Monday, June 30, 2014

የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌ በጁን 29, 2014 መደበኛ ስብሰባውን አካሄደ

ሔለን ንጉሤ/ ከኖርዌ

የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌ እ.ኤ.አ በጁን 29, 2014 ከተለያዩ የኖርዌ ከተሞች በመጡና በኦሎ የሚኖሩ በርካታ አባላቶቹ በተገኙበት መደበኛ ስብሰባውን በተሳካ ሁኔታ አከናወነ።

የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ በአምባገነኑ የወያኔ ስርዓት  በግፍ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማስደረግ ፕሮግራሙን ያስጀመሩ ሲሆን በመቀጠል የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌ ዋና ሊ/ቀ መንበር የመግቢያ ንግግር አሰምተዋል። በንግግራቸውም የድርጅቱን አመሰራረትና አላማውን ጨምረው በዝርዝር በማስረዳት የድርጅቱ አላማ የጋራ ሰላምና መግባባት ቀናነት ያለበት መሆኑን በመጠቆም የምንታገልለትን ሀገራዊ ራዕይ ለማስፈፀምና የተጫነብንን የድህነት ቀንበር ለመስበር የምንችለው አንድ ሆነን ስንታገል ብቻ መሆኑ በማስገንዘብ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለአባላቱ አቅርበዋል። ቀጥሎም የድርጅቱ ዋና ፀኃፊ የድርጅቱን አጠቃላይ የስድስት ወራት የሥራ ክንውን ሪፓርት በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌ ለፍትህ ለነፃነትና ለዲሞክራሲ ከሚታገሉ በውጪ ካሉ ድርጅቶች ግንባር ቀደም መሆኑንም ጠቁመዋል።

በመቀጠል የድርጅት ጉዳይ ኃላፊው የስድስት ወር ሪፓርታቸውን በዝርዝር ሲያቀርቡ በእቅድ የተያዙና የተከናወኑ ስራዎችን እንዲሁም በስራ ላይ ያጋጠሙ ችግሮችንና መፍትሄዎቻቸውን ጨምረው አስረድተዋል። በተለይ ቅርንጫፎችን በማስፋት የአባላት ምልመላን በተመለከተም ከእቅድ በላይ አባላትን መመልመል እንደተቻለ ተናግረዋል። በድርጅት ጉዳይ ስር የተዋቀሩ ንዑሳን ኮሚቴዎችም ያከናወኑትን ስራ በሪፓርታቸው አካተዋል። ባጠቃላይ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊው የተሰሩ ስራዎችን በምስል በማስደገፍ በፓወርፓይንት ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለአባላቱ በማቅረብ የንዑሳን ኮሜቴና ከየቅርንጫፍ ፅ/ቤቱ የመጡ ተወካዮችንም በመጋበዝ እራሳቸውን ለአባላት እንዲያስተዋውቁና ወደፊት ለመስራት ያሰቧቸውን ስራዎች በአጭሩ እንዲያስረዱ  አድርገዋል።
ከዚያም የድርጅቱ የሂሳብ ሪፓርት በሂሳብ ሹሟ የቀረበ ሲሆን በድርጅቱ ኦዲት ክፍልም የኦዲት ሪፓርት ቀርቧል። ከዚያም የምንደግፋቸውን ድርጅቶች አስመልክቶ በድርጅቱ የተወከሉ የድርጅቱ አባላት የሰማያዊ ፓርቲን፣ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን እንዲሁም የግንቦት7 የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄን የገመገሙበትን ሪፓርት በየተራ ለአባላቱ ያቀረቡ ሲሆን አባላቱም ሪፓርቱን ካደመጡና ከተወያዩ በኋላ በቀጣይ ሶስቱንም ድርጅቶች ለመደገፍ መስማማታቸውን ገልፀዋል።

በስብሰባው መሀል የሰማያዊ ፓርቲ ሊ/መንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት በስልክ በመግባት ሰማያዊ ፓርቲ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ሐገር በሰላማዊ መንገድ ትግሉን ከሚያግዙ ድርጅቶች ጋር ትኩረት በመስጠት እየሰራ መሆኑንና ከዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌ ጋር ስራ ለመስራት በፓርቲው በኩል ህጋዊ ውክልና ለድርጅቱ መስጠታቸውን ገልፀው በተጨማሪ የሰማያዊ ፓርቲ ባዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ እለት ከዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌ የገንዘብ ልገሳ እንደተደረገላቸው አረጋግጠዋል። ኢንጅነሩ ሲናገሩ በቀጣይም ትግሉን ወደፊት የሚያራምድ ስራ በጋራ እንዲሰራና ትግል ብዙ መስዋእትነት የሚጠይቅ መውደቅ መነሳት ያለበት እልህ አስጨራሽ በመሆኑ ጠንክረን በጋራ እንድንሰራ ጥሪያቸውን በማቅረብ መልክታቸውን
አስተላልፈዋል።


በመቀጠል የአባላት የውይይት ተደርጎ የድርጅቱ ሊቀመንበር የውይይት ጊዜውን በመምራት ከአባላት የተነሱ ጥያቄዎችን በተገቢው መንገድ ምላሽ በመስጠት የተለያዩ ገንቢ አስተያየቶችንም ከአባላት ተቀብለዋል። በመጨረሻም የድርጅቱ ም/ሊቀመንበር የመዝጊያ ንግግር አሰምተው ስብሰባው በተያዘለት ሰዓት በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!

No comments:

Post a Comment