Saturday, January 11, 2014

በቃ ጥሪኝ ሐገሬ


ሔለን ንጉሴ/ኖርዌ/
ጃንዋሪ 11, 2014

ሰሞኑን በቃ ጥሪኝ ሐገሬ የሚል የህብረት ዜማ ሰማሁ በዚህ ቅንብር ላይ በስተመጨረሻ አካባቢ በሳኡዲ አረብያ ጎዳና ላይ ወጣት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እልህ በተሞላበት አንደበት ኢትዮጵያ አንድ ናት ኦሮሞ፤ ጉራጌ፤ አማራ፤ ትግሬ ሁላችን አንድ ነን እያሉ በሰው ሃገር ጎዳና ያሰሙት ሀይልና ብሶት የተቀላቀለበት ድምፅ ከዜማው የበለጠ መንፈሴን ክፉኛ እረበሸው እናንተንም እንደሚረብሻችሁና እንደሚያሳዝናችሁ እረግጠኛ ነኝ ሙዚቃውን ከታች አዳምጡት እኔ ግን ወደዛሬው ጉዳዬ ልግባ፤

ዘመናችንን ወደኋላ ለሁለት 10 አመታት ጠምዘዝ አድርገን ብንመለከት የነበረን የኢትዮጵያዊነት ኩራታችን፤ ክብራችን፤ ውበታችን፤ ማእረጋችን፤ ሃይማኖታችን፤ ዘራችን፤ ጎሳችን፤ የህብረ ብሄር ቀለማት እሴቶቻችን እነኚህ ሁሉ የምንመካባቸው የኢትዮጵያዊነት ታላቅ መለያችን ነበሩ። ዛሬ ዛሬ እነኚ ሁሉ የጋራ ሐብቶቻችንን ለማየት የማንችልበት ትልቅ ጥቁር መጋረጃ  ከፊት ለፊታችን ተጋርዶ ማንነታችንን፤ አንድነት ህብረታችንን እንዳናይ ተገደናል። አምባገነኑ ወያኔ ይህንን የዘር መጋረጃ ሲጋርድብን እምቢኝ አሻፈረኝ ሳንል በፀጋ የተቀበልን እስኪመስል ድረስ አንደበታችን ተዘግቶ ወኔያችን ተሰልቦ መብታችንን ማስከበር አቅቶን ሁላችንም በየፊናችን ባገኘነው ቀዳዳ ባህር የብሱን አቋርጠን በፀሀይ በጨረቃ፤ በምድረ በዳ በረሃ፤ ዳገት ቁልቁለቱ፤ እረሃብ ጥማቱ፤ ግርፋት እንግልቱ ሳይበግረን ሐገራችንን ለቀማኛ ሰጥተን ያለ እረኛ ብትን ብለን ከተሰደድን ለብዙዎቻችን ዘመናት ተቆጥረዋል።

አልሰደድም እምቢኝ ለመብቴ እምቢኝ ለሃገሬ ብሎ ባለ ብእሩ በብእሩ ለሃገሩ እድገት ሲፅፍ ሲተጋ እውነትን ሲናገር ሲያጋልጥ ዜመኛው በዜማው እያዝናና እያሳዘነ ለመብቱ ሲናገር ፖለቲከኛው በፖለቲካ እውቀቱ የሰብአዊ መብት ጥሰቱን ሲያጋልጥ እውነቱን ሲናገር እውነት አላርጂክ የሆነበት ወያኔ የተገዳደረውን ሁሉ በማእከላዊና በቃሊቲ በዝዋይ ሲያስር ሲደበድብ ሲያንገላታ ሲገድል ሃይ ባይ አጥቶ እየፈነጨ አልሰደድም ሐገሬን አለቅም ባሉ ሁሉ ላይ የፈሪ ዱላውን እያሳረፈ እድሜውን እያራዘመ ድፍን ሃያ ሶስተኛ አመቱን አሳለፈ።

ስደት ለሐገራችን ችግር ዋነኛ መፍትሄ ባይሆንም ስደትን የመረጥነው የሰው ሐገር መሆኑን እያወቅን እንደማይደላን እንደማይመቸን ቢገባንም የተሰደድነው ግን አንድም ለራሳችን በህይወት ለመኖር አንድም ላገራችን መሆኑ ሁላችንንም የሚያስማማን ነጥብ ቢሆንም ቅሉ ሐገራችንን ነፃ እስከምናወጣ ድረስ በሰው ሐገር የተስፋ እንጀራ ዘመናችንን እየጨረስን የምንገኝ ብዙ የኢትዮጵያ ብርቅዬ ልጆች የነገ ሐገር ተረካቢ ወጣቶች መስራት ያለብንን በስደትም ቢሆን በማይመች ሁኔታ ውስጥ እያለፍን ሐገራችንና ህዝባችንን ከአምባገነኑ የወያኔ ቡድን ነፃ በማውጣት ሐገራችን የህግ የበላይነት የሚከበርበት ዜጎች እንደዜጋ እኩል የሚተዳደሩበት ፍትህ የሰፈነበት ዘረኝነት የሌለባት እህቶቻችን ለግርድና የማይሸጡበት እንድትሆንና እኛም የስደት ኑሯችንን ለማሳጠር እና በምንናፍቃት እምዬ እናት ሐገራችን ለመኖር በቃ ጥሪኝ ሐገሬ ብለን አምርረን ትግሉን ከምንችለው በላይ ታግለን ወያኔን እንዳይመለስ አርገን ቀብረን ሐገራችን ለመኖር የሚያስችለንን ሁኔታዎች ማመቻቸት ያለብን እኛው እራሳችን ስደት ላይ የምንኖር ወገኖች ነን።

አምባገነኑ የወያኔ ቡድን እስካሁን ስልጣን ላይ የቆየው ማስተዳደር ችሎ ወይም ከኛ በልጦ ምናምን አይደለም በኛ ድክመት በመጠቀም እሱ ለኛ አጀንዳ ይሰጠናል እኛ በተሰጠን አጀንዳ ላይ ትኩረት ሰጥተን ስንወያይ ስንከራከር ዘራችንን ስንቋጠር የራሳችንን መብት ማስከበር ተስኖን እነሱ በሚሰጡን የቤት ስራ ላይ ትኩረታችንን እያደረግን ዋነኛ ጠላታችን የሆነውን ሥርአት እንዳንመለከት በአጀንዳዎች ተከበን እንገኛለን። ስለዚህ ወያኔ የሚፈጥራቸውን ጊዜያዊ ችግሮች እንደየደረጃቸው ወደጎን በመተው የዚህ ሁሉ ችግር ፈጣሪና ባለቤት የሆነውን የሐገራችን አንድ እና አንድ ጠላት ወያኔ ላይ ትኩረታችንን በማድረግ እንታገልና እራሳችንን ነፃ በማውጣት የሚያሳዝኑ ስደትን የተመለከቱ ዜማዎችን የማንሰማበትን ዘመን እናምጣ በማለት እሰናበታለሁ። ዜማውን ለመስማት ከታች ሊንኩን ይጫኑ፦

ከደመናው በላይ ባለው መንገድ በየብሱም በባህሩ
ከአምበሳው ከአዞ አፍ ተርፎ ኖርኩኝ ብሎ ሲመኝ
በሰው ሃገር ቀረ ሞቶ
ማን ወዶ ይርቃል ከናቱ ካገሩ ባይሞለለት እንጂ ስደትን መምረጡ
ባይሆንለት እንጂ ስደትን መምረጡ.............

                                                                                 ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር

No comments:

Post a Comment