዲሰማሩ በማድረግ» የሚል ክስ ነው በወዲ ሃዉዜን/ትግራይ በሆነው አንጋፋ ፖለቲከኛ እና ብሎገር ላይ ክስ የቀረበው። ሌላው አንጋፋና አንደበተ ርትኡ፣ የሚሊዮኖች ድምጽ ንቅናቄ ግብረ ኃይል ሰብሳቢ፣ ሃብታሙ አያሌውም፣ «የግንቦት ሰባት ተባባሪ ነው» በሚል ነው ለመክሰስ ነው ዝግጅት እየተደረገ ያለው።

አብርሃ ደስታ እና ሃብታሙ አያሌው ፣ «ግንቦት ሰባትን ይደግፋሉ» የሚል ክስ ከቀረበባቸው፣ በተዘዋዋሪ መንገድ «ከሻእቢያ ጋር ወዳጆች ናቸው» ማለት ነው። ታዲያ የሻእቢያ ወዳጅ የሆነ ሰው፣ የኤርትራን መገንጠል ተቃዉሞ፣ ወይንም የኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤት መከበር እንዳለበት በማስመር ይናገራል ወይ ? እስቲ የጸረ-ሽብርና የአገር ደህንነት ተብዬው ምላሽ ይስጠን !!!
ሁላችንም እንደምናውቀው፣ በኤርትራ በኩል ትግል እናደርጋለን የሚሉ ወገኖች፣ ኢትዮጵያ የባህር በር እንደሚያስፈልጋት ሊናገሩ አይችሉም። በሻእቢያ ሥር እስካሉ ድረስ ቀይ መስመር ተሰምሮላቸዋል። እነ ግንቦት ሰባቶች፣ ኦነጎች …፣ እርዳታ የሚያገኙጥ ከሻእቢያ ማእከላቼ ደግሞ አስመራ እስከሆነ ድረስ፣ «ኢትዮጵያ የባህር በር ያስፈልጋታል» ብለው የመናገራቸው ነገር ጭራሽ የማይታሰብ ነው።

ዶር ብርሃኑ ነጋ ከቃሊት እሥር ቤት ሆነው የጻፉት አንድ መጽሃፍ ነበር። መጽሀፍ ላይ ባለው የ ኤርትራ ካርታ ፣ ኤርትራ ተቆርጣለች። ሃብታሙ አያሌው የጻፈው መጽሃፍ ላይ በሚታየው የ ኤርትር ካርታ ኤርትራ አልተቆረጠችም። ሃብታሙ አያሌው፣ ምንም እንኳን ሻእቢያና ሕወሃት/ኢሕአዴግ ከመረብ በስተሰሜን እና በስተደቡብ ያለዉን ሕዝብ ከፋፍለው፣ በደም ቢያቃቡትም፣ «ሰላማዊ በሆነ መንገድ፣ ሁለቱም ወገኖች አሸናፊ በሆኑበት መልኩ፣ ወንድማማቾችን አንድ ማድረግ ይቻላል» የሚል እምነት ስላለው ነው፣ ኤርትራ ከተቀረው የኢትዮጵያ አካል ጋር የቀላቀላት። ከ23 አመታት በፊት ያለው አስቦ ሳይሆን ፣ ወደፊት የሚሆነው ታይቶት ነው። ታዲያ ይህ አይነት ፖለቲከኛ ነው የሻእቢያ አሽከር ነው ተብሎ የሚከሰሰው ?
ወደ አብርሃ ደስታ ልውሰዳችሁ። በቅርብ ጊዜ ስለ አሰብ የጻፈው አስደናቂ ጽሁፍ ነበር። «ጦርነት ፈርተን ግን ሐገራችንን አሳልፈን አንሰጥም» በሚል ርእስ፣ በአደብ ጉዳይ ላይ፣ አብርሃ ደስታ ሲጸፍ « እኛ ጦርነት አንፈልግም። ሕጋዊ ንብረታችን (ወደባችን) በሰለማዊ መንገድ እንዲሰጠን ነው የምንጠይቀው። አዎ! ጦርነት አንፈልግም። ጦርነት አንፈልግም ማለት ግን ጦርነት ከፍተን በሃይል የሌላ ሀገርና ህዝብ ንብረት አንወርም ማለት እንጂ ጦርነት ፈርተን ልአላዊ ግዛታችን (ሃብታችን) ለሌሎች ሃይሎች አሳልፈን እንሰጣለን ማለት አይደለም። ጦርነት አንፈልግም ማለት ጦርነት እንፈራለን ማለት አይደለም። አዎ! ጦርነት ስለማንፈልግ ሌሎች ህዝቦችን አንወርም። ጦርነት ፈርተን ግን እናት ሀገራችን አናስደፍርም» ነበር ያለው።
ታዲያ በምን መሰፍርትና ሚዛን ነው አቶ ሃብታሙ አያሌው እና አቶ አብርሃ ደስታ የ«ሻእቢያ ተላላኪ» የሚሆኑት ? በምን መስፈርት ነው ግንቦት ሰባቶች ሊባሉ የቻሉት ?
«ህወሓት በራሱ ኮ የሻዕቢያ ተልእኮ ለማስፈፀም በሻዕቢያ የተቋቋመ ድርጅት ነው። ህወሓት የመሰረተው ማነው? ሻዕቢያ ነው። ሻዕቢያ መሓሪ ተኽለ (ሙሴ) የተባለ ኤርትራዊ የሻዕቢያ አባል በትግራይ ለሻዕቢያ ሊያግዝ የሚችል ድርጅት እንዲያቋቁም ወደ ኢትዮዽያ ላከ። እነዚህ ህወሓት የመሰረቱ የሚባሉ ሰባት ሰዎች አሰባስቦ እንዲደራጁ አደረገ» ብሎ አብርሃ ደስታ እንደጻፈው፣ ለሻእቢያ ዉስጥ ዉስጡን የሚቆረቀረዉስ ሕወሃት አይደለችንም ? ያ ባይሆን ኖሮ ተሽቀዳድሞ የአልጀርስ ስምምነት ይፈረም ነበርን? ያ ባይሆን ኖሮ አገር ቤት ካሉ ሰላማዊ ተቃዋሚዎች ጋር አልነጋገርም እያሉ፣ የሕወሃት/ኢሕአዴጉ ዳግማዊ መለስ ዜናዊ፣ ኃይለማሪያም ደሳለኝ «ካስፈለገም አስመራ ድረስ እሄዳለሁ» ይሉ ነበርን ?

እርግጥ ነው እነዚህ ሁለቱ አንጋፋ ወጣት ፖለቲከኞች፣ ኢሳት በተሰኘው ሜዲያ ቀርበው ቃለ ምልልስ አድርገዋል። አቦይ ስብሐት ነጋ፣ አምባሳደር ቪኪ ሃደልሰን፣ ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን፣ ወንጌላዊ ዳንኤል ጣሰው ..የመሳሰሉትም በኢሳት ቀርበዋል። ታዲያ እነ አባይ ስብሐት ፣ «ኢሳት ላይ ቀረባችሁ» ተብለው ወደ ወህኒ የወረዱበት ሁኔታስ የታለ ?
በአንድ ሜዲያ መቅረብ አንድን ሰው ጥፋተኛ አያሰኘዉም። አንድ ሰው መከሰስ ካለበት፣ ሊከሰስ የሚገባው በቃለ መጠይቆቹ ዉስጥ ባለው ይዘት ነው። አቶ ሃብታሙና አቶ አብርሃ፣ ሲጽፉም ሲናገሩም በግልጽና በአደባባይ እንደመሆኑ «ይሄን ተናገረዋል.. » ተብለው የሚከሰሱበት ነጥብ ይኖራል ብዬ አላስብም። በመሆኑም አገዛዙ ፣ እነዚህ ሰላማዊ ዜጎችን ሽብርተኞች ናቸው ብሎ ማሰሩ የትም አያደርሰውም። ይህ አይነቱ ፍርድ ገምድልነትና ዜጎችን ያለ ከልካይ ማሰርና ማንገላታት መቆም አለበት።

Saturday, August 23, 2014

አገራቸውን ጥለው የተሰደዱት የ 7 ጋዜጠኞች (ፎቶዎች)


 


 



ጋዜጠኛ ግዛው ታዬ

       ጋዜጠኛ ቶማስ አያሌው

የኢህአዴግ መንግስት በጋዜጠኞች ላይ የሚያደርሰውን ጫና ተከትሎ ከሀገር የተሰደዱትን የሎሚ፣ ጃኖ እና አፍሮ ታይምስ ጋዜጠኞችን ፎቶ ከዚህ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል፡፡
1.ጋዜጠኛ ግዛው ታዬ የሎሚ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር
2. ጋዜጠኛ ቶማስ አያሌው የአፍሮ ታይምስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር
3. ጋዜጠኛ ዳንኤል ድርሻ የሎሚ መጽሔት ሚዲያ ዳይሬክተር
4. ጋዜጠኛ ሰናይ አባተ የሎሚ መጽሔት ዋና አዘጋጅ
5. ጋዜጠኛ ሰብለወርቅ መከተ የሎሚ መጽሔት ከፍተኛ ሪፖርተር
6. ጋዜጠኛ አቦነሽ አበራ የሎሚ መጽሔት ከፍተኛ ሪፖርተር
7.ጋዜጠኛ አስናቀ ልባዊ የጃኖ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር

ጄ/ል ባጫ ደበሌ በሜሪላንድ ግዛት የ350ሺህ ዶላር ቤት ገዙ


August22/2012

Gen. Bacha Debele (left), meets Pakistan President Pervez Musharraf.

ጄ/ል ባጫ ደበሌ በአሜሪካ ሜሪላንድ ግዛት በ350ሺህ ዶላር ቤት መግዛታቸው ታውቋል። የባጫ ባለቤትና አንድ ልጃቸው እንደሚኖሩበት ሲታወቅ ልጃቸው በተርም ከ20ሺህ ዶላር በላይ እየተከፈለለት እንደሚማር ማወቅ ተችሏል።

በከፍተኛ ሙስና ውስጥ ከተዘፈቁ የመከላከያ ከፍተኛ የጦር አዛዦች አንዱ የሆኑት ባጫ ደበሌ በቦሌ ከለንደን ካፌ ፊት ለፊት ባለሁለት ፎቅ ዘመናዊ ቪላ ገንብተው እንደሚያከራዩ ይታወቃል። በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ወቅት አሰብን ለመቆጣጠር ይገሰግስ የነበረውን የኢትዮጵያ ሰራዊት ከመለስ ዜናዊ በተላለፈ ትእዛዝ ግስጋሴው እንዲገታና ወታደራዊ እቅዱ እንዲኮላሽ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት ባጫ ደበሌ መሆናቸውን የቅርብ ምንጮች ያረጋግጣሉ።

ባጫ የአቶ መለስን “ሃሳብ” ተግባራዊ በማድረጋቸው በሙስና ሃብት ጥግ መድረስ ችለዋል ሲሉ ምንጮቹ ያክላሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ተስፋዬ ገ/አብ በዲሲ የሃበሻ ሬስቶራንት ውስጥ ሲገባ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሬስቶራንቱን ለቀው እንደወጡ ታውቋል። « አንተ ባለህበት መመገብም ሆነ አብረን መቀመጥ አንፈልግም» ሲሉ ነበር የወጡት። ኢትዮጵያውያን ወንድማማቾችን ለማጋጨት ከሻዕቢያ የተቀበለውን መሰሪ አጅንዳ ይዞ የሚንቀሳቀሰው ተስፋዬ ገ/አብ ያሳተመውን መፅሐፍ ተረክበው እንዲሸጡለት የጠየቃቸው የሃበሻ መደብሮች በሙሉ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። « ኦሮሞ ነኝ» በማለት እያደነገረ የሚገኘው ተስፋዬ ለሻዕቢያው መፅሄት በሰጠው ቃለምልልስ « ኤርትራዊ ነኝ፤ ወላጆቼም ኤርትራውያን ናቸው» ሲል ተናግሮዋል።