ሟቹ የወያኔ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ የዛሬ ስምንት አመት ገደማ ይመስለኛል በራሳቸው አንደበት ጋዜጠኛም ሳያስፈልጋቸው በቴሌቪዢን መስኮት ብቅ ብለው ማንም ሰው ከዛሬ ጀምሮ ሰላማዊ ሰልፍም ሆነ ስብሰባ ማድረግ የማይችል መሆኑን አስረግጠው በማስፈራሪያ መልክ የተናገሩት፡፡
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ለረዥም ጊዜ /ላለፉት ስምንት/ ዓመታት ሰላማዊ ሰልፎች በሃገራችን ላይ ሳይደረጉ የህዝባችንም ድምፅ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትእዛዝ ታፍኖ ቆይትዋል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ህገመንግስታዊ መብቱን በመጠቀም በዛሬው እለት የጠራው ሰልፍ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ በሰለማዊ መንገድ የተለያዩ መፈክሮችን በማሰማት እንዲሁም ያለ አግባብ የታሰሩ የፖለቲካ የሀይማኖት እና የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ፤ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎች በአግባቡ እንዲመለሱ እና አፈናቃዮች ለፍርድ እንዲቀርቡ፤ የኑሮ ውድነቱ አስተማማኝ እልባት እንዲሰጠው እና ሌሎችንም በርካታ ጥያቄዎች ያቀረቡ ሲሆን፤
መንግስት እነኚህን የህዝብ ጥያቄዎች በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ካልመለሰ ድምፃቸውን በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚያሰሙ የፓርቲው አመራር ገልፀዋል፡፡
ሰልፉ ከጠዋቱ አራት ሰዓት ጀምሮ እስከ ስምንት ሰዓት ድረስ እጅግ ደማቅ በሆነ መልኩ የተከናወነ ሲሆን ቀበና ከሚገኘው ሰማያዊ ፓርቲ ፅ/ቤት አንስቶ በአራት ኪሎ በፒያሳ እና በቸርቸር ጎዳና ሄዶ መድረሻውን ኩባ አደባባይ ያደረገው ሰልፍ ባልተጠበቀ የህዝብ ቁጥር ብዛት በኢትዮጵያዊ ጨዋነት በሰላም ተጠናቋል፡፡

እንግዲህ ወያኔዎች ከዚህ የሰላማዊ ሰልፍ ብዙ ልትማሩ የሚግባችሁ ይመስለኛል ህዝቡ ምን ያህል ድምፁ ታፍኖ እንደነ በረና እንደተማረረ ብሶቱን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ መግለጽ እንደሚፈልግ እንዲሁም በሃገራችን ውስጥ የስርአት ለውጥ እንደሚያስፈልገን መገንዘብ ይኖርባችኌል፡፡ በመሆኑም በጠመንጃ አፈሙዝ፤ በዘር በሃይማኖት ከፋፍሎ የአንድ የብሄር የበላይነትን አጉልቶ ሌላውን ብሄር በማሳነስ ሃገር መግዛት አይቻልምና ሃገራችን የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት የሚከበርባትና ሁሉም ዜጋ በሃገሩ ሳይሸማቀቅ አንገቱን ቀና አድርጎ የሚኖርባት አንዲት ኢትዮጵያ እንድትኖረን እንፈልጋለንና ሃገራችንን ብትለቁልን በሚል የግል አስተያየቴን በመስጠት ሰማያዊ ፓርቲዎችን በርቱ ተበራቱ እኛም ከጎናችሁ ነን ለማለት እወዳለሁ፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር
ሄለን ንጉሴ
No comments:
Post a Comment