Saturday, September 6, 2014

መነበብ ያለበት ስለ ሃብታሙ የተጻፈ (ዘሪሁን ሙሉጌታ) ክፍል 1

እሁድ (ሐምሌ 1 ቀን 2004 ዓ.ም) በአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ጽ/ቤት ውስጥ የ“አዲሱ ትውልድ ተልዕኮ” በሚል ርዕስ ወጣት ሀብታሙ አያሌውን ገብዘዉት ነበር፡፡ ሀብታሙን በአካል ያየሁት ያኔ ነበር፡፡ ከሀብታሙ ጋር በደንብ የተዋወቅነው ከዚህ ዘገባ በኀላ ነበር፡፡ ሀብታሙን ስሞኑን ሳስታውስው፣ ያኔ በስንደቅ ጋዜጣ ላይ የዘገብኩትን መለስ ብየ አየሁ። እስቲ በጋራ እናነብው ፡፡
ክፍል 1 – የዛሬው ወጣት ትግል የሚመዘነው የራሱን የመከራ ዘመን በማሳጠር ብቻ ሳይሆን (ሃብታሙ አይሌው)
የሀብታሙ አቅርቦት የነበረው ሀሳብ በዋናነት በሦስት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር። የመጀመሪያው የዚህ ዘመን ትውልድ የፖለቲካ ፍዘት፣ ድንዛዜ፣ ቁዘማና ትካዜ ላይ ሲሆን፤ በሁለተኝነት ታሪክን ማረም እንዲሁም በሦስተኝነት የኢትዮጵያ አንድነት ግንባታ የሚሉ ነበሩ።
ወጣት ሐብታሙ ለውይይት የመረጣቸው ሦስቱ ጉዳዮች በዋናነት የዚህ ዘመን ትውልድ ከኋላቸው ትውልድ በተለየ ሁኔታ ያጣቸው ጉዳዮች መኖራቸውን በሰፊው የሚዘረዝር ነበር። በወጣት ሐብታሙ ገለፃ ኋለኛው ትውልድ ለዚህ ትውልድ ወደፊት መወርወር አይነተኛ ግብአት በመሆኑ፤ የኋላኛውን ዘመን ሕፀፅ እያረሙ፣ በጎ ጎኑን እያጎሉ የሀገርን አንድነት ማስቀጠሉ ተገቢም አስፈላጊም የመሆኑን ጉዳይ በሰፊው አብራርቷል። በዚህ ረገድ የድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮን) ስንኝ በማውሳት ለንግግሩ በግብአትነት ተጠቅሞበታል። ድምፃዊ ቴዎድሮስ የትውልድን የታሪክ ቅብብሎሽ፤ “ሳይራመድ በታሪክ ምንጣፍ ሰው አይደርስም ከዛሬ ደጃፍ” ማለቱን በማስታወስ አዲሱ ትውልድ ከፖለቲካ መፋዘዝ፣ ከጓሮ ትካዜና ቁዘማ እንዲሁም በአልባሌ ስሜቶች ከመደንዘዝ መውጣት እንዳለበት በሰፊው አውስቷል።
እኔም ከሦስቱ ርዕሰ ጉዳዮች የወጣቱ የፖለቲካ ፍዘትና ታሪክን በአጭሩ ለይተን ለጋዜጣ በሚመች መልኩ አቅርቤው ነበር። ትውልዱ ከፖለቲካ ፍዘት እንዴት ይወጣል?
በወጣት ሀብታሙ እምነት በዚህ ዘመን ያለው ወጣት በፖለቲካ ፈዟል፣ ደንዝዟል፣ ከደርግ ጊዜ በባሰም የዚህ ዘመን ወጣት ስለፖለቲካ የማይጠይቅ፣ የማይናገር፣ የማይፅፍ ፍዝዝ ያለ ትውልድ አድርጎ መስሎታል። የዚህን ምክንያት ከመዘርዘሩም በፊት በደርግ ጊዜ ተነግሯል ያለውን ምሳሌ አቅርቧል።
“ነገሩ በደርግ ጊዜ የሆነ ነው። ሁሉም በየዘመኑ የተለያዩ የፖለቲካ ቋንቋዎች አሉ። በደርግ ጊዜም የገዢ መደብ፣ የሰራተኛ መደብ፣ የአሰሪ መደብ ወዘተ የሚሉ የፖለቲካ አገላለጾች ነበሩ። እናም በአንድ ወቅት ከአንድ ቤተሰብ ውስጥ የሚኖር ልጅ አባቱን የገዢ መደብ፣ የአሰሪ መደብ፣ የሰራተኛ መደብ ምን ማለት ነው ብሎ ይጠይቃል። አባትም፤ ስለ መደብ ስርዓት ለልጁ እንዴት አድርጎ ማስረዳት እንደሚችል ካሰበ በኋላ፤ በቀላል ምሳሌ የገዢ መደብ ማለት እኔ ነኝ፣ የአሰሪ መደብ ደግሞ እናትህ ናት፣ የሰራተኛ መደብ ሰራተኛችን ናት ብሎ ዘርዝሮ ነገረው። ልጁ እኔስ ከየትኛው ነው የምመደበው አለው። የእርሱም ታናሽስ ከየትኛው ይመደባል ሲል ጠየቀው። አባትም አንተ ሕዝብን ነው የምትወክለው፣ ታናሽህ ደግሞ መጪውን ትውልድ ነው አለው። ልጅ በጉዳዩ ላይ ካሰበ በኋላ በአንድ እኩለ ሌሊት ይነሳና ገዢ መደቦች ምን እየሰሩ ነው ብሎ መጀመሪያ ገዢው መደብ ወደተኛበት ሄደ፤ አባቱ ከተኛበት አልጋ ላይ የለም (ገዢው መደብ የለም)። እናቱ (አሰሪ መደብ) በጣም የጦፈ እንቅልፍ ላይ ነበረች (ስለዚህ አሰሪው መደብ ተኝቷል)። ቀጠለና ወደሰራተኛው መደብ (ሰራተኛዋ ጋ ሄደ) በሩንም በዝግታ ሲከፍተው ሰራተኛዋ ተኝታለች። ነገር ግን አንድ አዲስ ነገር አየ። በቦታው ያልነበረው ገዢ መደብ ከሰራተኛዋ ጋር ነበር።
ልጁም ይሄንን ተመለከተና አንድ ነገር ታዘበ። ይህም ገዢው መደብ ሰራተኛው ላይ መሆኑን ።ከዛም ቀጠለና ታናሹ ወንድሙ ወደተኛበት ሄደ፤ ሄዶም ሲያየው ከእንቅልፉ ነቅቶ ምርር ብሎ ያለቅስ ነበር። ለጁም ይሄንን ሁሉ ካየ በኋላ ተነስቶ ተኛ።

ጠዋት ተነስቶ ለአባቱ “ስለመደብ ፖለቲካ” የነገርከኝ በሚገባ ግልፅ ሆኖልኛል አለው። አባትም ደነገጠ፤ “ምን ገባህ” ብሎ ሲጠይቀው ገዢው መደብ የሰራተኛውን መደብ ይጨቁናል። አሰሪው መደብ የጦፈ እንቅልፍ ተኝቷል። መጪው ትውልድ ያለቅሳል። ስለዚህ “የመደብ ፖለቲካ” ገብቶኛል አለው።
“ልጁ በሕዝብ ይመስላል” ያለው ወጣት ሀብታሙ የፖለቲካ ፍዘት በዚህ መልኩ ሊመሰል ይችላል ብሏል። አሁን ያለው የፖለቲካ ከባቢ አየር ከላይ ከተጠቀሰው ምሳሌ ብዙም አይርቅም ብሏል። ይህ ትውልድ በዋናነት “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” እንደ ጥላ ሞት የፖለቲካ ፍዘት ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል፣ የሚለው ወጣት ሀብታሙ፤ ትውልዱ ከዚህ የፖለቲካ ፍዘት በመውጣት የኢትዮጵያን መፃኢ ዕድል ከመወሰን አንፃር የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መውጣት ይገባዋል ብሏል። “የዛሬው ወጣት ትግል የሚመዘነው የራሱን የመከራ ዘመን በማሳጠር ብቻ ሳይሆን ያለፈው ትውልድ በብዙ ፈተና እና መከራ ያቆያትን ጥንታዊቷንና ታላቋን ኢትዮጵያ ለመጪው ትውልድ ከማቆየት አንፃር መመዘን አለበት” ያለው ወጣት ሀብታሙ የአንድ ትውልድ ተልዕኮ ለራሱ የምትመች ሀገርን ብቻ በመፍጠር ታጥሮ መቀመጥ የለበትም ብሏል።
በወጣት ሀብታሙ ማብራሪያ “የፖለቲካ ፍዘትን” የሚፈጥሩት ገዢዎች ናቸው። ገዢዎች የፖለቲካ ፍዘትን የሚፈጥሩት የሕዝብ ፍላጎትን ወደጎን በማለት የስልጣን ዕድሜአቸውን ለማራዘም ሲሉ ነው። ዜጐችም ከፖለቲካ የእሳት ነበልባል እንዲርቁ በማድረግ “እኔ ከፖለቲካ ሩቅ ነኝ” እንዲሉ በማድረግ እንዲርቁ ያደርጋሉ ብሏል። እናም ገዢው በሚፈልገው መንገድ የሚመራ ሀገር የፖለቲካ ፍዘት እንደ ስልት ይተገብራል ያለው ወጣት ሀብታሙ በሕዝብ ፍላጎት የሚመራ ሀገር ውስጥ የፖለቲካ ፍዘት እንደማይኖርም አመልክቷል።
በኢትዮጵያም ደረጃ የፖለቲካ ፍዘት እንደ ስልት እየተተገበረ በመሆኑም ወጣት ሀብታሙ በሰፊው አስረድቷል። የዛሬይቱ ኢትዮጵያ መሪዎችም በፖለቲካ አፍዝዞ የመግዛት የአረጀ ስልትና ዘለአለማዊ ስልጣን ግንባታ ፍላጎት አልፈው ኢትዮጵያን በአብዮታዊ ስርዓት ብቻ በመለካት መወሰናቸውን ገልጿል።
“ዛሬ በሀገራችን ዋነኛ የፖለቲካ ፍዘት መፍጠሪያ መንገድ ሆኖ የምናየው ኢትዮጵያዊነትን በአብዮታዊነት በመተካት ነው። አብዮታዊነት የገዢው መደብ ስርዓት ሲሆን ኢትዮጵያዊነት ግን ሰው ከመሆናችን ጋር ተያይዞ ለዘመናት ተሻግሮ የመጣ ነገር ነው። ኢትዮጵያዊነት የሦስት ሺህ ዘመን ታሪክ ነው። አብዮታዊነት የሃያና የሰላሳ ዓመት ታሪክ ነው። ኢትዮጵያን በሃያና ሰላሳ ዓመት ታሪክ ውስጥ ለክተን ኢትዮጵያ ይህቺ ናት እየተባልን፣ የሦስት ሺህ ዘመን ታሪክን በመቶ እየለወጡብን ነው” ሲል ወጣት ሀብታሙ ተናግሯል። ኢትዮጵያ የሦሰት ሺህ ዘመን ታሪክ እንዳላት እነ ሆሜርን እነ ስትራቮን ሌሎች የታሪክ ተመራማሪዎችንና ፖለቲከኞችን በመጠቃቀስ ታሪካዊውን ሂደት በሰፊው አብራርቷል። ማንኛውም የውጪ ሀገር ታሪክ ተመራማሪ ኢትዮጵያን “The oldest and Independent Country” በማለት ይገልፁታል ያለው ወጣት ሀብታሙ “The Oldest የሚባለው የመቶ ዓመት ታሪክ ነው ወይ?” ሲል ለታዳሚዎች የምፀት ጥያቄ አቅርቧል። የአንድን ሀገር ታሪክ የማስረዘምና የማሳጠሩ ምስጢር ገዢዎች በሚያመጡት የአገዛዝ ስርዓት ችግር መሆኑን ወጣት ሀብታሙ አብራርቷል። በአሁኑ ጊዜም ኢትዮጵያዊነትን በአብዮታዊነት የሚተካ አዲስ ስርዓት ለመተካት ጥረት እየተደረገ ነው ብሏል።

No comments:

Post a Comment