Wednesday, April 30, 2014

ሴቶችን አብዝቶ የሚፈራው መንግሥት

April 29, 2014

ቹቸቤ
Jailed Ethiopian female bloggers, activists and journalists
መነሻቸው ግልብ ጎጠኛነት መድረሻቸው መንደረተኛነት በመሆኑ በዘረፋ እየከበሩ በመለስ ራዕይ እያጨናበሩ ከመኖር ያለፈ ከእውነት ጋር ፊት ለፊት ተያይተው መኖር ያልቻሉት የትግራይ ጉጅሌዎች በወጣቶች ላይ የሚፈጽሙት ሰቆቃ አሳፋሪ ነው። በህጻናትና በሴቶች ላይ የሚበረቱ የማስተዋል ድርቅ የመታቸው፣ የእውቀት ረሀብ ያደነዛቸው ፍርሃት እንቅልፍ የነሳቸው ናቸውና ድፍረት ያላቸው ህጻናት ያስፈሯቸዋል እውነት የያዙ ሴቶች ያስደነግጧቸዋል። ለዚህ ነው የወጣቶችን ግንባር በምንደኛ ጦር ሲነድሉ ወጣት ሴቶችን ሲደፍሩ ሲያስደፍሩና ሲያዋርዱ ደስታን የሚያገኙት።


አብዛኞቹ በዚህ ጎጠኛ ቡድን የሚንገላቱት ወጣቶች ወያኔ በገባበት ዘመን የተወለዱ ወይም ገና ድክድክ የሚሉ ህጻናት ነበሩ። ሲነገራቸው የኖረውና ህይወታቸውን ሙሉ የተመለከቱት ኢትዮጵያ ስትዋረድ የሀገሪቱ ጀግኖች ሲሰደቡና ዘር በዘር ላይ ሀይማኖት በሀይማኖት ላይ የሚያነሳሳ ታሪክ ሲማሩ ነበር ያደጉት። ሬድዮ፣ ቴሌቭዥን ጋዜጣና መጽሄቱ ሁሉ የሰሩት የወያኔን ፕሮፓጋንዳ ነበር። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያዊነት ከቀን ወደ ቀን ይበልጥ እየገነነ፣ ለነፃነት የሚደረገው ትግል እየጠነከረ መምጣቱ ይልቁንም አፍራሹ ፕሮፓጋንዳና ድርጊት ጠንካራ ወጣት ወንዶችና ወይዛዝርቶችን ቁርጠኛ ታጋይ እንዲሆኑ አደረገ እንጂ ኢትዮጵያዊነት ሲሞት አላየንም።
ከዚህ መማርና መለወጥ የሚቻል ቢሆንም ኢትዮጵያዊነትን ያሟጠጠ አእምሮው በጥላቻ የሰከረን መመለስ እንደማይቻል መመልከት አሳዛኝ ነው። “የሚያድግ ልጅ አይጥላህ” የሚባለው ተረት የሚያስተምር ቢሆን በወጣቶች ላይ የሚሰራውን ግፍ ቀነስ ማድረግ በተቻለ ነበር። እኒህ ወጣቶች ይቅር ባይ እንጂ ቂመኛ እንዳይሆኑ ግን ምኞቴ ነው።
እነዚህ ክፉዎች በየቀኑ የሚተክሉት የጥላቻ ችግኝና የእልቂት ድግስ የመቶ አመቱን በደል አስታውሶ ከሚያጫርሰው በላይ ዛሬ የሚደርሰውን ግፍና በደል አጉልቶ የሚያሳይ በመሆኑ የታች አምናውን ሳይሆን የትናንቱን የወያኔን ሕዝብ ከመኖርያ ማፈናቀል፣ ገበሬዎችን መበተን፣ የሀገር ድንበር መቁረስን፣ በአማራና ኦሮሞ ላይ እየተኪያሄደ ያለውን የዘር ማጥፋት እያስታወሰ የሕዝብ ሃይል መልሶ ጠራርጎ እንደሚያጠፋቸው አለማወቅ የግብዝነትና የድንቁርና ምልክቱ ነው። በዘመነ ደርግና በንጉሳውያኑ ዘመን ከሆነው ሁሉ የበለጠ ግፍና በደል የተፈጸመው በነዚህ ጎጠኞችና የሀገር ጠላቶች እንደሆነ ለመናገር እዚያው ትግራይ ያለውን ተቃውሞ ምሳሌ ማድረግ ይበቃል። ጎጠኞቹ ልብ ያላሉት የታቀፉት የእባብ እንቁላል እነሱኑ ቀድሞ እንደሚነድፍ ነው። ይህ እንደሚሆን ለማወቅ በሀገሪቱ ከተበተኑት ሰላዮች መስማት የሚፈልጉትን ብቻ ሳይሆን እውነት እንዲናገሩ ብቻ ቢፈቅዱላቸው እንኳ ያንዣበባቸውን አደጋ ባወቁት ነበር።
ርዕዮት አለሙ ጽንፈኛና አሸባሪ ልትባል የምትችልበት ምንም መረጃ የለም። ወያኔዎችን ያስፈራው እውነትን መያዝዋና ድፈረቷ ብቻ ነው። ርዕዮትን ማሸማቀቅ ሌሎችን ለማስፈራራት የተወሰደ እርምጃ ነበር ግን ውጤቱ በተቃራኒው ሆነ። እናም አነሆ ወይዛዝርቶቹ ተነሱ! ስለወያኔ ክፋት ሳይሆን ስለሕዝባችን ብርታትና መነሳሳት የምናወጋውም በኩራት የሚሆነው ለዚህ ነው።
ሴቶች ትግሉን አልተቀላቀሉም፣ ብዙዎቹ ወደሁዋላ ይላሉ እንላለን ጥቂት ግን በጣም ጥቂቶቹ ደፍረው ሲወጡ ከጎናቸው ልንቆምና በየአቅጣጫው ልንታገልላቸው ይገባል። ርዕዮት እድሜዋ ገና ሰላሳዎቹ ውስጥ ያለች ወጣት ትዳር ያልመሰረተችና ልጅ የሌላት ብዕረኛ ናት። ትዳሩ ይቅር ልጅም አይኑራት ነገር ግን ለህይወትዋ አስጊ በሆነ የጤና ችግር ላይ መሆንዋ እየታወቀ ህክምና እንዳታገኝ ማድረጉ አሰቃይቶ የመግደል እኩሌታ ነው። ይህ የግፍ ጽዋ ሞልቷል። ወጣቱ ቆርጦ ተነስቷል።
ምስላቸው ከዚህ ጽሁፍ ጋር የሚታየው ወጣቶች የእስርቤት ሰለባ ይሆናሉ ብሎ ማሰብ በጣም ያሳዝናል። ይሁን እንጂ ሁላቸንንም የሚያበረታቱ የጣይቱ የዘር ግንድ የጀግኖች የዜግነት ውርስ በዚህ ትውልድ ደም ውስጥ መፍሰሱን ስለሚያመለክቱ ተስፋ ይሰጡናል ብርታትም ይሆኑናል። እኒህ ወጣቶች ከታሰረው ከሰፊው ሕዝብ ጋር ተቀላቅለው ለነጻነት ለሚደረገው ትግል አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ተባብረን እንነሳ! ከትንሹ እስር ቤት ወደ ትልቁ ይመጡ ዘንድ ድምጻችንን እናሰማ። አብረንም ሆነን የተነጠቁ መብቶቻችንን እናስመልስ። ኢትዮጵያችንንም ነፃ እናውጣ!
ኦህ ኢትዮጵያ ባንቺ ተሰፋ አይቆረጥም… ልጆችሽ የነጻነት ዐየርን ይተነፍሱ ዘንድ በጀግንነት እንታገላለን… ሁሌም የመከራ ገፈት የሚቀምሱትና የበደል ጫና አንገት ያስደፋቸው የሀገራችን ሴቶች በሀገራቸው ኮርተው አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሄዱ የድርሻችንን ሁሉ እናበርክታለን።
ምንጭ፦ ኢካዲፍ

Tuesday, April 29, 2014

በዞን ዘጠኝ ጦማርያን እና በጋዜጠኞች ላይ የተወሰደው የእስር እርምጃ እንዳሣሰበው ሲ.ፒ.ጄ ገለጸ።

ዓለማቀፉ የጋሴጠኞች ተንከባካቢ ድርጅት(ሲፒጄ)  ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት ሰሞኑን በ9 ጸሀፍያን ላይ የወሰደው የእስር እርምጃ፤ ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ላይ ከተቃጡ የከፉ እርምጃዎች አንዱ ነው ብሏል።
“የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በሰላማዊ መንገድ ሀሳብን መግለጽን እንደወንጀል እየቆጠሩት ነው” በማለት ነው -የሲፒጄ የምስራቅ አፍሪቃ ወኪል-ቶም ሩድስ-እርምጃውን የኮነኑት።
እሁድ ዕለት የመንግስት አቃቤ ህግ በ አዲስ ጉዳይ ዋና አዘጋጅ በ አስማማው ሀይለጊዮርጊስ፣ በፍሪላንስ ጋዜጠኞቹ በተስፋለም ወልደየስ እና በ ኤዶም ካሣዬ፣ እንዲሁም በጦማርያኑ በ አቤል ዋቤላ፣በ አጥናፍ ብርሀኔ፣በማህሌት ፋንታሁን፣ በዘላለም ክብረት እና በበፈቃዱ ሀይሉ ላይ  ከውጪ ድርጅቶች ጋር ይሠራሉ፣ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀምም በሀገሪቱ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ይንቀሳቀሳሉ.. የሚል ክስ እንደመሰረተባቸው ሲፒጄ አውስቷል።
ተስፋለም፣አስማማውና ዘላለም ለፊታችን ሚያዚያ 28 ቀሪዎቹ ደግሞ ለሚያዚያ 29 እንደተቀጠሩ ከሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች የደረሰውን መረጃ ዋቢ አድርጎ የጠቀሰው ሲፒጄ፤ በታሳሪዎቹ ላይ እስካሁን መደበኛ ክስ እንዳልተመሰረተ ጠቁሟል።
ሲፒጄ በመግለጫው-ፀሀፊዎቹ ዞን ዘጠኝ ተብሎ የሚጠራ የገለልተኛ አክቲቪስቶች ስብስብ አባል ሆነው የተለያዩ ዜናዎችንና ጽሑፎችን ይጽፉ እንደነበር  አመልክቷል።
“ዞን ሰጠኝ የተሰኘው ስያሜ ከቃሊቲ የተገኘ  መሆኑና  የጸሐፊዎቹ  መሪ ቃል፦”ስለሚያገባን እንጦምራለን” የሚል  መሆኑ በሲፒጄ መግለጫ ተመልክቷል።
ጦማርያኑና ጋዜጠኞቹ የታሰሩት ከደህንነቶች በሚደርስባቸው ወከባ ምክንያት ላለፉት ሰባት ወራት ዘግተውት የቆዩትን የፌስቡክ ገፃቸውን ዳግም በከፈቱ ማግስት መሆኑን እንደተረዳም የጋዜጠኞች መብት ተንከባካቢ ተቋሙ ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ አማካሪ የሆኑት ጌታቸው ረዳ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ፦”የታሰሩት ጋዜጠኞች አይደሉም፤ እስሩ ከጋዜጠኝነት ሥራቸው ጋር የተገናኘ አይደለም። ከከባድ ወንጀል ጋር የተገናኘ ነው” ማለታቸውን ሲ.ፒ.ጄ ጠቁሟል።
“በጋዜጠኝነት ወይም ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ላይ የቃጣነው በትር የለም። ሆኖም ማንም ቢሆን ሙያውን ሽፋን በማድረግ ወንጀል ለመፈፀም ሲሞክር በህግ ይጠየቃል” ሲሉም አክለዋል-አቶ ጌታቸው ረዳ።
“የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ወደለየለት ፈላጪ ቆራጭ አገዛዝ  ማዘንበላቸውን እንዲገቱና በሀገሪቱ  ነፃ ሀሳቦች ይንሸራሸሩ ዘንድ እንዲፈቅዱ ጥሪ እናቀርባለን” ብለዋል-ሚስተር ቶም ሩድስ።
የታሰሩት 9ኙም ጸሀፊዎች በአስቸኳይ ሊፈቱ ይገባል ሲሉም ጠይቀዋል። ዓለማቀፉ የሰብዓዊ መብት ተቋም ሂውማን ራይትስ ዎችና ሌሎች ድርጅቶችም የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በጦማርያኑ እና በጋዜጠኞቹ ላይ የወሰዱትን እርምጃ በማውገዝ ፤ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ዛሬ አዲስ አበባ የሚገቡት የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ  እስረኞቹን እንዲፈታ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ግፊት እንዲያደርጉ ጠይቋል።
የተለያዩ ዓለማቀፍ የሚዲያ ተቋማትም ሰሞኑን የኢትዮጵያ መንግስት በ9ኝ ጦማርያን እና ጋዜጠኞች ላይ የወሰደውን የማሰር እርምጃ ሽፋን ሰጥተውታል።
ከሚዲያ ተቋማቱ መካከል ኤ.ቢ.ሲ ኒውስ፣ ሲ ኤን.ኤን፣ ዋሽንግተን ፖስት፣ ሬውተርስ፣ እና አልጀዚራ ይገኙበታል።
እንዲሁም የዩናይትድ ስቴትስ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ በጉብኝታቸው ስለታሰሩት ጦማርያን እና ጋዜጠኞች አጠንክረው እንደተናገሩ  የኒውዮርክ ታይምሱ ታዋቂ አምደኛ  ኒኮላስ ክሪስቶች ለሰጣቸው አስተያዬት፤ “ በጣም  ጠቃሚ ጉዳይ ነው። ዩናይትድስቴትስ  በመላው ዓለም ላይ የፕሬስ ነፃነትን በመደገፍና ከጥቃት በመከላከል ባላት ጠንካራ አቋም ትቆያለች” በማለት ምላሽ ሰጥተውታል።
ምንጭ፦ ኢሳት

Saturday, April 26, 2014

Nine Bloggers and journalist Tesfalem Woldey arrested in Addis Ababa /Meakelawi/


Zone9 has confirmed that Six Zone9 bloggers and journalist Tesfalem Woldeyes are in Addis Ababa central investigation center (meakelawi) since their arrest last night. during the arrest their house was searched and police took laptops, Newspapers and books from their home. Families were not allowed to meet them.We believe members and friends of Zone Nine have nothing to do with any illegal activities and we again request the government to release them immediately.

#FreeZone9bloggers #FreeTesfalem #Ethiopia

1. TESFALEM WELDEYES @tesfalemw.
Journalist, Former addis neger ,
Founder of Habeshawi Kana.Worked @ A.Standard & A Fortune.
Arrested Apr25
2. BEFEKADUHAILU @befeqe
was a MIS Expert at St. Mary's U/College.
Blogger & Activist @ #Zone9.
Arrested Apr25. 3
3. . NATNAIL FELEKE @EthioLiberty
HR Mgmt Officer at C and B Bank S.C.
Blogger & Activist @ #Zone9.
Arrested Apr25.
4. . MAHLET FANTAHUN @faantish a Data Officer at PMU.
Blogger & Activist @ #Zone9.
Arrested Apr25
5. . ATNAF BERHANE @Atnaf1
an IT and Services professional.
Blogger & Activist @ #Zone9.
Arrested Apr25.
6. . ZELALEM KIBRET, @zelalemkibret
Studied Law.
Lecturer at Ambo Unv..
Blogger & Activist @ #Zone9. Arrested on Apr25.
7. . ABEL WABELLA @abelpoly,
a Tooling Engineer at Ethiopian Airlines.
Blogger & Activist @ #Zone9
Arrested Apr25


Friday, April 25, 2014

የሚታደስ ቃል ኪዳን


አጼ ዮሃንስ (1837-1889)
(ጸጋዬ ገብረ መድኅን አርአያ)
“መኳንንቶቼ፣ ልጆቼና ሕዝቦቼ ሆይ! እኔ ስለ እናቴ ኢትዮጵያ ሕይወቴን ልሰዋላት ሙሉ ፈቃድ አለኝ። በእኔ ልብ ያለው አሳብ በትክክል በእናንተም ልብ በመታሰቡ በጣም ደስ ብሎኛል። እንግዲህ አሳባችን አንድ ከሆነ ጠንክሩ እንጂ አትፍሩ። ለዘመቻውም አዋጅ አናግራለሁና አይዞአችሁ አትፍሩ! አገሬ ሆይ ስሚ! መኳንንቶቼ፣ ወታደሮቼ፣ ሕዝቦቼ ስሙ…..ወደፊት ገስግሱ እንጂ ወደኋላ አትቅሩ! የኢትዮጵያ ልጅ ሆይ! ልብ አድርገህ ተመልከት ኢትዮጵያ የተባለችው አንደኛ እናትህ ናት! ሁለተኛ ዘውድህ ናት! ሦስተኛ ሚስትህ ናት! አራተኛ ልጅህ ናት! አምስተኛ መቃብርህ ናት! እንግዲህ የእናት ፍቅር፣ የዘውድ ክብር፣ የሚስት ደግነት፣ የልጅ ደስታ፣
የመቃብር ከባቲነት እንደዚህ መሆኑን አውቀኸው ተነሳ!”



- አንበሳው አጼ ዮሐንስ- ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ

ለእናታቸው፣ ለሚስታቸው፣ ለልጃቸው፣ ለዘውዳቸውና ለመቃብራቸው የተሰውትና በሕይወት ዘመናቸው “አንበሳው አጤ ዮሐንስ” እየተባሉ ይጠሩ የነበሩት ሰማዕት ከሞቱ 125 ዓመት ሆናቸው። አንድ አሜሪካዊ ታጋይ በ1775 በአንድ የፊላደልፊያ ፍርድ ቤት ቀርቦ የታላቁን የእንግሊዝ መንግሥት አመራር በመቃወም በፈፀመው ወንጀል እንዲሰቀል ሲፈረድበት የተናገረው ተጠቃሽ ቃል ነበር። “አዝናለሁ እግዚአብሔር አንድ ነፍስ ብቻ ስለሰጠኝ” ነበር ያለው። አጤ ዮሐንስን በዚያ ታሪካዊ ብጽአት የምለካቸው፣ በዚያው ራሳቸው በመደቡት የወርቅ ሚዛን የምመዝናቸውና ለኢትዮጵያ ተከታታይ ትውልዶች ሁሉ ዘላለማዊ ብሔራዊ ቃል ኪዳን ቀርጸው ያለፉ ታላቅ መሪ ስለሆኑ ነው። በዚህ መስፈርት የኖሩም ናቸው። ደርቡሽ ጀግናውን መሪ ገድያለሁ፣ አንገቱንም ቆርጨ ወስጄ ተጫውቸበታለሁ ሊል ይችላል። ዮሐንስ ተገድሎ የኢትዮጵያ መሬት በደርቡሽ ተወስዶ ቢሆን ቁጭቱ ባነደደን ነበር። እስከማዕዜኑ። ቢያንስ 125 ዓመት የዚያ አካባቢ ኢትዮጵያዊ መሬትነት ተጠብቆ ቆይቶአል። ደርቡሽ የደፈረንስ አሁን ነው። አገር ሲያረጅ እሾህና አሜከላ ያበቅላልና! አጤ ዮሐንስ - ራሳቸው ባሰፈሩት መዳልው መሠረት ለእናታቸው፣ ለሚስታቸው፣ ለልጃቸው፣ ለዘውዳቸውና ለመቃብራቸው ሕይወታቸውን “ለመሰዋት ሙሉ ፈቃድ አለኝ” እንዳሉት ጽዋውን ተጐንጭተው አለፉ። ልቅሶ መቀመጥ የሚገባቸው “እናታቸው፣ ልጃቸው፣ ሚስታቸው፣ ዘውዳቸውና መቃብራቸው” ደግሞ እንደ ዘመኑ ባህል ቅቤ መቀባት የነበረባቸው ይመስለኛል። በደስታ የሚሞትላቸው መሪ መታደል እንደ ቀላል ነገር የሚታይ አይደለማ። እኔስ በእኔው ደረጃና አጋጣሚውን አውቀዋለሁ። ከጉራና ከአጉል መንጠራራት ጋር ካላያችሁብኝ።

አንድ ጊዜ በጦቢያ ላይ በወጣ ጽሑፍ ምክንያት ከከፍተኛው ፍርድ ቤት እመላለስ ነበር። እንዳጋጣሚ ታላቅ እህቴ ማን እንደነገራት ሳላውቅ በመጨረሻው የፍርድ ዕለት ችሎቱ ሲከፈት ከሕዝቡ መሐል ጉብ ብላለች። እህቴን ሳያት “አርፈህ ብትቀመጥስ? አንተ ታማሚ ነህና ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርገህ ተቀመጥ- እኛንም በስጋት ጨረስኸን” ብላ ትጨቀጭቀኛለች ብዬ ጥርሶቼን ሳፉዋጭ ቆየሁ። ወዲያው ተጠራሁና ፍርደ ገምድሉን የእነ ሽመልስ ከማል ውሳኔ ተቀብዬ የተጣለብኝን አሥር ሺህ ብር መቀጮ ጓደኞቼ ከፍለው ወጣሁ። ከመኪናችን ውስጥ ሁለቱ የጦቢያ አርበኞች ደርበውና ጐሹ ነበሩ። እህቴ ዘርትሁን ከእኛው ጋር ትዳበላለች። አሁን ካሁን ጭቅጭቅዋን ትጀምራለች ስል “በሉ ከሰዓት በኋላ ሁለት ላሞች ሸጨ አሥሩን ሺ ብር እሰጣችኋለሁ። በእኔ በኩል ዛሬ የፌስታዬ ቀን ነው። የጀግና እህት ሆኛለሁ። እግዚአብሔር እኔን ጀግና አድርጐ አልፈጠረኝም። ወንድሜ ከወያኔ ጋር ተቋቁሞ…እንዲህ ሲያስከብረኝ ምነዋ አልደሰት! ሁላችንም በዕድሜና በበሽታ ተቀፍድደን ነው እንጂ ኑሮአችን በዱር በሆነ ነበር። አዎን እንደ ደሀ ጨርቅ በመርፌ እየተጠቀጠቅን.. ሽባ ሆነን ጠበቅናቸው” ስትል ሆደ ቡቡ ነኝና እንባዬን ስለቅቀው ሁለቱ ጓደኞቼ ለብዙ ጊዜ የእህቴን ንግግር የመጽናናት መልእክትና የሕዝባችንን ባሮሜትር መለኪያ ያደረጉት ይመስለኛል።( ዛሬ እህቴ ከዘመናት ክስለት በኋላ አርፋለች)

ጌቶቼና እመቤቶቼ፣ ወንድሞቼና እህቶቼ- ልጆቼም! አንድ ውለታ ዋሉልኝ። የአጤ ዮሐንስን አዋጅና ኢትዮጵያን በምን እንደመሰሉአት መላልሳችሁ አንብቡልኝ። መለስ ዜናዊና እሱን ለመሆን የሚፈልጉ ፍጡራን ለመሆኑ ይህን መሆን ሳይሆን ለማንበብ እንኳ እንደሚደነግጡ አይሰማችሁም? ኢትዮጵያ እናት፣ ልጅ፣ ሚስት፣ ዘውድ፣ መቃብር..ሁሉንም ናት። አጤ ዮሐንስን ሠራዊታቸው- የጦር አበጋዞቻቸውና ጭፍራው በሙሉ ያደነቃቸው ፊት ለፊት ፈረሳቸውን እየጋለቡና እንደ አንበሳ እየተጐማለሉ የሚመሩ ጀግና በመሆናቸው ነው። በአዋጁ ላይ እንደተመለከተው ሠራዊታቸውን በማሳሳት መልክ እንኳ ከኋላ አልተከተሉም። በመሐል ሆነው አልተደበቁም። ምሽግ አሠርተው፣ እርድ አስቆፍረው ከዚያ መምራትን አልፈለጉም። እንደ ንጉሥ ዳዊትና እንደ ትልቁ እስክንድር - እንደ አቲላና እንደ ጄንጂስካን

Tuesday, April 15, 2014

በኖርዌ ኦስሎ ከተማ የግንቦት 7 አመራር አባል አቶ ብዙነህ ፅጌ በተገኙበት ታላቅ ህዝባዊ ውይይት ተካሄደ

በሁለገብ ትግላችን ወያኔን እናስወግዳለን በሚል መሪ ቃል የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌ በአፕሪል 12, 2014 በወቅታዊ የሐገራችን ሁኔታ ላይ ታላቅ ህዝባዊ ውይይት አዘጋጀ። በዝግጅቱ ላይ ተጋባዥ እንግዳ የነበሩት የግንቦት 7 የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አመራር አባል አቶ ብዙነህ ፅጌ ነበሩ። 

የኦስሎ ነዋሪዎች እና ከኖርዌ የተለያዩ ከተሞች የመጡ በርካታ ታዳሚዎች በዝግጅቱ ላይ የተገኙ ሲሆን በኖርዌጂያን የሰአት አቆጣጠር ከቀኑ 15፡00 የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌ የህዝብ ግንኝነት ሃላፊው በወያኔ ስርአት ለተጎዱ ወገኖቻችን እንዲሁም በየእስር ቤቱ ያለወንጀላቸው ለሚሰቃዩና ህይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን በሙሉ መታሰቢያ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት እንዲያደርግ ታዳሚውን ጋብዘው ፕሮግራሙን አስጀምረዋል። በመቀጠል የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌ ዋና ሊቀመንበር የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌ በተመለከተ አመሰራረቱን እና የቆመለትን አላማ እንዲሁም የትኛውን የፖለቲካ ድርጅት እንደሚደግፍ እንዲሁም ድርጅቶቹን ለምን እንደሚደግፍ እንዲሁም የድርጅቱን አላማ በማስመልከት ለታዳሚው ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ተጋባዥ እንግዳው አቶ ብዙነት ፅጌ በተራቸው ስለ ኢትዮጵያ ያለፉት መንግሰታት ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ የደርግን መንግስት እና አሁን እስከደረስንበት የአፈና አገዛዝ ድረስ ያለውን የኢትዮጵያ መንግስታቶች ታሪክ በዝርዝር ለታዳሚው በሚገባ መልኩ አስረድተው በተለይ አሁን ያለውን የአምባገነን ስርአት ከድሮው መንግስታቶች ጋር በማነፃፀር ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ አስረድተዋል። ማብራሪያቸውን ከጨረሱ በኋላ የተለያዩ ታዳሚዎች በተለያዩ የሃገራችን ጉዳዮች እና ግንቦት 7 ትን አስመልክቶ ላቀረቡላቸው ጥያቄች በቂ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በዝግቱ ላይ የተለያዩ አዝናኝ ባህላዊ ውዝዋዜዎች እንዲሁም ምግብና መጠጥ የተዘጋጀ ሲሆን የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ም/ክትል ሊ/መንበር ሰፋ ያለ ቀስቃሽ የአቋም መግለጫ በመስጠት የማጠቃለያ ንግግር አድርገው ዝግጅቱ ከምሽቱ በ21፡00 በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል።

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር
ሄለን ንጉሴ/ኖርዌ

Friday, April 11, 2014

በኖርዌ የሚገኙ የወያኔ ሰላዮችን በመቃወም ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ በኦስሎ ከተማ ተካሄደ


ማርች 11, 2014 በኖርዌ የሚገኘው የኢትዮጵያን የስደተኞች ማህበር ያዘጋጀው ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ከተለያዩ የኖርዌ ከተሞች በመጡ ታዳሚዎች እና በኦስሎ ነዋሪ በሆኑ ኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያ ባንዲራ እንዲሁም በተለያዮ መፈክፎች ታጅቦ በተሳካ ሁኔታ ተከናወነ። 

የዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ዋና አላማ በኖርዌ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቀው በሚኖሩበት ሐገር እንደሚሰለሉ እና የወያኔ ሰላዮች በኖርዌይ ምድር መኖራቸውን የኖርዌ የደህንነት ፓሊስ ለሀገሪቱ ትልቅ ጋዜጣ መረጃ መስጠታቸውን እና በተመሳሳይ የሂውማን ራይትስ ዋች በቅርቡ ያወጣውን መረጃ መሰረት በማድረግ የኖርዌ መንግስት ለወያኔ ሰላዬዮች የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያቆም እና አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ ለመጠየቅ እና ኖርዌ በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ ያላትን የአሳይለም ፖሊሲ እንድታስተካክል የሚጠይቅ የተቃውሞ ሰልፍ ነበር።

ፕሮግራሙ ከቀኑ 12፡00 የተጀመረ ሲሆን የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌ ምክትል ሊቀመንበር ሰፋ ያለ የወያኔ ሰላዮችን የተመለከተ ንግግር ያሰሙ ሲሆን የዚሁ ድርጅት የሴቶች ክፍል ተወካይ ወ/ሪት ሔለን ንጉሴ አጠቃላይ በኖርዌ ያሉ ሰላዮችን እና በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ በመስጠት ሴቶች በሁለገብ ትግል ውስጥ ያላቸውን ጉልህ ሚና እንዲሁም ወደፊት ሊኖራቸው የሚገባውን ሚና ጨምረው በማስረዳት ለትግሉ አጋር መሆናቸውን ገልፀዋል። በመቀጠል የስደተኛ ማህበሩ ፀሐፊ ወ/ሪት የሺሃረግ በቀለ ሰፋ ያለ ማብራሪያ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ያቀረበች በመሆኑ የሐገሪቱ ዜጎች መልክቱን በደንብ እንዲሰሙ ያደረገች ሲሆን የኖርዌጅያን ተወላጅ የሆኑትና በስደረኞች ጉዳይ ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች ተወካዮች በተመሳሳይ ስለ ኢትዮጵያ አምባ ገነን መንግስት ከስደተኛው በላይ የሚያውቁትን መረጃ በዝርዝር በየተራ በንግግር አሰምተዋል። ይህንን የሰላማዊ ሰልፍ ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ የመሩልን የስደተኛ ማህበሩ የኮሚቴ አባላት የሆኑት አቶ ዮናስ እና አቶ ጌታቸው ናቸው።

በመጨረሻም ከሰላማዊ ሰልፉ በኋላ በወ/ሮ ሰዋሰው እና በባለቤታቸው የተዘጋጀ የምሳ ግብዣ የተከናወነ ሲሆን የስደተኛ ማህበሩም የውይይት ጊዜ አዘጋጅቶ የነበረ በመሆኑ የስደተኛ ማህበሩን የሶስት ወር ሪፖርት ካቀረበ በኋላ በቀጥታ ወደ ውይይት በመግባት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በኖርዌ ስለሚገኙ የወያኔ ሰላዮች በሰፊው ምክክር አድርገው ወደፊት ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንዴት እነኚህን ሰላዮች በምን መልኩ ማጋለጥ እንዳለባቸው ተወያይተው በመቀጠል አጠቃላይ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ውይይት አድርገው ፕሮግራሙ በተሳካ ሁኔታ ከምሽቱ 19፡00 ተጠናቋል። watch the video



ሄለን ንጉሴ/ኖርዌ

Wednesday, April 9, 2014

በሶማሊ ክልል የኮካ ኮላ ምርት እንዳይገባ ታገደ

የክልሉ የኢሳት ምንጭ እንደገለጸው ካለፉት 2 ሳምንታት ጀምሮ የኮካ ኮላ ምርት ወደ ክልሉ እንዳይገባ በመታገዱ ነዋሪው ህዝብ ከሶማሊላንድ እየታሸገ በኮንትሮባንድ የሚገባውን ኮካ ኮላ ለመጠቀም ተገዷል። ኢትዮጵያ በሚገኘው በኮካ ኮላ ድርጅትና በክልሉ መንግስት መካከል ልዩነት መፈጠሩም ታውቋል።

ቀደም ብሎ በክልሉ የኮካ ምርትን የሚያከፋፍለው የታዋቂዋ ባለሃብት የወ/ሮ ሱራ ድርጅት ሲሆን፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት አብዲ ሙሃመድ ግለሰቡዋ የኦጋዴን ተወላጅ ባለመሆናቸው ለወ/ሮ ሃዋ እንዲሰጥ በመወሰናቸው ነው።
ወ/ሮ ሃዋ  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ ቁጥር አንድ ባለሃብት እየሆነች የመጣች የጄኔራል ዮሃንስ ገብረመስቀል የፍቅር ጓደኛ ናት።
ወ/ሮ ሱራ ከ ወ/ሮ አዜብ መስፍን ጋር በሽርክና በመስራት ጫት ከኢትዮጵያ ወደ ሶማሊላንድ በማመላለስ ከፍተኛ ሃብት አካብታለች። ግለሰቡዋ ሶማሊላንድ ላይ ግንባታዎችን ማካሄዱዋን እንደሰበብ የተጠቀሙበት የክልሉ ፕሬዚዳንት፣ ኮካን የማከፋፈሉን ስራ ከወ/ሮ አዜብ የንግድ ሸሪክ ወደ ጄኔራል ዮሃንስ ገብረመስቀል የፍቅር ጓደኛ አዙረዋል።
መስተዳድሩ የኮካን ምርት ወ/ሮ ሃዋ የማታከፋፍል ከሆነ ኮካ ኮላ በክልሉ መሰራጨት የለበትም የሚል አቋም መያዙን ተከትሎ፣ የኮካ ኮላ መስሪያ ቤት ለሁለቱም ባለሀብቶች መስጠቱን ትቶ ራሱ ማከፋፈል እንደሚጀምር መግለጹ ታውቋል።
በክልሉ መሪ በአቶ አብዲና በወ/ሮ አዜብ መስፍን መካከል የተፈጠረው ልዩነት ወ/ሮ ሱራ የኮካ ኮላ ማከፋፈሉን ስራ እንድትነጠቅ ከማድረጉም በላይ ወደ ሶማሊላንድ ስትልከው የነበረውንም ጫት  ከወ/ሮ ሃዋ ጋር በየሁለት ሳምንቱ ተካፍለው እንዲልኩ በመወሰናቸው ወ/ሮ ሱራን ከጫዋታ ውጭ እያደረጉዋቸው ነው።
ወ/ሮ ሃዋ በጅጅጋ፣ በደገሃቡርና በመቀሌ የተለያዩ ግንባታዎችን እያካሄዱ ነው። ጄ/ል ዮሃንስ በክልሉ ውስጥ በአዛዥነት ይሰሩ በነበረበት ወቅት የተለያዩ የመከላከያ ኮንትራቶችን ለወ/ሮ ሃዋ በመስጠት በአንድ ጊዜ ከኢንቨስተሮች ተራ እንድትገባ አድርገዋታል።
ወ/ሮ ሱራ በበኩላቸው ከጠ/ሚንስትር መለስ ሞት በሁዋላ በክልሉ ያላቸው ተሰሚነት እየቀዘቀዘ በመምጣቱ ትኩረታቸውን ሁሉ ሶማሊላንድ ላይ ለማድረግ ተገደዋል።
በጣም የሚገርመው ይላል ምንጫችን ኮካ ኮላ በህጋዊ መንገድ እንዳይገባ ከተደረገ በሁዋላ በኮንትሮባንድ ከሶማሊላንድ እያስገቡ የሚሸጡት ጅጅጋን የሚያስተዳድሩት የህወሀት የመከላከያ አዛዦች ናቸው። እነዚህ አዛዦች ያለምንም ከልካይ ኮካ ኮላ በማምጣትና በማራገፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ገንዘብ እያጋበሱ ነው።
ጄ/ል ዮሃንስ ጄ/ል ሳሞራ የኑስን ይተካሉ ተብሎ ይጠበቃል። በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለከተማ  ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ዘመናዊ የንግድ ድርጅት መገንባታቸውን ኢሳት በፎቶ ግራፍ አስደግፎ ማቅረቡ ይታወቃል።
የህወሃት የመከላከያ አዛዦች ጅጅጋን የሃብት ማግኛ ማእከላቸው አድርገው እንደሚቆጥሯት የክልሉ ተወላጆች ሲገልጹ ይሰማል።
በሌላ በኩል ደግሞ የተለያዩ የክልሉ የገጠር ከተሞች በአንበጣ መንጋ መወረራቸው ታውቋል። የክልሉ መንግስት እስካሁን ምንም አይነት እርምጃ አለመውሰዱንም የደረሰን መረጃ ይገልጻል።

Monday, April 7, 2014

ስለፍትሕ ሲባል፤ ሥርዓቱ ይፍረስ!


(ተመስገን ደሳለኝ)

ባለፉት አራት አስርታት ሀገሪቱ አያሌ ተግዳሮቶችን መጋፈጧ ባይዘነጋም፤ በተለያየ ጊዜ ሚሊዮኖችን ካረገፈው አሰቃቂው ረሃብ በማይተናነስ መልኩ ሕዝቦቿን ዋጋ ያስከፈለ ጉዳይ ቢኖር የፍትሕ አለመከበር ያስከተለው ሁለንተናዊ ምስቅልቅሎሽ ነው ብሎ ለመናገር የሚያስደፍሩ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ የየካቲቱን አብዮት ጠልፎ ሥልጣኑን የተቆጣጠረው ወታደራዊው ደርግ፣ የፍርድ ቤት ደጆችን በጓጉንቸር ቆልፎ ሲያበቃ፣ የራሱ አባላት እጃቸውን እያወጡ ድምፅ በመስጠት በአፄው ባለስልጣናትንም ሆነ ግብረ-አበሮቹ በነበሩ መኮንኖች ላይ የሞት ቅጣትን ያህል የመጨረሻ ከባድ ውሳኔ የማሳለፍን አስደንጋጭ ክስተት ጨምሮ፤ ከከተማ እስከ ገጠር ያደራጃቸው የአብዮት ጠባቂዎችና የገበሬ ማሕበራት ከየቤቱ አንቀው እያወጡ “ነፃ እርምጃ” እንዲወስዱ፣ ከየእስር ቤቱ እየለቃቀሙ በጅምላ እንዲረሽኑ በአዋጅ የፈቀደበት ጊዜ የፍትሕ ምኩራቡ ፈርሶ በግላጭ የተቀበረበት ዕለት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በርግጥ ይህ የማን-አለብኝነት አረመኔያዊ አገዛዝ የታቃውሞውን ጎራ በማጠናከር ታሪካዊ ውድቀቱ እንዲፋጠን ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ እንደነበር ለመረዳት 17 ዓመታትን መውሰዱ አይዘነጋም፡፡

“ፍትሕ አልባው አምባ-ገነናዊ የደርግ ስርዓት አማርሮ በርሃ ያስወጣንና ብሶት የወለደን የለውጥ ሃዋርያት ነን፤ በመቃብሩም ላይ ፍትሕ-ርትዕ የሰፈነባት ዲሞክራሲያዊት አገር እንመሰርታለ” በማለት ከበሮ ይደስቁ የነበሩት የያኔው “ነፃ አውጪዎች”ም፣ ደርግ አፍርሶ የቀበረውን የፍትሕ ምኩራብ አመዱን አራግፈው ቢያነሱትም፤ ባነበሩት አስመሳይ ሥርዓት በኩል በዘውግ ማንነት፣ በሙስናና በሙያ አልባ ዜጎች በክለው ክብር የለሽ ሲያደርጉት በጣት የሚቆጠሩ ወራት እንኳ አልፈጀባቸውም፡፡ ‹‹አዲስ ንጉስ አንጂ ለውጥ መቼ መጣ!›› እንዲል ከያኒው፤ ካስወገዱት የደርግ መንግስት ጋር ልዩነታቸው-ደርጉ ያልቻለበትን የተቃውሞ ድምፆች በአዋጅ እንዲንቀሳቀሱ በአንድ በኩል ፈቅደው፣ በሌላ በኩል መልሶ ለመጨፍለቅ የፍርድ ቤቶችን ባረኮት የመጠቀም ባለ ሁለት ገፅ ብልጠታቸው ብቻ ነው፡፡

ይህ አይነቱ አገዛዝም ሥልጣን በያዘ ማግስት ሀገሪቱን እንዳሻው ለመርገጥ ሲቪል ቢሮክራሲውን ብቻ ሳይሆን የፍትሕ ስርዓቱንም በአምሳሉ አፍርሶ መስራት ነበረበት፡፡ ይሁንና ተቋሙን በዚህ መልኩ ለማዋቀር ጊዜ እንደሚያስፈልግ በመረዳቱ አሁን ድረስ በቂ መከራከሪያ ሊቀርብላቸው የማይችሉ ጉዳዮችን ከፍትሕ ሥርዓቱ ነጥቆ ሕገ-መንግስቱ ውስጥ በመዶል ለሌሎች ሰጥቷል፡፡ ለዚህ ደግሞ በቂ ማሳያ የሚሆነው፤ ሕገ-መንግስታዊነትን አስመልክቶ የሚነሱ የማጣራት ኃላፊነቶችን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መስጠቱ ነው፡፡ በርግጥ አንዳንድ የወቅቱ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ሕገ-መንግስቱ በተረቀቀበት ሰሞን፣ ከሕገ-መንግስቱ የሚጣረሱ አዋጆች፣ ክሶች አሊያም ኩነቶች ሲፈጠሩ፣ የማጣራቱ ኃላፊነት የፍርድ ቤት መሆን አለበት ሲሉ የተከራከሩ ድምፆች ነበሩ፡፡ ዳሩ ውሎ-አድሮ ምን እንደሚሰሩ አስቀደመው የሚያውቁት ታጋዮች፣ በዛ ካድሬ-ዳኞች ባላፈሩበት ወቅት እንዳሻቸው ሕገ-መንግስቱን እየናዱ ቢያስሩ፣ አዋጅ ቢያወጡና ቢያስፈርዱ ድጋፉን የሚሰጣቸው ተቋም፣ በኢሠፓውያን እንደተሞላ የሚጠረጥሩት ፍርድ ቤት ሳይሆን፣ እንደ ልብ ሊቆጣጠሩት የሚችሉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት መሆኑን በመረዳታቸው፣ በፓርላሜንታዊ ሥርዓት ትመራለች በተባለች ሀገር ብዙም ባልተለመደ አኳኋን ሕገ-መንግስታዊ ትርጉም የሚሻቸውን ጉዳዮች የማጣራት ስራን ለዚሁ ምክር ቤት ሰጡት፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም በጥቂት ዓመታት ውስጥ የፍትሕ ተቋሙን በፓርቲ ፖለቲካ የተተበተበ፣ ለጉልበተኛ የሚገብር፣ ገንዘብ ሊገዛው የሚችል፣ ተቀናቃኝ ድምፆችን የማፈኛ መሳሪያ… አድርጎ የመቅረፅ ዓላማቸውን ማሳካት ችለዋል፡፡ በውጤቱም ተቋሙ የህግ የበላይነት የተደፈጠጠበት አድሎአዊና በየጊዜው ደካሞችን የሚያጠቃ ከሆነ እነሆ ከሁለት አስርት በላይ አስቆጥሯል፡፡

የሆነው ሆኖ የሥርዓቱን ፍትሕ ረጋጭነት በተጨባጭ ፍፃሜዎች አስደግፎ ለማቅረብ ሁለት አብነቶችን እጠቅሳለሁ፡፡ ቀዳሚው የበርካታ ግፉአንን እሪታ ሲወክል፤ ተከታዩ ደግሞ የገዥዎቹን የሙስና እና የጓዳ ፖለቲካ ትስስሮች ይጠቁመናል ብዬ አምናለሁ፡፡

የሞገስ ወልዱ-ጩኸት

ሰማይ ከመፍገጓ በፊት፣ ሁሌ ንጋት ላይ ኮተቤ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ተነስቶ፣ በእግሩ ሰከም ሰከም እያለ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ግድም ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይደርስና ዋናው በር ፊት ለፊት ቆሞ ከአንድ ሰዓት ላላነሰ ጊዜ ‹‹ሌባ ዳኛ!›› እያለ ይጮኻል፡፡ ያፏጫል፡፡ ‹‹እናንተ ገላችሁኛል፤ ቀብራችሁኛል፤ አምላክ ፍርዱን ይሰጣል!›› በማለትም ተስፋው በሰማያዊው መንግስት ላይ ብቻ እንደሆነ ያውጃል፡፡ …ይህ ሰው እንደምን ያለ ከባድ በደል ቢደርስበት ይሆን ምሬቱ እንዲህ ጣራ የነካው?
አሳዛኙ የሞገስ ታሪክ እንዲህ ይጀምራል፡- በ1997 ዓ.ም የወላጅ እናቱን ወ/ሮ አስካለ ቢፋ ህልፈት ተከትሎ፣ ወንድሙ ኃይሉ ወልደአማኑኤል የወራሽነት ድርሻውን እንዲያካፍለው ክስ መስርቶ ሲያበቃ፤ ሶስት ጥያቄዎችን ለፍርድ ቤቱ ያቀርባል፡-
‹‹ንብረትነቱ የእናታችን የሆነ ቀበሌ 14/15 ውስጥ የሚገኝ 250 ካሬ ሜ. ላይ ያረፈ መኖሪያ ቤት፣ ሁለት ማሳ የእርሻ መሬት እና በንግድ ባንክ አራት ኪሎ ስላሴና መገናኛ ቅርንጫፍ የተቀመጠ መጠኑ ያልታወቀ ገንዘብን ያካፍለኝ፡፡››

የከሳሽ ወንድም የሆነው ኃይሉም ፍርድ ቤት ቀርቦ ‹‹ቤትም ሆነ የእርሻ መሬት የሚባል ነገር የለም፤ በባንክ አለ ስለሚባለው ገንዘብም አላውቅም፤ እናታችን በሞተችበት ወቅት ስሟን ለማስጠራት ስል የእርሷ የነበረውን መሬት በ30 ሺህ ብር ሸጬ፤ ለአርባ፣ ለመንፈቅ፣ ለተስካር 10 ሺህ ብር ያወጣሁ ሲሆን፤ ቀሪውን 20 ሺህ ደግሞ ለወንድሜ ማረፊያ የሚሆን ቤት ሰርቼበታለሁ›› ሲል ምላሽ ይሰጣል፡፡ ችሎቱም ‹ቤቱንና የእርሻ መሬቱን በተመለከተ የቀረበ ማስረጃ አለመኖሩን› ገልፆ ‹የ30 ሺህው ጉዳይ ግን ያለይግባኝ ባይ ፍቃድ ወጪ የተደረገ ስለሆነ፤ የገንዘቡ ግማሽ 15 ሺህ ብር ድርሻው ስለሆነ እንዲሰጠው› በማለት ወስኖ መዝገቡን ይዘጋል፡፡ በውሳኔው

እጅግ በጣም የተበሳጨው ሞገስ፣ ጉዳዩን በይግባኝ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ይወስደዋል፤ ይግባኝ ሰሚውም ‹‹ቤቱ ይገኝበታል›› የተባለው ቀበሌ የእናታቸውን ማህደር እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ ግና፣ ሀገሪቷ ኢትዮጵያ ናትና፤ ቀበሌው ማህደሩ መጥፋቱን፣ ሟችም በተከሳሽ ቤት ይኖሩ እንደነበረ በደብዳቤ ያሳውቃል፡፡ ሆኖም ቀበሌው ይህንን ምላሽ ከሰጠ ከ14 ቀን በኋላ ‹የቀድሞውን አስተዳደር ጠይቄ ያገኘሁት መረጃ ነው› በማለት ለፍርድ ቤቱ እንዲህ የሚል ሌላ ደብዳቤ ይልካል፡- ‹ወ/ሮ አስካለ የግል መኖሪያ ቤት የነበራቸው ሲሆን፣ ቤቱ ያረፈበት መሬት ለ‹‹ሪል እስቴት›› በመሰጠቱ፤ ምትክ ቦታና ስድስት ሺህ ብር ወስደዋል›፡፡ የሰው ምስክሮችም ቀርበው ሟች እናት ቤት ሰርተው እንደነበረ ያረጋግጣሉ፡፡ ይህም ሆኖ የወ/ሮ አስካለ ማህደር ከቀበሌው ‹‹ጠፍቷል›› በመባሉ ምንም አይነት ማስረጃ ስላልቀረበ የቀድሞው ውሳኔ በይግባኝ ሰሚው ችሎትም ሊለወጥ አልቻለም፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ላለፉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛው ፍርድ ቤት በር ላይ ቆሞ መጮኽን ስራዬ ብሎ ይዞታል፡፡ በርግጥ ከቀን ቀን አካላዊ መዳከም እየበረታበት መሄዱ በግልፅ ቢታይም የ40 ዓመቱ ጎልማሳ ሞገስ ወልዱ ዛሬም ከፍርድ ቤት ደጅ ቆሞ መጮኹና ማፏጨቱ የበርካታ ግፉአንን ድምፅ የሚወክል ይመስለኛል፡፡

ይህ ጉዳይ የሚያሳየው፣ የመንግስት ደመወዝ እየተከፈላቸው በዜጎች ሕይወት ላይ ሊወስን የሚችል እንዲህ አይነቱን ማስረጃ ያለአንዳች ጭንቀት ‹‹ጠፋ›› ብሎ ለመናገር የሚደፍሩ፣ ስለሕዝብ ብሶትና ችግር ምንም ግድ የሌላቸው ካድሬዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም እንደ ሞገስ ያሉ የፍትሕ እጦት ረመጥ ሆኖ ያንገበገባቸው ምስኪኖች በአደባባይ ሲጮኹ ውለው፤ ሲጮኹ ቢያድሩ ‹‹ምን ይሆን ችግራቸው?›› ብሎ ለማድመጥ የሚሞክር አንድ እንኳን ባለሥልጣን መታጣቱንም ጭምር ነው፡፡ ‹‹ሳይሰሙ ቀርተው ይሆናል!›› ማለቱን ከባድ የሚያደርገው ደግሞ፣ በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አካባቢ የሚተላለፉ መንገደኞችም ሆኑ ወደ ተቋሙ የሚመጡ ባለጉዳዮች ክስተቱን የማወቃቸው እውነታ ነው፡፡ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ሰዎችን የችሎት ውሎ ለመሰለል ከተከሳሾች ቀድመው የሚደርሱ የደህንነት ሰራተኞችም ሞገስን ለማወቃቸው እኔው ራሴ ምስክር ነኝ፡፡ በአናቱም ከዚህ ቀደም በሸገር ራዲዮ ‹‹ኧረ በሕግ›› የሚል ፕሮግራም ያዘጋጅ የነበረውና በአሁኑ ወቅት በ97.1 ኤፍ.ኤም ‹‹የእኔ መንገድ›› የተሰኘ በተመሳሳይ ጭብጥ ዙሪያ የሚያተኩር ፕሮግራም የሚያዘጋጀው በሳሉ የሕግ ባለሙያ ሰለሞን ጓንጉል፣ ይህንን ታሪክ ከአንዴም ሁለቴ ለአድማጭ አድርሶታል፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ነው ከቀበሌ አንስቶ ላይ ድረስ ያሉ መንግስታዊ መዋቅሮችን የዘረጋውና የሚቆጣጠረው የኢህአዴግ አመራር አባላት፣ የሞገስን ጩኸት ‹‹አልሰሙም›› ማለቱን ከባድ ያደረገው (በነገራችን ላይ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ግቢ ለአስር አመት ያህል በየቀኑ እየተመላለሱ የሚቆሙ አንዲት አዛውንት እና በፍትሕ ሚኒስቴር በር ላይ ቆማ መዋል ከጀመረች ስድስት ዓመት ያለፋት ራሄል የተባለች አቤት ባይ እንስት… መኖራቸውን አልዘነጋሁም)

ሙስና እና የጓዳ ፖለቲካ ትስስሮሽ

አገሪቷ በዚህ ሁሉ መፍትሔ እጦትና በፍትሕ መዛባት እየተመሰቃቀለችና በሕዝቦቿም ዋይታ እየተናወፀች ቢሆንም፤ መጽሐፉ ‹‹ዓይን አላቸው አያዩም፤ ጆሮ አላቸው አይሰሙም›› እንዲል፤ ገዥዎቻችን ይህን መሰሉን የድሆችና የአቅመ ደካሞች ብሶት መስማትን ፍፁም አይሹም፡፡ እነርሱ የታጋሉትም ሆነ የሚሰሙት አለቆቻቸውንና ባለፀጋዎችን ብቻ እንደሆነ ከሚያሳዩን በርካታ ማስረጃዎች መሃል ለአብነት አንድ ምሳሌ ላቅርብ፡-

ጉዳዩ በሙስና ተጠርጥሮ በእስር ላይ ከሚገኘው የቀድሞ ገቢዎችና ጉምሩክ ዳይሬክተር መላኩ ፈንቴ ጋር ይያያዛል፡፡ ከዚህ ሰው ሃያ አንድ ገፅ ከፈጀ የእምነት ክህደት ቃል ውስጥ ኮነ ምህረቱ የተባለ ግለሰብ በአራጣ ማበደር ተጠርጥሮ ከተያዘ በኋላ ‹‹እነአየለ ደበላ ለዳኛ ጉቦ ሰጥተው በዋስ ከእስር ተፈትተው፣ ከሀገር ለመውጣት ያስባሉ›› የሚል ‹‹መረጃ›› በመስጠት መተባበሩን ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስ እንደነገረው ገልፆ፣ ከእስር እንዲለቀቅ መደረጉን እናገኛለን፡፡ መቼም በሙስና ወንጀል ከተጠያቂነት የሚድን ተከሳሽ የሚሰጠው መረጃ ተጠርጣሪዎችን በሕግ ለመጠየቅ የሚጠቅም ሲሆን እንጂ፤ እንዲህ ባለ ከዋናው ክስ ጋር በማይዛመድ ተራና የአሉ-ባልታ ወሬ አለመሆኑን እነገብረዋህድና እነመላኩ ቀርቶ ማንኛውም መንገደኛ እንኳ ሊጠፋው አይችልም፡፡ አውቆ የተኛ… እንደሚባለው ካልሆነ በቀር፡፡

የሆነው ሆኖ ከመላኩ ፈንቴ የእምነት-ክህደት ቃል ትኩረት የሚስበው፣ ግለሰቡ በዚህ መልኩ ከሱ ተነስቶለት ከእስር ከተፈታ በኋላ ንብረቱና የባንክ ሒሳቡ መታገዱን አስመልክቶ የተፈጠረው ኩነት ነው፡፡ አቶ መላኩ ጉዳዩን ለመርማሪዎቹ ሲያብራራ ቃል-በቃል እንዲህ ነበር ያለው፡-

‹‹አቶ አባይ ፀሀዬ እና አቶ ደመቀ መኮንን ደውለው ‹ግለሰቡ አቤቱታ እያቀረበ ነው፡፡ ለምን አታዳምጡትም? ሲሉኝ፤ እኔም ከዚህ በኋላ ነው ግለሰቡን እቢሮዬ አግኝቼ ከላይ በገለፅኩት ሁኔታ እንዲስተናገድ ያደረኩት፡፡››

እነዚህ ሰዎች ‹‹ነፃ አወጣነው›› የሚሉትን ሕዝብ ለስቃይ ዳርገው፣ ጥቂት ባለፀጎችን ብቻ ለማገልገል የቆሙ መሆናቸውን ለማስረገጥ ከዚሁ የእምነት-ክህደት ቃል አንድ ማሳያ ልጨምር፡- ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ የተባለ የአዲስ ልብ ህክምና ክሊኒክ ባለቤት ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው የሕክምና መሳሪያዎች (የልብ ፒስ ሜከር ተብሎ ተጠቅሷል) በሕገ-ወጥ መንገድ ሲያስገባ በቦሌ ኤርፖርት ጉምሩክ ሠራተኞች እጅ ከፍንጅ ከተያዘ በኋላ መለቀቁን በተመለከተ የህወሓት ከፍተኛ አመራር አባል የሆነው ዶ/ር ቴዎድሮስ አድህኖም ስልክ ደውሎ ‹‹ክሱን ብታነሱላቸውና በአስተዳደራዊ መፍትሔ ብትሰጧቸው›› ብሎ ከመንገሩም በላይ የግለሰቡ ክስ እንዲቋረጥ የሚጠይቅ ደብዳቤ እንደፃፈላቸው መላኩ ፈንቴ ለመርማሪዎቹ መናገሩ በመዝገቡ ላይ ተጽፎ ይገኛል፡፡ ይህንን ሁናቴም ከወቅቱ የፖለቲካ አሰላለፍ አኳያ ስንተነትነው አቶ መላኩ ‹ዶ/ር ቴዎድሮስን መስማት፤ ህወሓትን እንደመታዘዝ ነው› የሚል እምነት አድሮበት የተባለውን ፈፀመ ብለን ብንደመድም ተምኔታውያን አያሰኘንም፡፡

እነዚህ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ያውም ሀገር በሚጎዳ ወንጀል የተከሰሰ ተጠርጣሪን በተመለከተ ከሥልጣን ገደባቸው አልፈው ‹‹አድምጥ!›› እያሉ የማዘዛቸው ምስጢር ሥርዓቱ ለፍትሕ ያለውን ግድየለሽነት እና በዚህ ሥርዓት የሕግ የበላይነት ብሎ ነገር

እንጦሮጦስ መውረዱን ፍንትው አድርጎ ያሳያል ብዬ አምናለሁ፡፡ በርግጥ ይህንን ጉዳይ ለጥጠን ከተመለከትነው ‹‹…ለምን አታዳምጡትም?›› የምትለዋን ቃል ሰምና ወርቅ የለበሰች ቅኔ አድርገን በመውሰድ ልንፈታት እንችላለን፤ በተለይም መላኩ ፈንቴ ከዚህች ጥያቄ መሰል ትዕዛዝ በኋላ ግለሰቡን ቢሮ ጠርቶ ማስተናገዱን ስናስተውል፡፡ ምንም እንኳን አባይ ፀሀዬ በጊዜው በጉዳዩ ላይ መላኩን ሊያዝበት የሚያስችል መንግስታዊ ሥልጣን /የዕዝ ተዋረድ/ ባይኖረውም፤ አንጋፋ የህወሓት አመራር አባልና የበለጠ የፖለቲካ ጉልበት ያለው መሆኑ፤ ደመቀ መኮንን ደግሞ በብአዴን በኩል የአለቃነቱ ነገር ሲታሰብ፣ አሁንም መላኩ ፈንቴ የተጠየቀውን ‹‹ጥያቄ›› ከማስተናገድ ውጪ ሌላ አማራጭ አይኖረውም ወደሚል ጠርዝ ይገፋናል፡፡ በርግጥ እውነታው ይህ ቢሆንም፣ መላኩ ዛሬም እስር ቤት ውስጥ ሆኖ የቀድሞ አለቆቹንም ሆነ ራሱን ተጠያቂ ለማድረግ አልደፈረም፡፡ በግልባጩ ለቀረቡበት ክሶች በሙሉ ተጠያቂው ገብረዋህድ እንደሆነ ከመናገሩም በላይ እንዲህ በማለት ወንጅሎታል፡-

‹‹የአያት ባለቤት በግብር ማጭበርበር ተከሶ በነበረበት ወቅት የተከሳሹ ቤተሰብ የሆነ ሰው እቢሮዬ መጥቶ ‹ገብረዋህድ ምንም ጥፋት ሳያጠፋ ነው የአያት አክሲዮን ማሕበር ባለቤትን ያሳሰረው፤ አሁንም አንድ ሚሊዮን ብር ካመጣችሁ ከእስር ይፈታል ብሎናል› የሚል ጥቆማ አመጣልኝ፡፡ …ገብረዋህድ እና ነጋ ገ/እግዚአብሔር (የነፃ ትሬዲንግ ባለቤት ነው) ጓደኛሞች ናቸው፡፡ ነጋ ዕቃ ሲያስመጣ አያስፈትሽም፤ የነጋም ጓደኞች እነ አልሳም፣ ጌት አስ የመሳሰሉት ድርጅቶች ዕቃ በቀላል ቀረጥና ታክስ እንዲሁም አልፎ አልፎ ሳይፈተሹ ያልፋሉ፤ …ባለቤቱ ሃይማኖትም፣ በነጋ ድርጅት ውስጥ ትሰራለች…››

መላኩ ፈንቴ ይህንን ጉዳይ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መናገሩንና ጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ ፀጋዬ በርሄን ‹‹ተከታተል›› ብሎት እንደነበረ ከአስረዳ በኋላ እንደሚከተለው ይቀጥላል፡-

‹‹ገብረዋህድ በኋላ እንደነገረኝ ባለቤቱን ከነጋ ድርጅት አስወጥቶ በአዜብ ትዕዛዝ መሰረት ኤፈርት ውስጥ ያስቀጠራት መሆኑን ገልፆልኝ ‹አንተም ላይ የሚወራው ስለምትታገል ነው ብላኛለች አዜብ› ሲለኝ እኔም ተከታትዬ ፀጋዬ በርሄ ከምን እንዳደረሱት አልጠየኩም፡፡ መጠየቅ ነበረብኝ፤ ጥፋት ነው፡፡ በአጠቃላይ ገብረዋህድ ላይ ብዙ ነገር ይባል ነበር፡፡››

መቼም ይህ ምላሽ በ1981 ዓ.ም ከአስመራ ዩንቨርስቲ በኢኮኖሚክስ ዲግሪውን፣ ከአውስትራሊያ በገቢ አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪውን፤ ከለንደንም በቢዝነስ አስተዳደር በተመሳሳይ መልኩ ትምህርቱን ካጠናቀቀና የረዥም ዓመታት የስራና የፖለቲካ ተሞክሮ ካለው ሰው የተሰጠ መሆኑን ስናስተውል፤ ሀገሪቱ የአምባገነን ባለሥልጣናት መቀለጃ ብቻ ሳትሆን፤ የሰዎቹንም የአቅም ማነስ ያመላክታል፡፡ እንዲሁም እነሞገስ ሰሚ ያላገኙበትን ምክንያትም ሆነ በዚህች ሀገር ገንዘብ ያለው የፈቀደውን መፈፀም የመቻሉን ምስጢር ይገለፅልናል፡፡

ኢህአዴጋዊ ዕድሜ ማራዘሚያ…

ገዥው ስብስብ የፍትሕ ስርዓቱን ተቋማዊነት ሳይነካ፣ ለጨቋኝነቱ መጠቀሚያ የሚያደርግበት አንዱ መንገድ ከጠቅላይ እስከ ታች በተዋረድ የሚገኙ ፍርድ ቤቶች ድረስ ያሉ ዳኞችን የሚመድብበት አካሄድ ነው፡፡ በርግጥ እንዲህ አይነቱ ሀገርና ሕዝብ አልያም ሞራላዊ ልዕልና እና የሕግ-የበላይነት የማያስጨንቀው አገዛዝ፣ የፍትሕ ስርዓቱ ቅጥ የለሽ ተባባሪነት ሳይታከልበት የሥልጣን ዕድሜውን ማራዘም እንደማይችል መረዳት አይሳነውም፡፡ ይህን ለማድረግም ያለው ብቸኛ ምርጫ ዳኞቹን ከስሩ መሰብሰብ ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢህአዴግ መሩ-መንግስት ሁለት አካሄዶችን ለመተግበሩ ያሳለፋቸው ሁለት አስርታት በሚገባ ያሳያሉ፡፡

የመጀመሪያው የሚሾሙት ዳኞች፣ የግንባሩ ከፍተኛ የካድሬ ማሰልጠኛ እንደሆነ ከሚነገርለት ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ተማሪዎች መካከል ማድረጉ ነው፡፡ ከዚህ ‹‹የትምህርት›› ተቋም ውስጥ የሚወጡ የሕግ ምሩቃን ደግሞ ስለጥልቅ ዘመናዊ የሕግ ፅንሰ-ሃሳብ ለማወቅ ከመትጋት ይልቅ፤ የኢህአዴግ ፖሊሲዎች እና አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሕግን እንዴት ‹‹ለመደብ ጠላት›› መጠቀም እንደሚያስችሉ በሚሰብኩ መምህራን ስር እንዲያልፉ ይገደዳሉ (ስለመምህሮቹ ምሁራዊ ልሽቀት ለመረዳት የሕዝብ ሙስሊሙን ጥያቄ በሽብር ተግባር ለመፈረጅ እና ማሕበረ ቅዱሳንን በአክራሪነት ለመወንጀል በ‹‹ጥናታዊ ጽሑፍ›› ስም የተጓዙበትን ርቀት ማየቱ ብቻ በቂ ይመስለኛል)፡፡ ተማሪዎቹም በዚህን መሰሉ የካድሬ ተቋም ስልጠና ስር ሰንብተው ሲወጡ፤ በፍፅምና ሊታመኑላቸው ይገቡ የነበሩትን ፍትሓዊ ዳኝነትና ህሊና የሚባሉ ጉዳዮችን ጨፍልቀው፣ በተለይም ፖለቲካዊ ነክ በሆኑ አይረቤ ክሶች ፊታቸው በሚቆሙ ንፁሀን ዜጎች ላይ መከራን የሚያዘንቡ አሽከሮች ይሆናሉ፡፡ ይህንን አስነዋሪነት ካለመታከት የሚፈፅሙትም፣ ሥልጣንን እና ተያያዥ ጥቅማ-ጥቅሞችን እያጋበሱ ወደ ከፍታ ሲወጡ ተመልክተናል፡፡

ሁለተኛው የግንባሩ አካሄድ ከካድሬ ማሰልጠኛውም ሆነ የተሻለ ነው ከሚባለው የአ.አ.ዩ. የሕግ ፋካሊቲ የሚመረቁትን፣ በተከታታይ ርዕዮተ-ዓለማዊ ጠመቃ የሥርዓቱ ጋሻ-ጃግሬ ማድረግ ላይ ያተኮረው ነው፡፡ በሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ሲያገለግሉ ቆይተው ስደትን የመረጡ ዳኞችና ዐቃቢ-ህግያት በተለያየ ጊዜ እንደ መሰከሩትም አሰልቺ የርዕዮተ-ዓለም ጠመቃ የፍትሕ ሥርዓቱን ነፃነት ጽልመት ካላበሱት ሂደቶች በዋነኛነት ተጠቃሽ ነው፡፡ በአንድ ወቅትም ሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ የሀገሪቱን ዳኞች ሰብስቦ ስለሕገ-መንግስት እና ሕገ አተረጓጎም መርህ ሲያስተምር ለማየት የተገደድነው የዚሁ የጠመቃው አንድ አካል በመሆኑ ይመስለኛል፡፡ ዳሩስ፣ ይህማ ባይሆን ኖሮ እስክንድር ነጋ ላይ 18 ዓመት መፍረድ ሕሊና እንዴት ይፈቅድ ነበር? ኦልባና ሌሊሳንስ ለ11 ዓመታት ወህኒ ያስወረወረው ጥፋት ምን ተብሎ በአሳማኝ መልኩ ሊጠቀስ ይችል ይሆን?
… ቀሪው ለሳምንት ይቆየን!

ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com – April 6, 2014

Sunday, April 6, 2014

በደሴ ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ ተደረገ

April 6, 2014

UDJ party demonstration in Dese
አንድነት ፓርቲ “የሚሊዮኖች ድምጽ ለመሬት ባለቤትነት” በሚል መሪ መፈክር በተለያዩ ከተሞች የሰላማዊ ሰልፍ እንደሚደረግ ባሳወቀው መሰረት ዛሬ በደሴ ከተማ ብዙ ሺህ ህዝብ አደባባይ ወጥቶ ድምጹን ሲያሰማ ውሏል።
በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ከተስተጋቡት መፈክሮች ውስጥ ጥቂቶቹ፣
- መሬት ከካድሬው ወደ ህዝቡ ይመለስ
- አንድነት ኃይል ነው
- የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ
- መሬት ለህዝብ ይመለስ
- ጭቆና በቃን
- ድል የህዝብ ነው
- በግፍ የታሰሩ ይፈቱ
በሰላማዊ ሰልፉ ማብቂያ ላይ የአንድነት ፓርቲ ተ/ም/ፕሬዝዳንት አቶ ተክሌ በቀለ፣ የአንድነት ፓርቲ ውጪ ጉዳይ ኃላፊ ኢ/ር ዘለቀ ረዲ እንዲሁም የአንድነት ፓርቲ የደሴ ሰብሳቢ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በህወሃት/ኢህአዴግ ማስፈራሪያ ሳይሸበር አደባባይ ወጥቶ ድምጹን ያሰማውን የደሴና አካባቢውን ህዝብ አመስግነዋል።

Thursday, April 3, 2014

የጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ መልዕክት ከሳዑዲ አረቢያ እስር ቤት


Nebiyu Sirakግፍ ከበዛበት ወህኒ የአክብሮት ስላምታየ ይድረሳችሁ!
እነሆ ለሁለተኛ ጊዜ ለአፍታ ያህል እድሉን አግኝቸ ወህኒ የመውረዴን እውነታ ላስረዳችሁ ግድ አለኝ ። ዛሬ አስረግጨ የምነግራችሁ ወህኒ የመውረዴ ምክንያት ሚስጥር ግምሽ እድሜየን ህግና ስርአቷን አክበሬ የኖርኩባትን የሳውዲት አረቢያን ህግ ተላልፊ አይደለም ! የስደተኛው ጉዳይ ያገባኛል በሚል የማቀርበው መረጃ ቅበላየ የማይመቻቸው ፣ ያመማቸው ከተሰረሰውና እየተሰራ ካለው ከእገታው ጀርባ ስለመኖራቸው አልጠራጠርም ። … ዛሬ በዚህ ዙሪያ ብዙ አልልም!
አላወቁትም እንጅ ክፉዎች ጠቅመውኛል ፣ ያላየሁትን እንዳይ አድርገውኛል። መንገዱ የከፋ ቢሆንም በወሰዱኝ መንገድ ተመርቸ እሰማው የነበረውን የወገኖቸ የወህኒ የከፋ ኑሮና ህመም ፣ በተቆርቋሪ ጠያቂ ማጣት ፣ በፍትህ መነፈግ እይሆኑ ያሉትን ከመስማት ማየት ማመን ነውና በአካል ማየት ችያለሁ !
ከመታሰሬ ጥቂት ቀናት በፊት በግፍ ለተደበደበው፣ ሁለት አይኑን ላጣውና ” አይሆኑ ከሚሆን ቢሞት ይሻላል “ተብሎ የፎቶ መረጃው ሳይቀር በእጀ የገባውን ወጣት ምንዱብ የወህኒ ህይወትን ተጨባጭ ታሪክ ከአይን እማኞች ቃርሜያለሁ! እሱም ያለው ከታሰርኩበት የቅርብ ርቀት ነው ። … አትጠራጠሩ አገኘውም ይሆናል !
በዚህ የጭንቅ ሰአት ከእኔና ከቤተሰቦቸ ጎን ሆናችሁ አለኝታችሁን ለገለጻችሁልን ምስጋናየ ከፍ ያለ ነው ! ዛሬ ወደ ዝርዝር ጉዳዩ አንገባም ። በላይ በመላ አለም የምትገኙ ወገኖቸ ያሳያችሁኝ ድጋፍና መቆርቆር ከጨለማው ቤት ደርሶኝ ጽናት አጎናጽፎኝ ሰንብቷል። ይህም በአረብ ሃገር ስደተኛ ዙሪያ ሳቀርነው ለነበረው መረጃ ያገኘሁት ክብርና ሞገስ ሆኖ መከራውን አስረስቶኛል: ) ምስጋናየ አይለያችሁ!
ወገኖቸ ወዳጆች ፣ ዛሬ ሰላም መሆኔን ብቻ ተረዱ ብየ እንጅ በሰፊው ስለሚሆነው አቅም በፈቀደ መጠን እናወራለን ! ዝምታው ከናፈቅኳቸው ልጆቸ ፣ ከቤተሰቦቸና ከእናንተ ጋር የሚያደርሰው መንገድ ውል እንዲይዝ የሚደረገው ሙከራ ውል እንዲይዝ የሚተጉ ወገኖችን ሂደት ላለማደናቀፍ ብቻ ለመረጋጋት ሲባል ብቻ ነው !
በጨለመው የሳውዲ ወህኒም ይነጋል ፣ በንጋቱ ጮራ ታግዘን የምናወጋው የማለዳ ወግ ናፍቆኛል: ) ይህን ለማድረግ የሚከፈለውን ሁሉ ለመክፈል ደግሞ ልቤ ብርቱ ነው …
ሰላም ለሁላችሁ !
ነቢዩ ሲራክ
ከአንዱ የሳውዲ ወህኒ ቤት