Tuesday, June 10, 2014

በምርጫ 97 በግፍ ለተገደሉ ወገኖቻችን መታሰቢያ በኦስሎ ከተማ የሻማ ማብራት ስነስርአት ተካሄደ


በምርጫ 97 በወያኔ አጋዚ ጦር በግፍ ለተገደሉ ዜጎቻችንን ለማስታወስ   በጁን 8, 2014 በኦስሎ ከተማ የሻማ ማብራት ስነስርአት ተደረገ ። የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌ ይህንን የሻማ ማብራት ያዘጋጀበት ዋናው አላማ በምርጫ 97 የዲሞክራሲ ጥያቄ ባነሱና ድምፃችን ተሰርቋል ድምፃችንን መልሱልን ያሉ ንጹሀን ዜጎቻችን የተገደሉበት እለት በመሆኑ ለሞቱት ወገኖቻችን መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ነው።


ዝግጅቱ በግፍ በወያኔ ታጣቂዎች ደረትና ግንባራቸውን ተብለው የተገደሉ ንፁሃን ወገኖቻችን በማስብ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ የተጀመረ ሲሆን በመቀጠልም የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌ ምክትል ሊቀመንበር ምርጫ 97ትን አስመልክቶ ሰፋ ያለ የመግቢያ ንግግር አድርገዋል እደዚሁም የኢትዮጵያ ማህበር በኖርዌ ሊቀመንበርም አጠር ያለ መልክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን የተለያዩ ተጋባዥ እንግዶችም በምርጫ 97 ወቅት የነበረውን የግፍ ግድያ አስመልክቶ በየተራ መልክቶቻቸውን አስተላልፈዋል። በተጨማሪም ድርጅቱ በምርጫ 97 በግፍ ህይወታቸውን ያጡ ወገኖቻችንን ለማስታወስ አጭር በፊልም የተደገፈ ምስል በስነስርአቱ ላይ ቀርቧል። በዝግጅቱ ላይ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ አባላትና ሌሎችም ኢትዮጵያዊያን ተገኝተዋል። ዝግጅቱ በኖርዌጅያን የሰአት አቆጣጠር ከምሽቱ 19፡00 ተጀምሮ 20፡30 ተጠናቋል።


ምርጫ 97ትን ሁላችንም ስናስታውስ ገዢው ፓርቲ እድሜያቸው ትንንሽ የሆኑ ልጆችን በአልሞ ተኳሾች  ግንባርና ደረታቸው ብሎ ካስገደለ በኋላ የሰጠን ምላሽ ዘራፊዎች ናቸው ባንክ ለመዝረፍ ሲሞክሩ ተገደሉ ይለናል የሞቱት ህፃናት እንኳን ባንክ የመዝረፍ እውቀትና አቅም ሊኖራቸው ቀርቶ ስለባንክ ቢጠየቁ ብዙም እውቀቱ የሌላቸው ህፃናት ነበሩ። ወያኔ እስከአሁንም ድረስ ንፁሃን ዜጎቻችንን በግፍ ከገደሉት ሎሌዎቹ አንዳቸውንም ለፍርድ ለማቅረብ ምንም አይነት ሙከራ አለማድረጉ ይታወቃል። ሐገራችን የወያኔ አድርባይ ግፈኞችና ወንጀለኞች የማይጠየቁባት እንደፈለጉ ወንጀል የሚሰሩባት በአንፃሩ ምንም ወንጀል ያልሰሩ ለሃገራችን ያገባናል የሚሉ ዜጎች ያለምንም ማስረጃ በተዛባ የፍርድ ሂደት በእስር የሚማቅቁባት የወንበዴዎች ሐገር ሆናለች። እነኚህን በምርጫ 97 የተገደሉ ወገኖቻችንን ሁሌም እንዘክራቸዋለን እናስታውሳቸዋለን ሆኖም ግን ሁሌ በየአመቱ ሻማ በማብራት ብቻ ሳይሆን ገዳዮቻቸውን ለፍርድ ለማቅረብም መስራት አለብን። በአጠቃላይ በሃገራችን የህግ የበላይነት እንዲኖርና ሁሉም ሰው በሃገሩ ያለምንም የዘር መድልኦ በነፃነት የሚንቀሳቀስበት ስርአት ለመፍጠር ይህ ስርአት መወገድ ስላለበት በዚህ ላይ ትኩረት አድርገን መታገል ይኖርብናል። ምክንያቱም ወያኔ በ97 ገደለ አሁንም እየገደለ ነው ዜጎች በየቀኑ ዛሬም እየሞቱ ነው ይህንን ሞት የምናቆመው ወያኔን ስናስወግድ ብቻ በመሆኑ ሁላችንም በመተባበር ሐገራችንን እንድናድን ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።

ኢትዮጵያ  በክብር ለዘላለም ትኑር  
ሄለን ንጉሴ

No comments:

Post a Comment