Thursday, June 5, 2014

ጅቡቲን ውሃ ጠማት አለ /TPLF/

ሔለን ንጉሴ/ከኖርዌ

ገዢው ፓርቲ ወያኔ ጅቡቲን ውሃ ጠማት እሷን ከሚጠማት እኛን ይጥማን በሚል ይመስላል ጅቡቲ የኢትዮጵያ ድንበር አቋርጣ ሐገር ውስጥ ድረስ ገብታ ከድሬደዋ ሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሽንሌ የከርሰምድር ንፁህ ውሃ በነፃ አውጥታ እንድትጠጣ መሬት ለመስጠት የሚያስችል ረቂቅ ወጥቶ በምክር ቤት ለውይይት የቀረበ መሆኑ ተሰማ። የራስዋ ሲያርባት የሰው ታማስላለች ይላሉ ይሄ ነው! ህዝባችን መቼ ውሃ ጠጣና ነው ለጎረቤት ማሰብ የተጀመረው ምላሹን ለራሳችን እንተወውና

በሐገራችን ቁጥር አንድ ችግር የውሃ እጥረት መሆኑ እየታወቀ ህዝብ በውሃ እጥረት ምክንያት ከፍተኛ ችግር ውስጥ መውደቁንና ውሃ በመሃል አዲስ አበባ ከተማ ሳይቀር በመጥፋቱ ዜጎች ውሃ ፍለጋ ከሰፈር ሰፈር እየተንከራተቱ መሆኑንና ህዝባችን በውሃ ችግር እየተሰቃየ እያለ ይህንን ችግር መፍታት አቅቷቸው ጅቡቲን ውሃ ጠማት የጅቡቲ ህዝብ የንፁህ ውሃ መጠጥ ያስፈልገዋል ብለው በምክር ቤት ውይይት መጀመራቸው እጅግ በጣም ያስገርማል። ወያኔ መሬት ቆርሶ ለጅቡቲ ውሃ ትጠጣ ብሎ ለሰላሳ አመታት የሚቆይ ኮንትራት ፈርሞ እንደሚሰጥ የቀረበው እረቂቅ የሚገልፅ ቢሆንም በአንፃሩ ኢትዮጵያ ይህንን መሬት በመስጠቷ በምትኩ የምታገኘው ጥቅም እንዳለ ቢጠየቅም ምላሹ የፓለቲካ ጥቅም እንዳለው ብቻ ከመናገር ውጪ ዝርዝሩን ለምክር ቤቱ ማስረዳት አልቻሉም። ጅቡቲ ይህንን መሬት ከኢትዮጵያ ለሰላሳ አመት ኮንትራት ወስዳ ህዝቦችዋን ንፁህ ውሃ ስታጠጣ ጅቡቲን ውሃ ለማጠጣት ከስፍራው የሚፈናቀሉ ዜጎቻችንስ እጣ ፋንታ ምን ሊሆን እንደሚችል ሁላችንም መገመት እንችላለን በየቦታው በልማት ሰበብ ከተፈናቀሉት ካለፉት ተፈናቃዮች ተሞክሮ አለንና በከፍተኛ ሁኔታ ሊታሰብበት ይገባል።

  
ጅቡቲ እንደሚታወው ከወደብ ኪራይ ከኢትዮጵያ በአመት አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር እንደምታገኝ ይታወቃል። ከዚህ በተጨማሪም በሐገራችን በከተሞች ሳይቀር የመብራት እጥረት  በከፍተኛ ሁኔት እየታየ ባለበት ሁኔታ ጅቡቲ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ታገኛለች። ኢትዮጵያ ከጅቡቲ የምታገኘው ምንም አይነት ጥቅም ሳይኖር ለምን የጅቡቲ ጉዳይ እንዲህ እንዳሳሰባትና ወያኔ በዚህ ዙሪያ ያለው ድብቅ የፓለቲካ አጀንዳ ምን እንደሆነ በግልፅ ባያሳውቀንም መገመት ግን እንችላለን። በሌላ መልኩ ወያኔ በማንአለብኝነት ሐገሪቷን እየሸነሸነ መሸጡን መቀጠሉን እያሳየን ነው ትላንት 17 ቀበሌዎችን ለሱዳን አሳልፎ በመስጠቱ የተፈናቀሉ ዜጎች ምን ያህል እንደተቸገሩ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ሆኖ ሳለ ዛሬ ደግሞ ጅቡቲ ሐገራችን ገብታ ውሃ እንድትጠጣ መሬት ተሰጣት ነገስ ማን ይሆን ባለተራው!!

ለማንኛውም ወያኔ ሐገሪቱን ሸንሽኖ ከመጨረሱ በፊት ሁላችንም ልናስብበት ይገባል ሐገር የማዳን ስራ መስራት ያለብን ወሳኝ ጊዜ ላይ እንገኛለን በመሆኑም እኛ ውሃ እየጠማን ለጅቡቲ ውሃ አንሰጥም ብለን ተቃውሟችንን ማሰማት መቻል አለብን ከሀገር ይልቅ ስለሌሎች የሚቆረቆር ወራሪ በመሆኑ ይህን ብልሹ አስተዳደር ተባብረን ከሐገራችን ማባረር መቻል አለብን እላለሁ።

ኢትዮጵያ ሐገራችንን እግዚአብሄር ይባርክልን

No comments:

Post a Comment