Saturday, July 5, 2014

አሳዛኝ ዜና በባህል ዘፈኖቹ የሚታወቀው አርቲስት ዳምጠው አየለ ከዚህ አለም በሞት ተለየ



በአማርኛ ባህላዊ ዘፈኖቹ የምናደንቀው ተወዳጁ ድምፃዊ ዳምጠው‬ ‪‎አየለ ከዚህ አለም በሞት ተለየ። በባህላዊ አዘፋፈኑ ከአንጋፋዎቹ ተርታ የሚመደበው አርቲስት ዳምጠው አየለ በስደት ይኖርበት በነበረው ኖርዌይ ከስምንት አመት በላይ የኖረ ሲሆን በኖርዌ በሚደረጉ በተለያዩ ሃገራዊ ጉዳዮችና ባህላችንን በተመለከተ በሙያው ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክትዋል። ዳምጠው ሐገሩን ወዳድ በመሆኑ በተለይ የወያኔን መንግስት ለመጣል በሚደረግ እንቅስቃሴ ላይ ሁሉ ግንባር ቀደም ሆኖ በሙያው ሲያገለግል የነበረ ሲሆን በኖርዌ ቆይታው በመልካምነቱና በሃገር ወዳድነቱ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ክብር ያለውና ተወዳጅ አባት ነበረ። አርቲስት ዳምጠው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደረሰበት የጤና መታወክ በኖርዌይ ሀገር ሲታከም ቆይቶ  ህመሙ ሲጠናበት ወደ ሃገር ቤት በመሄድ ከቤተሰቡ ጋር ለመገናኘት በመወሰኑ በኖርዌ የሚገኘው የኢትዮጵያ ማህበርና በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያውንን በማሰባሰብ በርካታ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት ደማቅና የተሳካ የክብር ሽኝት ዝግጅት ተደርጎለት ወደሃገሩ ተሸኝቶ ከቤተሰቦቹ ጋር ለመገናኘት በቅትዋል። ነገር ግን ህመሙ ስር የሰደደ በመሆኑ በቤተሰቦቹ መኖሪያ ቤት በሐገሩ ምድር  ሰኔ 27, 2006 ዓ.ም /July 4, 2014/ ከዚህ አለም በሞት ተለይቶናል። ለአርቲስት ዳምጠው አየለ ቤተሰቦችና ለአድናቂዎቹ በሙሉ እግዚአብሄር መፅናናትን ይስጥልን። 
ዳምጠው እንወድሃለን

No comments:

Post a Comment