(አስገደ ገ/ስላሴ)
የህወሓት መሪዎች ከመጨረሻ ታህሳስ ወር እስከ ጥር 8/2006 ዓ.ም ድረስ በክልሉ የሚኖሩና በመላው የኢትዮጵያ ክልሎች ተሰማርተው የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ሰብስበው ችግራቹሁ ንገሩን በክልላችን እንቨስትመንት ለመስራት (ለማፍሰስ) የተመቻቸ ሁኔታ አለ ሲሉ ሰነበቱ።
ለዚሁም ከሶስት ሳምንት በፊት ከመቀሌ ባለሃብቶች ጋር ውይይት ተደርጎ ባለሃብቶች ለትግራይ ክልል አስተዳዳሪዎች እስከ ወረዳ ባለስልጣናት ከሚገኙ የመቀሌ ባለሃብቶች ሲያብጠለጡሉዋቸው ታዩ። የባለሃብቶች ንግግሮች ለመጥቀስ የትግራይ ህዝብ ለፍትሃዊ ልማት አልታደለም። ፍትሃዊ የሆነ የግልጋሎት ሰጪ አካላት የሉም። ፍትህ ባለመኖሩ በትግራይ ክልል የጀመሩት እንቨስትመንት እየጣሉ ወደ ሌሎች ክልሎች ሂደዋል። ፍትሃዊ ባልሆነ የግብር አደላደል በሌሎች ክልሎች የሌለ የንግድ አሰራር በትግራይ ክልል ተፅኖ ይደረጋል። አቤቱታ ለማቅረብ ቢሮዋቸው ምንጊዜም ዝግ ነው። የመንግስት ሰራተኛው በትዕቢት ተሞልቶ በደንብ አያስተናግድም ለህዝብም አገልጋይ መሆኑ አያውቅም ወ.ዘ.ተ ብለዋል።
ከ 5/5/2006 እስከ 8/5/2006 ዓ.ም በመላው አገራችን የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ብቻ መንግስት በመደበው የአየር ትራንስፖርትና የውሎ አበል ገንዘብ ተመድቦ ወጪ ሆኖ በአቶ ስብሃት ነጋ፡ አቶ አባይ ፀሃዬ አብዛኞች የህወሓት ማ/ኮሚቴና የክልሉ አስተዳዳሪዎች ባለስልጣናት ባሉበት በፕላኔት ሆቴል ስብሰባ ተደርጎ ሰፊ ውይይት በማካሄድና በትግራይ በመንግስት የተሰሩ መንገዶች የትእምት ኩባኒያዎች እንዲሁም አንዳንድ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት አንድ የዱቄት ፋብሪካና የብረታ ብረት ድርጅት ጐበኙ። በተጨማሪ ለእንቨስትመንት የተዘጋጀ ክፍት መሬት እያዞሩ አሳዩዋቸው።ጅመረቶችና የተተው ግን አላሳዩዋቸውምም በዚሁ በተደረገው የባለሃብቶች ስብሰባ በህወሓት መሪዎች የተሰነዘሩ ወቃሽ የሆኑ ሃሳቦች ነበሩ። አብዛኞቹ ባለሃብቶች በትግራይ ሃብትን አፍስሶ እንቨስት ለማድረግ የማይቻል መሆኑ ልክ ከሳምንት በፊት የመቀሌ ባለሃብቶች እንደሰነዘሩት የባሰ ለክልሉ መንግስት ሲወቅሱ ነገር ግን አንድ አንድ አድር ባዮች ባለሃብቶች የክልሉና የዞኖች መሪዎች ቅንና ታታሪዎች ፍትሃዊያን ናቸው አሉ። ዋና ችግሩ ከወረዳ መሪዎች በታች ያሉ ናቸው ችግር የሚፈጥሩ አሉ። ችገሩ ግነ ከጭነቀላቱ ነው ያለው።
ይህ አነጋገር ጠ/ሚኒስተር መለስ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ ፖሊሳችን፡ እቅዳችን፡ መመርያችን፡ ትክክል ነበር ዋና ችግራችን ታች ያለው መዋቅር የአተገባበር ችግር ነው እየተባለ ነው የመጣው። አሁንም ያንን ደግመው እየነገሩን ናቸው። ይህ አባባል ማንም ህልና ያለው ሰው አይቀበለውም። በአገርና በክልል በዞን መሪዎች ያሉ የሚያወርዱት ፖሊሲ፡ እቅድ፡ መመርያ ባይበለሽ ንሮ ታችኛው አካል አይበላሽም ነበር። ስለዚህ የህወሓት አሰራር ከላይ ጀምሮ እስከ ታች ያለው አሰራር ከድሮ ጀምሮ ይዞት የመጣ የፖለቲካ አስተሳሰብ (አይዶሎጂ) ፖሊሲና አሰራር ከፀረ ካፒታላዊ (ባለሃብት) መስመር የመነጨ መሆኑ ነው የሚያመለክተው።
የህወሓት መሪዎች ከትጥቅ ትግል ጊዜ ጀምሮ ጠላት፡ ማኽል ሰፋሪ እያለ ወዳጅ ማን ነው ብሎ አበጥሮ የተጓዘ ኃይል ነው። ለዚሁም በግንባር ቀደምት በጠላትነት ያስቀመጣቸው መሳፍንቶች ፊዩዳሎች ካፒታልዝም (ባለሃብቶች) ቢሮክራሲዎች ካፒታሊዝም ፋሺዝም ኢምፐረያሊዝም ከፍተኛ ሙሁር የደርግ ስርዓት ነበር። በማኽል ሰፋሪነት የተሰለፉ መካከለኛ ባለሃብቶች መካከለኛ አረሶ አደር መካከለኛ ሙሁር ነበር። ይህም በተወላዋይ ጠላትነት ተጠርጣሪ ነበር። ህወሓት ወዳጅ የሚላቸው ኃይሎች ድሃ አርሶ አደር፡ ታችኛው ሙሁር፡ ወዝ አደር፡ አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ናቸው።
የህወሓት መሪዎች ላይ የጠቀስኩት የኃይሎች አሰላለፍ እስከ አሁንም የሚከተለው የኃይል አሰላለፍ አልተቀየረም። የአቤዮታዊ ዴሞክራሲ አይዶሎጂና ፖሊሲ በካፒታሊዝም ካልተቀየረ ደግሞ የህወሓት መሪዎች ከባለሃብቶች ታርቀው አብረው ሊሰሩ አይችሉም። የህወሓት ኢህአዴግ መሪዎች ግን ልክ ድመቷ ለአይጧ አዝናንታ እንደበላች ሁሉ ለባለሃብቱ አዝናንተው ለማታለልና የሚያደርጉት ሴራ አያቋርጥም። ለዚሁ መስፈርት 1ኛ ነፃ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መተግበር የግለ ሰው መብት መከበር ሲል ብቻ ነው በቀረ የህወሓት መሪዎች አይታመኑም። የአገራችን ባለሃብቶች ግን የዋሆችና ለመደባቸው በንቃት የማይታገሉና የቻይናው አቢዮታዊ ኮሞኒስት ወዳጃችን ነው ብለው ተሰብስበው የሚወያዩ ናቸው ብልጦቹ የህወሓት መሪዎች ሰብስበው ለጥቅማቸው ሲያንጨበጭቡላቸው ይውላሉ። የትግራይ ተወላጆች ባለሃብቶች ግን ላም ከአራጇ ጋር ውሃ ትጠጣለች እንደሚባለው ከአራጃቸው አቢዮታዊ ዴሞከራሲ በፕላኔት ሆቴል ሲናገሩ ሰነበቱ።
በትግራይ ህዝብ ከበሬታን ያተረፉት አንጋፋ የትግል ሰው አቶ አስገደ ገ/ስላሴ
ለመሆኑ ለትግራይ ባለሃብቶች ብቻ ሃብታቸውን እንቨስት ሊያደርጉ ለምን ተጠሩ?። ትግራይ ከኢትዮጵያ ክልሎች እንድ ናት የትግራይ ተወላጅ ባለሃብትም በዘጠኝ የአገራችን ክልሎች አገራችን ነው ብለው ሃብታቸው ሙያቸው ጉልበታቸው በማፍሰስ ለራሳቸው ተጠቅመው አገራቸው ይጠቅማሉ ይህ የሚያመለክተው ኢትዮጵያዊ እምነታቸው ነው። የህወሓት መሪዎች ግን ለሁሉ ኢትዮጵያዊ ባለሃብት ጠርተው እንደመጋበዝ ሁኔታው በጠባብ እምነት በማየት ለክልሉ ተወላጅ ብቻ መጥራቱ ለምን? ተደረገ። ይህ ሁኔታ በስተጀርባው ምን ዓይነት ሴራ ይኖረዋል? የሚለው ጥያቄ ለማንሳት አስገደደኝ። እነ አቶ ስብሀት ነጋ አቶ አባይ ፀሃዬና ብዙ የህወሓት መሪዎች ያስተባበሩት የባለሃብቶች ስብሰባ ለምን ጠባብነት ያንጃበበው ሆነ የሚለው የሁሉም በንቃት የሚመለከት የትግራይ መላው ኢትዮጵያዊ ተወላጅ ጥያቄ ሁነዋል። እኔ የሚያሰጋኝ ግን በ1968፡ በ1969ና በ1970 ዓ.ም በረሃ እያለን ትግራይ ለትግሬዎች ነች የሚል ኋላቀርና ጠባብ አስተሳሰብ እንዳይመጣ እጅጉን አስደነገጠኝ። በትግራይ ክልል ለእንቨስትመንት የተመቻቸ ሁኔታ ካለ ኦሮሞዎች፡ ሶማሌዎች፤ አማራዎች፤ ደቡብ ህዝቦች፤ ጉራጌዎ ወ.ዘ.ተ ወደ ትግራይ ክልል ለምን ጥሪ አይደረግም? ለህነድ ለቻይና ለሌሎች ጥሪ ሲደረግ። በበኩሌ ለትግራይ ተወላጅ ብቻ የተደረገ ጥሪ ፍፁም በጠባብነት የታጀበና ወደ ትግራይ የሌላ ክልል ተወላጅ ባለሃብት እንዳይገባ የሚያግድ ነው።
የትግራይ ህዝብ አሁንም የህልም እንጀራ እየበላ ነው
የትግራይ ተወላጆች ባለሃብቶች ስብሰባ ሊካሄድ ዋዜማ ለመነሳሳት ተብሎ በ5/5/2006 ዓ.ም ምሽት የኢትዮጵያ ተለቪዥን የትግርኛ ፕሮግራም ሲዋሽ ሲደሰኩር በትግራይ ክልል ባለው የእንቨስትመንት ፍሰት አንድ ሚልዮን ወጣቶች በስራ ላይ ተሰማርተዋል ብለው ተናገሩ። እኔ እምለው ነገር በትግራይ ከሁለት ዓመት በፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ የህንፃ ተቋራጮች በብዙ ሺ የሚቆጠሩ መሃንዲሶች ፎርማኖች በመቶ ሺ የህንፃ ስራ ሙያተኞች የቀን ሰራተኞች ከትግራይ ተሰደው ወደ አዲስ አበባና አዳማ ሌሎች ክልሎችና ደቡብ ሱዳን ዓረብ ተሰደው ይሰራሉ። በትግራይ ክልል ከ30 እስከ በሺ የሚቆጠሩ ሰራተኞች የነበሩዋቸው ትላልቅና አነስተኛ ህንፃ ተቋራጮች ነበሩ። በአሁኑ ጊዜ የሉም። የብረታ ብረትና የጣውላ ተቋማትም ተሰደዋል። በአሁኑ ጊዜ በትግራይ ክልል የህንፃ መሳርያ ማከፋፈያና ችርቻሮ የገበያ ልውውጥ የለም ገዢም የለም። ሌላ ቀርቶ ሲሚንቶም የሚገዛው የለም። ለዚሁ ሲሚንቶና የህንፃ መሳርያ ነጋዴዎች ምስክሮች ናቸው።
ሌሎች የንግድ ተቋማትም ተሰደዋል። በአሁኑ ጊዜ የትግራይ ክልል የንግድ ማከፋፈያና ችርቻሮ የገበያ ልውውጥ የለም ገዢም የለም። ከ10ኛ እስከ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ወጣቶች በብዙ ሺ የሚቆጠሩ በጉዳና ይገኛሉ። በኮብል ስቶን የመንገድ ስራ የተሰማሩ ተማሪዎች ጥቂት ናቸው። ብዙ ስራ ፈጥረዋል የሚባለው ትእምት ከ 60ሺ በላይ ሰራተኞች የሉትም። ብዙ የመንግስት ሰራተኞች ወደ ሌሎች ክልሎች ወይም ወደ ሱዳን አገሮች ተሰደዋል። ታድያ አንድ ሚልዮን ወጣት ስራ ተፈጥሮለታል ሲባል የት ነው የሚሰራው? ምን ዓይነት ውሸት ነው የሚያሰሙን?።
ለመሁኑ አንድ ሚልዮን ሰራተኛ በተፈጠረው የእንቨስትመንት እድል ስራ ተፈጥረዋል ሲባል አንድ ሰራተኛ አነስተኛ መካከለኛ ሚስት (ባል) ሁለት ልጆች ቢኖሩዋቸው አራት ሚልዮን ሰዎች በልተው ይኖራሉ ማለት ነው። በሌላ በኩል 300ሺ የመንግስት ሰራተኞች አሉ እነዚህም 300ሺ x4 = 1.2 ሚልዮን ሰው ነው። በድምር 5.2 ሚልዮን ሰው በልቶ ለብሶና ተምሮ ይገኛል ማለት ነው። ይህ አሃዝ የገጠር አርሶ አደር፤ የከተማ ነዋሪ የተሰደደው አይጨምርም። የትግራይ ህዝብ ግን በህዝብ ቆጠራ ጊዜ የተረጋገጠው 4.3 ሚልዮን ነበር። 5 ሚልዮን ቢሆንስ ያ የተባለው ነጭ ውሸት ነው። ለትግራይ ህዝብ የህልም እንጀራ በላ ያልኩት ለዚህ ነው። የስደቱ ጉዳይ ካነሳን ሕጋዊ አይደላቹሁም ተብለው ከሳዑዲ ዓረብያ የተባረሩ ዜጎቻችን አብዛኞቹ የትግራይ ተወላጆች ናቸው። ታድያ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያውቀው ሃቅ እያለ ውሸት ለምን አስፈለገ?። ይህ ህዝብ 39 ዓመት ሙሉ ለምን ታታልሉት አላቹሁ ለቀረቹው አጭር ዕድሜያቹሁ ለሃቅና ለህልናቹሁ ብትሰሩስ?።
በትግራይ ለእንቨስትመንት የተመቻቸ ሁኔታ አለ ተባለ
የህወሓት ባለስልጣናት ለባለሃብቶች ልባቸው ሞልተው ከተናገሩት በመቶ የሚቆጠር ሂክታር መሬት ለእንዱስትሪ ዞን ውሃ መብራት መንገድ ስልክ ወ.ዘ.ተ አለ ብለው ይደስኩሩ ነበሩ። ሃቁ ግን ለእንዱስትሪ ዋና አንቀሳቃሽ ውሃ ነው። ውሃ በተመለከተ መቀሌ ለእንዱስትሪ ግንባታ ይቅርና ሰው ለሚጠጣው ውሃ የለም። በሳምንት በወር ውሃ የምናገኝበት ሁኔታ ነው ያለው። ለአንድ በርሚል በ 30ብር ይሸጣል። በሽሬ ከተማ ህወሓት ለግንባታ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ውሃ አልተገኘም በሰሐርቲ ሳምረ ለሰውም ለእንሰሳም ውሃ የለም። ለአንድ ጀሪካን ውሃ 4 ብር ይሸጣል። ዓድዋና አክሱም ካልሆነ በትግራይ ክልል የንፁ ውሃ ተጠቃሚ አይደለም። ኢለክትሪክ ቢሆንም በሰዓታት እየተቋረጠ የኢሊክትሪክ ኃይል በሚለቅበት ጊዜ ብዙ ንብረት እየተቃጠለ ድሃ ወገን ተጎድተዋል። የስልክም እንደዚሁ ኔት ዎርክ ሁልጊዜ ይቆራረጣል።
ሌላ ባለሃብቶች መንግስት የሰራቸው መንገዶች ጎብኝተዋል ግን ደግሞ አስፋልት ተሰርቶዋል ከቤት ማራ ከተማ እስከ ውቅሮ ከተማ 100 ኪሎሚተር ከቤት ማራ እስከ አላማጣ ከተማ ከማይ ቀያሕ እስከ መኾኒ ከተማ ያለ መንገድ ፈርሰዋል ከመቀሌ ተንቤን አዲሱ አስፋልት መንገድ አሳይታቹሁ የተሰሩ መንገዶች አላሳዩዋቸውም። ይህም ማጭበርበር ነው። የህወሓት መሪዎች ያን ድብቅ ኮመኒስት የቻይና አክራሪነት የአቶ መለስ ራእይ እያላቸሁ ከሚያደነቁሩን አስተሳሰባቸውና ፖሊሳቸው በመሰረቱ በመቀየር የምዕራብ ዓለም ኢኮኖሚ ፖሊሲ ቢከተሉ ይሻል ነበር። ሌላ ብዙሃን ለውሁዳን ይመውኪ (ከግለ ሰው መብት) በመከልከል የቡድን መብት ማሰቀደሙ ትታቹሁ የግለ ሰው መብት ብታከብሩ ይመረጣል። የህወሓት መሪዎች የውስጣቹሁ አስተሳሰብና ፖሊሲ ደብቃቹሁ ለ 90 ሚልዮን የኢትዮጵያ ህዝብ ልታታልሉ አትችሉም። ስለዚህ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሉኡላዊነት የፀጥታ ጠንቅ የሆነውን ህዝብ ዜጋ በመሆኑ ማግኘት የነበረበት የገጠር ይሁን የከተማ መሬት የመንግስት ነው ማለታቹሁ ፀረ ሕገመንግስታችን ነው ህዝብም አልተቀበለውም። ስለሆነ የህወሓት መሪዎች ከመሬት ዋንነት እጃቹሁ አውጡ የፖሊስ ለውጥ ካላደረጋቹሁ በዚህች አገር ተቀባይነት የላቹሁም። ሁሉም ዓይነት ሰብአዊ መብት ነፃነት የሕግ የበላይነት ብታከብሩ ለናንተም ለአገርም ይጠቅማል።
እነ አቶ ስብሃት ብቅ ማለታቸው ለምን?
ይህ የባለሃብቶች ጉባኤ በነ አቶ ስብሃት ነጋና አቶ አባይ ፀሃዬ ማጀቡ ያስነሳብኝ ጥያቄ አለ። እነዚህ ሰዎች አዲስ ትውልድ በአቅም የተመሰረተ አገሩ መምራት እንዲችል ከማድረግ አሁንም በቃሬዛ ሁነን እንመራለን፤ ካለ እኛ ሌላ ሰው የለም እያሉን ነው። በበኩሌ ይህ ጉዳይ አሁንም ህዝብ ሁሉ ይፈትሸው። ኢትዮጵያዊ ሆናቹሁ ብታስቡ ይሻላል። የትግራይ ህዝብ ቢሆን ድሮ ከጥንቱ ኢትዮጵያዊ ዛሬም ኢትዮጵያዊ ነው። ሽወዳቹሁ የባህር በር ያሳጣቹሁ ሽወዳቹሁ ሉኡላዊነት ሃገር የቆረሳቹሁ ዓይነት የሚታለል ህዝብ አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ነው እናንተ በምትፈልጉት አይራራቅም አንድነቱን ነው የሚያሰቀድም።
በመጨረሻ የትግራይ ባለሃቶች አትታለሉ፤ የሰለጠኑ አገሮች ባለሃብቶች (ካፒታሊስቶች) የመንግስታቸው የማይመቻቸው ፖሊሲ በተፅኖ ያሰቀይራሉ። ለመደባቸው ንቁ ናቸው። የሃገራችን ባለሃብቶችም እንቢ ለመጉዚታዊ አሰራር ብላቹሁ ድመቷ ለአይጧ አዝናንታ እንደበላቻት የህወሓት መሪዎችም እያዝናኑ እንዳይበሉዋቹሁ ጠንቀቅ በሉ። የብሄራዊ ባለሀብት ቀንደኛ ጠለት የህወሓት ኢህአዴግ መንግስት ነው እንድታውቁት።
ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com
February 2, 2014
No comments:
Post a Comment