በመጀመሪያ ደረጃ የከበረ ሰላምታዬን አቀርባለሁ። በውስኗ አቅሜ ይህችን ደብዳቤ ለመፃፍ ስነሳ በውስጤ ብዙ ነገሮችን እያወጣሁና እያወረድኩ ነው። በወንድምና በእህቶቼ ላይ የምትፈፅሙት ኢሰብአዊ ድርጊት በእጅጉ ስላሳዛነኝና ዝምብዬም ማየት ስላላስቻለች ይህችን ደብዳቤ ልፅፍላችሁ ወደድኩ። የዚህች አጭር ደብዳቤዬ አላማ እናንተ ወንድምና እህቶቼ በሌሎች ወንድምና እህቶቼ ላይ የምትፈፅሙትን ኢሰብአዊ ድርጊት እንድታቆሙ ለማሳሰብና ከህዝብ ጎን ለመሰለፍ ግዜው እንዳልረፈደባችሁ ለመጠቆምም ጭምር ነው።
በቅድሚያ ግን ራሴን ስላላስተዋወኳችሁ ራሴን ላስተዋውቅ። ሙሉ ስሜ ኢዮኤል ፍሰሀ ዳምጤ ይባላል። የሀያ ሁለት አመት ወጣት ነኝ። አቅሜ በፈቀደው መጠን ሀሳቦቼን በሶሻል ሚዲያው ላይ የምሰነዝር ጦማሪ በእናንተ አጠራር “ሽብርተኛ” ነኝ። ብእር ያነሳን ሁላ ሽብርተኛ አይደል የምትሉት ፤ ይህች ደብዳቤዬ ብዙ ስያሜ ልታሰጠኝ ብትችልም ለእናንት ከመፃፍ ግን አልቦዘንኩም። በደብዳቤዬ መጀመሪያ ላይም ይድረስ ለኢህአዴግ የደህንነት ክፍል ያልኩበት ምክንያት የአንድ ድርጅት ደህንነት (ኢህአዴግ) እንጂ የኢትዮጲያውያን ደህንነት ስለማያስጨንቃችሁ ነው። በእውነት ለኢትዮጲያውያን በሙላ የቆማችሁ ቢሆን ኖሮ እኔም ይህችን ደብዳቤ መፃፌ ባላስፈለገ ነበር። ድርጊታችሁ እንደሚያሳብቀው የሚያስጨንቃችሁ ነገር የድርጅታችሁ ደህንነት ብቻ ነው።
የሚገዳደራችሁን ወይም መብቱን ለማስነካት ፈቃደኛ ያልሆነ ዜጋ ሲያጋጥማችሁ በተደጋጋሚ የምታሰሟት አንድ የተለመደች አባባል አለቻችሁ። ወንድ ከሆንክ ጫካ አትገባም! ወንድነት እናንተ ቤት የሚለካው ጫካ በመግባት ነው። ሀያአንደኛ ክፍለዘመን ላይ ሆናችሁ ከጫካ አስተሳሰብ አለመላቀቃችሁ ግን በእጅጉ ያሳፍራል። የዶ/ር መረራን ኢህአዴግ ከጫካ ወጣ እንጂ ጫካው ከኢህአዴግ አልወጣም የሚለውን አባባል እኔም በእጅጉ እጋራለሁ። ወንድሞቼ ያለነው እኮ በሀያአንደኛ ክፍለዘመን ላይ ነው። ዓለም በቴክኖሎጂው መስክ ትልቅ እድገት እያሳየ በሚገኘበት ዘመን ላይ እንዴት ስለጠመንጃ ትልቅነት ይሰበካል።
በሀሳብ የተለያችሁንስ እንዴትስ ለምንስ እንደ ጠላት ትቆጥሩታላችሁ። እኔ በበኩሌ ከእናንተ ጋር የሀሳብ ልዩነት ቢኖረኝም እናንተን እንደ ጠላት መመልከት በእጅጉ ይከብደኛል። እናንተ ግን በሀሳብ ከእናንተ የተለየውንና በድርጅታችሁ ላይ ትችት የሚሰነዝረውን ሁላ አሳድዶ በማንበርከክ ስራ ላይ ተጠምዳችኋል። የሀሳብ ልዩነት መኖሩ እኮ ችግር ሊሆን አይገባም። ምክንያቱም ሁሉም ሰው አንድ አይነት ሀሳብ እንዲያመነጭ አይጠበቅምና ፤ አንድን ሰው በሀሳብ ስለተለየ ብቻ ዛቻና ማስፈራሪያ ፣ ድብደባ ፣ እስር ፣ እንግልት የመሳሰሉበት እንዲደርስበት ማድረግ ኢሰብአዊ ድርጊት ነው። ከአለቆቻችሁ በተላለፈላችሁ ትዕዛዝ ሰውን በየፖሊስ ጣቢያውና በተለያዩ ቦታዎች ደህንነቶች ነን በማለት እየወሰዳችሁ የምትፈፅሙት ኢሰብአዊ ድርጊት ዛሬ ባያስጠይቃችሁ እንኳ አንድ ቀን ትጠየቁበታላችሁ። አላማችሁ ዜጎች በሀገራቸው ሀሳባቸውን እንዳይገልፁና ሰጥ ለጥ ብለው እንዲገዙ ማድረግ እንደሆነ እሙን ነው። ይህ ግን በጠመንጃ ሊሳካ አይችልም። ምንም አይነት የሀይል እርምጃ ብትወስዱ አንድን ሰው ከፈጣሪ የተሰጠውን መብቱን ልትወስዱበት አትችሉም።
በቅርቡ በእናንተ የደህንነት ሀይሎች ድብደባ የተፈፀመበትን አንድ ወዳጄን አግኝቼ አናግሬው ነበር። ወዳጄ የሰማያዊ ፓርቲ ምክር ቤት አባል ወጣት ዮናስ ከድር ነው። እዚህ ፅሁፌ ላይ በወጃጄ ላይ የፈፀማችሁትን የመብት ጥሰት ለአብነት ላነሳው ወደድኩ። ምክንያቴ ደግሞ አጋጣሚው የእናንተን ማን አለብኝነትና እብሪት በሚገባ እንደሚያንፀባርቅ ስላመንኩ ነው።
ወጣት ዮናስ ደብደባው እንዴት እንደተፈፀመበት ከጅምሩ በማንሳት እንዲህ ብሎ አወጋኝ “ከላንቻ ፓሊስ ጣቢያ ስልክ ተደውሎልኝ እንደምፈለግ ተነገረኝ። በመቀጠል ወደ ፓርቲዬ ፅ/ቤት አምርቼ ከፓሊስ ጣቢያው ለሌሎች ጓደኞቼ ስልክ ተደውሎላቸው እንደሆነ ጠየቋቸው። እነሱም ስልክ እንዳልተደወለላቸው ነገሩኝ። ይህን ግዜ እኔን ብቻ እንደፈለጉኝ ተረዳሁ። በመቀጠል ከፓርቲያችን የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ጋር በመሆን ወደ ላንቻ ፓሊስ ጣቢያ አመራን። ፓሊስ ጣቢያው እንደደረስን የፈለጉኝ ፓሊሶቹ ሳይሆኑ ከዚህ በፊት ተደጋጋሚ ዛቻና ማስፈራሪያ ሲያስከትልብኝ የነበረ አንድ ደህንነት ነው”።
ደህንነቱ ዮናስን አንድ ክፍል ውስጥ ይዞት ከገባ በኃላ ድብደባና ዘለፋ ያከታትልበት ቀጠለ። ደህንነቱ ወደ ክፍሉ ይዞት ሲገባ በአካባቢው የነበሩት ፓሊሶች እንግዲህ ድብደባ ሊፈፀምበት ነው ሲሉ ማዳመጡን ዮናስ አጫውቶኛል። ድብደባው ሲፈፀም የነበረውም ፓሊሶቹ ቢሮ ወስጥ ነው። ሶስት ሰአት ከፈጀ ድብደባና ዘለፋ በኃላ ዮናስ ድብደባው ፣ ማስፈራሪያውና ዛቻው ከተፈፀመበት ክፍል በመውጣት ላይ እንዳለ ደህንነቱ ከእኛ ጋር መስራት ይኖርብሀል። እዚህ የተፈፀመብህን ነገር ደግሞ ለማንም ትንፍሽ እንዳትል በተለይ ሶሻል ሚዲያው ላይ አንዲት ነገር ማየት አልፈልግም ሲል ማስፈራሪያውን አከለ። ወጣት ዮናስ ወደ ሶስት ሰአት የዘለቀው ደብደባ ፣ ዘለፋና ተግሳፅ ሲካሄድበት የነበረው በወለሉ ላይ ተንበርክኮ እንዳለ ነው። እኔ ወንጀለኛ አይደለሁም ወንጀለኛ ከሆንኩም ክስ ተመስርቶብኝ በፍርድ ቤት ልዳኝ እችላለሁ ሲል ምላሹን ለደህንነቱ የሰጠው ዮናስ ከደህንነቱ በኩል ፍርድ ቤት የማን ሆነና ነው እንዲህ የምትለው ፍርድ ቤት እኮ የእኛ የኢህአዴጎች ነው የሚል ምላሽ እንደተሰጠው አጫውቶኛል። ከላይ በደህንነቱ የተጠቀሰው ፍርድ ቤት እኮ የእኛ የኢህአዴጎች ነው የሚለው ንግግር እናንተ የምታገለግሉት ኢህአዴግን እንጂ የኢትዮጲያን ህዝብ እንዳልሆነ በሚገባ ያመላክታል። ከዛም በተጨማሪ ምን አይነት እብሪትና ድንቁርና በውስጣችሁ እንዳለም ፍንትው አድርጎ ያሳያል። አንድ የደህንነት ባልደረባ ነኝ የሚል ሰው በዚህ ደረጃ ሲናገር መስማት በእጅጉ ያሳፍራል። ታዲያ ይህ የደህንነት ባልደረባ የኢህአዴግ ደህንነት እንጂ የሌላው ሰው ደህንነት ያስጨንቀዋል? ይህ የደህንነት ባልደረባ ነኝ የሚለው ግለሰብ በእንደዚህ አይነት እብሪት ተወጥሮ የሚናገረው የግል አቋሙን ብዬ ለመናገር ይከብደኛል። ይህ የአብዛኞቻቹ ደህንነት ነን የምትሉ ሰዎች አቋም ይመስለኛል።
በዮናስ ላይ የደረሰውን ለአብነት አነሳሁት እንጂ ደህንነት ነን የምትሉ ሰዎች ሁላ ከዚህም እጅግ የከፍ አፀያፊ ተግባርን ነው የምትፈፅሙት። በቅርቡ እንኳ በአንድነት ፓርቲ ምክር ቤት አባል አቶ አበበ አካሉ ላይ የፈፀማችሁት እጅግ ዘግናኝ የሆነ ኢሰብአዊ ድርጊት ይታወሳል።
ዘመኑ የመረጃ ዘመን በመሆኑ እያንዳንዱ የምትሰሩት ግፍ ተደብቆ አይቀርም። ግዜውን እየጠበቀም ይወጣል። በዘረጋችሁ የአፈና መረብና ባነገታችሁት ጠመንጃ ተኩራርታችሁ አለቃዎቻችሁን ለማስደሰትና ከእነሱ የሚወረወርላችሁን ፍርፋሪ ለመልቀም ኢሰብአዊ ድርጊት መከወኑን ትገፉበት ይሆናል። አንድ ነገር ግን እርግጥ ነው። በምትፈፅሙት ኢሰብአዊ ድርጊት የተነሳ የህሊና እረፍት የላችሁም። የህሊና እረፍት የሌለው ሰው ደግሞ በውስጡ ሰላም የለም። በእርግጥ ዛሬ ህሊናችሁ ጥያቄ አንስቶባችሁ አያውቅ ይሆናል። ጥያቄ ያነሳለት ግን እረፍት አይኖራችሁም። ባሪያ ሆኖ ዘወትር ፍርፋሪ ከመልቀም የአንድ ቀን የህሊና እረፍት ፍፁም ሰላምን ይሰጣል። ውድ የኢህአዴግ ደህንነት ክፍል ባልደረቦች ሆይ በዜጎች ላይ የምትፈፅሙትን ኢሰብአዊ ድርጊት በማቆም ከኢትዮጲያ ህዝብ ጎን ለመሰለፍ ጊዜው አልረፈደም። ጊዜው ሳይረፍድ ፈጥናችሁ መርከቧ ላይ በመሳፈር ከህዝብ ጎን ተሰለፉ።
No comments:
Post a Comment