Thursday, December 12, 2013

በሴቶች እህቶቻችን ላይ በሃገር ውስጥ እና በተለያዩ የአረብ ሃገራት እየደረሰ ያለውን ችግር የሚያጋልጥ የፎቶ ኤግዚብሽን በዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ኖርዌ የሴቶች ክፍል የተዘጋጀ ኖቬምበር 15, 2013



ሔለን ንጉሤ/ኖርዌ
December 10, 2013

በሐገራችን ኢትዮጵያ አምባገነኑ  የወያኔ መንግሥት ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ እየተባባሰ የመጣው የዜጎች መብት እረገጣ፤ ሥቃይ፤ እስር፤ እንግልት ባጠቃላይ የሰብአዊ መብት ጥሰቱ እና ህገወጥ የሰዎች ዝውውሩ በአስከፊ ደረጃ እየጨመረ የሚገኝ መሆኑ ይታወቃል። ዜጎች በሚደርስባቸው  የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች እረገጣና ወከባ  ሐገራቸውን ለቀው ወደማያውቁት ሐገር ህይወታቸውን ለማትረፍ የተለያዩ አስቸጋሪ መንገዶችን በመጠቀም ለመሰደድ ይገደዳሉ።

ዜጎች ሃገራቸውን ለቀው ከሚሰደዱባቸው መንገዶች አንዱና ዋነኛው ደግሞ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ነው። ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን በሃገራችን በዋናነት እራሳቸውን ህጋዊ ነን ብለው በሚጠሩ መንግስት በራሱ ባቋቋማቸው ቢሮዎች እና በህገወጥ መንገድ በተደራጁ ነብሰበላ የመንግስት ደላሎች አማካኝነት ይከናወናል። ይህንን የዘመናዊ ባርነት የሚያከናውኑት ደላሎች በየገጠሩ ቤት ለቤት በመቀስቀስ እድሜያቸው ለስራ ያልደረሱ ህፃናትን ጭምር በማታለል የወላጆቻቸውን ሃብትና ንብረት ቅርሳቸውን ሳይቀር እንዲሸጡ በማግባባት ልጆቻቸውን ለዘመናዊ ባርነት በሚዳርጉ ደላሎች አማካኝነት የህገወጥ ዝውውሩ ይካሄዳል።


በዚህ የህገወጥ የሰዎች ዝውውር (ዘመናዊ ባርነት) ዋነኛ ተጎጂ የሆኑት ደግሞ ሴቶች እህቶቻችን ናቸው ሴቶች በዚህ የህገወጥ ዝውውር ወቅት ገና ከመነሻው ጀምሮ የሚደርስባቸው ችግር በርካታ ነው በጉዟቸው ወቅት በመንገድ ላይ በደላሎች ይደፈራሉ ላልተፈለገ እርግዝና ይጋለጣሉ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ተጓዳኝ ለሆኑ የተለያዩ በሽታዎች ይጋለጣሉ፤ እድሉ ቀንቷቸው ያሰቡበት የባርነት ቦታ ሲደርሱ ደግሞ የከፋ ችግር ያጋጥማቸዋል ከነዚህም ችግሮች ጥቂቶቹን ለመዘርዘር ብንሞክር በአሰሪዎቻቸው ከፍተኛ የስራ ጫና ይጣልባቸዋል፤ ካቅማቸው በላይ እንዲሰሩ ይገደዳሉ በአማካይ ከ18 ሰአት በላይ ይሰራሉ፤ በአሰሪዎቻቸው ይደበደባሉ፤ የፈላ ውሃ ይደፋባቸዋል፤ በካውያ ሳይቀር ፊታቸውን ይቃጠላሉ፤ ከፎቅ ላይ ይወረወራሉ፤ በአሰሪዎቻቸውና በልጆቻቸው ጭምር ተገደው ይደፈራሉ አልፎ ተርፎም በአሰሪዎቻቸው ይገደላሉ፤ እራሳቸውንም ሰቅለው ይገኛሉ በማን እና ለምን እራሳቸውን እንዲያጠፉ እንደተደረጉ እንኳን አይታወቅም ጠያቂም የላቸውም ይህንን ሁሉ በደል መሸከም ሲያቅታቸው ደግሞ የአእምሮ በሽተኞች ሆነው እራሳቸውን ስተው በየጎዳናው እራቁታቸውን ሲሄዱ ይታያሉ ዘርዝረን የማንጨርሳቸው በጣም በርካታ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል።

ዜጎቻችንን ወክለው በየአረብ ሃገራቱ ያሉ ኢምባሲዎችም በሴት እህቶቻችን ላይ እየደረስ ያለውን አስከፊ በደል ለመከላከል ምንም አይነት እርምጃ ሲወስዱ አይታዩም ዜጎቻቸውን ሳይሆን የወከሉት ያሉበትን ሃገር ወክለው የተቀመጡ እስኪመስል ድረስ ቅንጣት ያህል እርህራሄ አይታይባቸውም እህቶቻችን መንግስት አልባ ሆነው በየመንገዱ ሲገደሉ ሲደፈሩ ሲሞቱ አቤት የሚል አለመኖሩ ይታወቃል።

በመሆኑም ህገወጥ የሰዎች ዝውውር በተለይ በሴት እህቶቻችን ላይ እያደረሰ ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግር በሃገር ውስጥ በፖለቲካ አመለካከታቸው የሚደርስባቸውን ሥቃይ፤ እስር፤ ግርፋት፤ እንግልት ከመሬታቸው መፈናቀል እንዲሁም በዚሁ የህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወይም ዘመናዊ ባርነት በአረብ ሃገራት በእህቶቻችን ላይ እየደረሰ ያለው አሰቃቂ ሞት፤ እስር፤ እንግልት ስቃይ፤ እንዲሁም አካላዊና ስነልቦናዊ ችግሮችን ለአለም ህብረተሰብ ለማጋለጥ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የሴቶች ክፍል የፎቶ ኤግዚብሽን እና የፅሁፍ ገለፃ እንዲሁም የእህቶቻችንን ስቃይ የሚያሳዩ የተለያዩ የቪድዮ ምስሎች እና ግጥሞችን በኖቬምበር 15, 2013 አዘጋጅቶ ለህዝብ አቅርቧል።

በዝግጅቱ ላይ ኖርዌጂያንና በርካታ ኢትዮጵያውያን የታደሙ ሲሆን ከቀኑ 16.00 ወ/ሪት ምስራቅ ስለኤግዚብሽኑ አላማ መግለጫ በመስጠት ፕሮግራሙን የጀመሩ ሲሆን በመቀጠል ስለተዘጋጀው የፎቶ ኤግዚብሽንና ህገወጥ የሰዎች ዝውውር በሴቶች ላይ እያደረሰ ያለውን ከፍተኛ ችግር በመዘርዘር ስለፎቶዎቹ ማብራሪያ ወ/ሪት ሔለን ንጉሤ አቅርበው ለመፍትሄውም ለህዝቡ ተቆርቋሪ መንግስት የሚያስፈል በመሆኑ የግድ የስርአት ለውጥ እንደሚያስፈልገን ጠቁመዋል። ሴቶች በሃገር ውስጥ በፖለቲካ አመለካከታቸው እና በተለያዩ ምክንያቶች የሚደርስባቸውን ችግር አስመልክቶ ወ/ሪት ለምለም አንዳርጌ በኤግዚብሽኑ ላይ ለቀረቡት ፎቶዎች ማብራሪያ የሰጠች ሲሆን ወ/ሪት ምህረት አሽኔ ለኖርዌጂያን እንግዶቻችን በቋንቋቸው ስለኤግዚብሽኑ ማብራሪያ ሰጥታለች። በመጨረሻም ወ/ሪት ታወቀች ተሰማ ሰው ባገሩ ቢኖር የተሰኘ አጭር ግጥም አቅርባለች የዚህን ፕሮግራም መድረክ በመምራት ያገለገለችው ወ/ሮ ስርጉት ይልማ ስትሆን ፕሮገራሙ በጣም የብዙ ሰዎችን ልብ ያሳዘነ ነበር በተለይ ለኖርዌጅያኖቹ እንግዳና ያልተለመደ ስለነበር በጣም እንዳሳዘናቸው ገልፀዋል።

ይህ ፕሮግራም በዲሞክራሲያዊ ለውጥ የሴቶች ክፍል ሲዘጋጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ቢሆንም ችግሩ እስኪቀረፍ ድረስ ወያኔ እያደረሰ ያለውን በደል ወደፊት በስፋት እየሰራን ለአለም የምናጋልጥ መሆኑንም በዚህ አጋጣም ለመግለፅ እወዳለሁ።

ሙሉውን ፕሮግራም ይመልከቱ http://www.youtube.com/watch?v=YwldLQWi3is

በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጭቆና እንታገላለን
ኢትዮጵያ  በክብር ለዘላለም ተከብራ ትኑር

   





No comments:

Post a Comment