Sunday, November 10, 2013

ሊነጋ ሲል ይጨልማል


ኖቬምበር 10, 2013
ሔለን ንጉሤ/ከኖርዌ

የግፍ ፅዋው ሞልቶ የፈሰሰ መሆኑን ይህ ሰሞኑን በወገኖቻችን ላይ ናየው በደል አመላካች ነው። 
ሁለት አስርተ አመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያውያን ሰቆቃ ሰሞኑን እጅግ የከፋ ሁኔታ ላይ ገኛ  እንዲሁም ሃገራችን ውስጥ ባለው የአስተዳደር በደል እንዲሁም የፖለቲካው ሁኔታ ዘርንና ጎሳን ያማከለ በመሆኑ ዜጎች ዜግነታቸውን የሚጠራጠሩበት ደረጃ ላይ በመድረሳቸው እና ኑሮን ለማሸነፍ በሃገራቸው ሰርተው መኖር ባለመቻላቸው አንዳንዶች ከወያኔ ሽሽት፤ ሌሎች ደግሞ የራሳቸውንና የቤተሰቦቻቸውን የከፋ ኑሮ ለማሻሻል እራሳቸውን መስዋእት በማድረግ ወደማልጉት  ነገር ግን እንደአማራጭ ሆኖ ከፊት ለፊታቸው ድቅን ወዳለው ሥደት እግሬ አውጪኝ ማለቱን ተያይዘውታል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በ2012 አመተ ምህረት ብቻ አንድ መቶ ሰባት ሺህ /107,000/ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ወደ ሳኡዲ አረቢያ እንደተሰደዱ ይነገራል። ይሄ አሃዝ በሌሎቹ አረብ ሐገራት የሚሰደዱትን ሳይጨምር ወደ ሳኡዲ የገቡትን ብቻ መሆኑ ነው። እነኚህ ወጣቶች ግማሾቹ በህጋዊ መንገድ አንዳንዶቹም እንዲሁ ተሰደው በሳኡዲ አረቢያ በስራ ላይ ተሰማርተው እራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን በመርዳት ለረዥም ጊዜ በሳኡዲ ኖረዋል። ሰሞኑን ግን የሳኡዲ አረብያ መንግሥት እነኚህ ወጣቶች ህገወጥ ናችሁ በማለት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየፈፀመባቸው የወንድሞቻችን ህይወት አልፏል፤ ሴቶች እህቶቻችን ተደፍረዋል፤ ሞተዋል። ወጣቶቹ በሳኡዲ ጎዳና ላይ በአደባባይ እየተደበደቡ እየተረገጡ እግርና እጆቻቸው በገመድ እያታሰረ ሲደበደቡ የወጡ ፊልሞች በማህበረ ገፆች ላይ እየተመለከትን ነው እንዲሁም የሰሩበትን እየተዘረፉ በጣም በርካታ ኢትዮጵያውያን በሳኡዲ አረቢያ ጎዳናዎች ላይ በስቃይ አምስተኛ ቀናቸን ይዘው ይገኛሉ። ሊንኩን ይመልከቱ https://www.youtube.com/watch?v=zVtt2amNm4A

 
ወጣቶቹ የወገን ያለህ ያገር ያለህ እያሉ ወገናዊ የድረሱልን ጥሪ ቢያሰሙም በተቃራኒው ለዜጎቹ ግድ የሌለው የወያኔ መንግስት ባለስልጣን አቶ ዲና ሙፍቲ ከመገናኛ ብዙሃን ለቀረበላቸው ጥያቄ የሳኡዲን መንግሥት በመወገን ይመስላል እየተያዙ ያሉት ህገወጦች ናቸው ስለሞቱትም መረጃ የለኝም በማለት በጣም የሚያሳዝን መግለጫ ሰጥተዋል። ዜጎች እንደዜጋ ችግር ሲያጋጥማቸው መጀመሪያ መነሳት ያለበት ዜግነታቸው እንጂ ህገ ወጥ ናቸው አይደሉም ብሎ ክርክርን ምን አመጣው በእውነት መንግስት ዜጎቹን የማይፈልግበትና ሆን ብሎ የሚያሳድድበት ሥርዓት የተመለከትነው በዚህ አገዛዝ ብቻ ነው። ኢትዮጵያዊነት በአለም ደረጃ የተዋረደበት ክብር ያጣበት የመጨረሻ የሚመስል የጨላማ ዘመን ያየንበት አስነዋሪና አሳፋሪ ጥላ ያጠላባትን ኢትዮጵያን ያየንበት ይሄ ዘመን ነው።

ድሮ ድሮ አሉ በንጉሡ ጊዜ ጃንሆይን ምእራባዊያን ከኢትዮጵያ ሰው ለመውሰድ ሲጠይቋቸው ህዝቤን ለባርነት አልሰጥም እምቢ ያሉበት ጊዜ ነበር አሉ። ያሁኑ ገዢዎች ደግሞ በተቃራኒው ጭራሽ ወገኖቻችን እየተሰቃዩና እየተገደሉ ባሉበት ሁኔታ እነዚህ የሚደበደቡትና የሚገደሉት በህገወጥ መንገድ ስለሄዱ ነውና ሌላ አርባ ሺህ /40,000/ ወጣት ገረዶችን በህጋዊ መንገድ እንሰጣችኋለን ብሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተብዬው ቴዎድሮስ አደሃኖም ከሳኡዲ አረቢያ ጋር ውል መፈራረሙን ሰማን አይደንቅም ልማታዊ መንግሥታችን!

ሌላው ከሰሞኑ የኔን ብቻ ሳይሆን የብዙሃንና ወያኔን ጨምሮ ቀልባችንን የሳበ ነገር ሰማን እድሜ ለኢሳት ጆሯችን ትክክለኛ መረጃ ጠግቦ ያድራል ወያኔ በግንቦት ሰባት ንቅናቄ ዋና ፀሃፊ በሆኑት በአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ እና በግንቦት ሰባት ህዝባዊ ሃይል አመራሮች ላይ በዋናነት አነጣጥሮ በተጨማሪ የሌሎች ብዙሃንን ህይወት ለማጥፋት በኢትዮጵያ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት ዋና ሃላፊ በአቶ ጌታቸው አሰፋ እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ በአቶ ፀጋዬ በርሄ ቁጥጥር የተመራው ወያኔ  ሚሊኒየም የተሰኘው የመግደል ሙከራ /ኦፕሬሽን/ መክሸፉን ሰማን። የወያኔ መንግስት በሃገሪቷ ላይ አሸባሪዎች ጥቃት ሊፈፅሙብን ነው እያለ መግለጫ በማውጣት ህዝቡን እያሳቀቀ እራሱ የሽብር ተግባር እየፈፀመ ህዝብ እየገደለ ይገኛል። http://ethsat.com/video/esat-efeta-special-11-november-2013/

በመሆኑም የወሮበሎችን ጥርቅም እስካላስወገድን ድረስ ለህዝባችን ተቆርቋሪ መንግሥት የለምና ወንድሞቼ በሳኡዲ አረብያ እየተሰቃያችሁ ያላችሁ ሁሉ እግዚአብሄር ይድረስላችሁ እናንተ ቆራጥ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይሎች እንዲሁም አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ አይዟችሁ በርቱ እውነት ሁልጊዜም ያሸንፋል ወያኔ ከነክፋት ስራው የሚቀበርበት ጊዜ ደርስዋል ይህ ሁሉ ስቃይና በደል በህዝባችን ላይ የሚደርሰው የግፉ ፅዋ በመሙላቱ ነው ለሃገራችን እግዚአብሄር ደርሷል ግፈኞች የሚዋረዱበት፤ አንገታቸውን የሚደፉበትና እውነተኛ የኢትዮጵያ ልጆች አንገታቸውን ቀና የሚያደርጉበት ያ የብርሃን ወጋገን ከቅርብ ይታየኛል ሊነጋ ሲል ይጨልማልና።



ኢትዮጵያን ከልጆችዋ ጋር እግዚአብሄር ይባርክልን

No comments:

Post a Comment