ዋ! ወንድሜን!
ይድረስ ለወንድሜ “ለማላውቅህ”፣ ባረመኔ ገራፊዎች እጅ ለወደቅኸው፣
በኮረንቲ ሽቦ ገመድ - መላው አካላትህ ለሚላጠው፤
ከጭለማው የግፍ “ቻምበር” - ከሰቆቃ መፈጸሚያው፣
የስቃይህ ጣር ዋይታ - ላለም ጆሮ ለተሰማው።
ከህመምህ ስታገግም - ላንዲት ቅጽበት ብጠይቅህ፣
ምንስ ይሆን “ሃጢያትህ”? በነሱ ዐይን “ጥፋትህ”?
እኔማ ምን አውቄ?
ስቃይህን ሰምቼ እንጂ መጨነቄ፤
ግን፣ ግን...፣
ከሚያቃትተው ድምጽህ ዋይታ፣
እስኪ ልገምት ...”መላ-ልምታ”፣
(በመዝገበ-ማሕደር ተከትቦ- ዓለም የሚያውቀውን እውነታ)፤
...ቆዳህን ባኮርባች ሲልጡ - ስጋህን በብረት ሲያቃጥሉ፣
አጥንትህን ፍቀው ሲግጡ - በስ ብልት ጠርሙስ ሲያንጠለጥሉ፣
አደንዛዥ መርፌ እየወጉ - መርዛቸውን በህዋሳትህ ሲረጩ፣
በቀዝቃዛ ውሃ እየደፈቁ - ከደረቅ ግድግዳ ጋር ሲያጋጩ፣
ጥፍርህን እየነቀሉ - ጸጉር-ጺምህን ሲነጩ...፣
በፈላ ዘይት እየጠበሱ፣
ዘቅዝቀው በመስቀል እንቅልፍ እየነሱ፣
የጸያፍ ስድብ ውርጂብኝ - የጭለማ ክፍል ደባ፣
የአእምሮ ስቃይ በትር - የስነ-ልቦና ሰለባ...፤
ለምኑ ይሆን የተጨነቁ? - አሰቃይቶ “ቃል” ለመቀበል?
“መረጃ” ለማሰባሰብ? - “ፍርድ ቤት” የሚቀርብ ለይምሰል?
እንደዚያማ እንዳልገምት - ፍርድ ቤቱ በጃቸው፣
በቀጭን ትዕዛዝ የሚወስኑ - ፍርደ-ገምድል ዳኞቻቸው፤
እና ታዲያ ለምን ይሆን? በሰው ልጅ ገላ እንዲህ መጨከኑ፣
ያገር-ልጅ በወንድሙ ላይ - ጭራቅ፣ አውሬ መሆኑ?!
… ቀውስ ነው ቂም-በቀል - ያገር-ወዳድ ቅስም ለመስበር፣
በዘረኝነት ጎዳና - ዝንተ-ዓለም ለመዘወር፤
እኩይ መንፈስ ጥላቻ ነው - የበታቸኝነት ስሜት ሕመም፣
ባለም መድሃኒት እማይድን - ነቀርሳ እማይታከም፤
ይድረስ ለወንድሜ “ለማላውቅህ” - ለእምዬ ልጅ የአንዷ፣
ለጋራ እናታችን፣ ለእማማ ኢትዮጵያ ስትል እምትቀበል ፍዳ፣
እግዚአብሔር ጽናቱን ይስጥህ - ከበላዔ-ሰብ መንጋጋ አላቆ፣
ለመልካሙ መጪ ጊዜ ያብቃህ - የተሰቃየህላትን ሀገር ጠብቆ!
ጌታቸው አበራ
ነሐሴ 2006 ዓ/ም
(ኦገስት 2014)
ማስታወሻነቷ፦
ሁለተኛው ክፍል ላይ፣ ከምስሉ በስተጀርባ (ባክ ግራውንድ)ይሰማ ለነበረው የሰቆቃና የስቃይ ደምጽ!
2.በዚሁም መነሻነት፦ ፍትህ፣ እኩልነትና ነጻነት... በሃገራችን እንዲሰፍኑ በመታገላቸው ብቻ፣ የወያኔ ማሰቃያ እስር-ቤቶች
ውስጥ፣ ፍጡር ከሚችለው በላይ የሰቆቃ ግፍ ለሚፈጸምባቸው ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ በሙሉ!
No comments:
Post a Comment