Monday, September 23, 2013

ወያኔ የሰላማዊ ትግሎችን እያደናቀፈ የትግሉን አቅጣጫ ሊያስቀይር ያሰበ ይመስላል!!


 September 23, 2013
ሔለን ንጉሴ/ኖርዌ

ላለፉት ሃያ ሁለት አመታት ብሔርንና ጎሳን መሰረት ባደረገው የወያኔ ከፋፋይ ሥርዓት የኢትዮጵያዊ አንድነትን በማደብዘዝና የጋራ ህብረ ቀለምና እሴቶችን ወደ ቡድንተኛና ጎጠኝነት በመቀየር፣ በሀማኖ በጎሳው ተከባሮና ተፋቅሮ ለዘመናት አብሮ የኖረውን ህዝብ የነሱን የስልጣን ዘመን ለማራዘም በታሰበ ሴራ ህዝቡን ለማጋጨት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ለሃያሁለት አመታት ቢቆዩም እንዳልተሳካላቸው ይታወቃል። ወደፊትም እንደማይሳካላቸው እርግጠኛ ነኝ።
እንግዲህ ወደ ሃገራችን ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታዎች እናምራና ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ብቻ በሃገራችን የተከሰቱትን ክስተቶች ባጭሩ ለመግለጽና ለመዳሰስ ያህል በቅርቡ ተቋቁሞ ታላቅ ታሪክ ማስመዝገቡ የተረጋገጠለት ሰማያዊ ፓርቲ ያዘጋጀው ሰላማዊ ሰልፍና አጀንዳዎቹ እንዲሁም በአንፃሩ የወያኔ መንግስት የሰላማዊ ትግሉን አቅጣጫ ለማስቀየር በሰማያዊ ፓርቲ ላይ ብቻ እያደረስ ያለው ጫናን ባጭሩ ስንመለከተው ሃገራችን በማን እየተመራችና ወዴት እየሄደች እንዳለች ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል
በወጣት አመራሮች የተገነባውና በርካታ ሴት አባላት እንዳሉት የሚነገርለት ሰማያዊ ፓርቲ በጠራው ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ በዋናነት የተገኘው ድል በሃገራችን ውስጥ ላለፉት ስምንት አመታት ተጋርዶ ያለው የፍርሃት ደመና መግፈፉ ነው። የቀድሞው የወያኔ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባስተላለፉት ትዕዛዝ በ1997 ዓ.ም በተደረገው ተቃውሞ ዜጎችን አልመው በሚተኩሱ አጋዚ ታማኝ የህወሃት ታጣቂዎች ደረትና አናታቸው እየተመቱ በርካታ ንፁሃን ዜጎቻችን እንዲገደሉ ከተደረገ በኋላ አቶ መለስ በቴሌቪዢን መስኮት ብቅ ብለው ጋዜጠኛም ሳያስፈልጋቸው ከዛሬ ጀምሮ አሉ ማንኛው ሰው የተቃውሞም ሆነ የሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ እንደማይችል ደነገጉ ከዚያ ወዲያ የተቃውሞ ሰልፍ በሃገራችን የማይታሰብ ሆኖ ላላፉት ስምንት ዓመታት መቆየቱ የሚታወስ ነው።
ይህንን ለብዙ አመታት ተዘግቶ የነበረውን በር ወለል አድርጎ የከፈተው ሰማያዊ ፓርቲ ከህዝብ ባገኘው ከፍተኛ ድጋፍ በሚዝያ 25 ቀን 2005 ዓ.ም አዲስ አበባን የተቃውሞ ጎርፍ አጎረፈባት። ሰላማዊ ሰልፉ በብዙ አስር ሺዎች በሚቆጠሩ ታዳሚዎች የተሳተፉበት ሰላማዊና የተሳካ እንደነበርም ኢህአዴግ ራሱ በወቅቱ አልሸሸገም ነበር። ህዝቡም ተቃውሞውንና ጥያቄዎቹን በሰለጠነ መንገድ ገልጾ ለጥያቄዎቹም መንግስት በሶስት ወር ጊዜ መልስ እንዲሰጥ ቀጠሮ ሰጥቶ ነገር ግን መንግስት ለጥያቄዎቹ መልሱን በተገቢው ጊዜ የማይሰጥ ከሆነ ሰልፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በማሳሰብ ነበር ሰልፉን ያጠናቀቀው።

በአንፃሩ አትነሳም ወይ አትነሳም ወይ የሚል መፈክር ማውረድና የታሰሩ እስረኞች እንዲፈቱ መጠየቅ ህግን መተላለፍና የፍርድ ሂደት ላይ ተጽዕኖ መፍጠር ነው በሚል በአቶ ሽመልስ ከማል የሰማያዊ ፓርቲን እንደመወንጀል የሚቃጣ ንግግር ተደረገ። ትንሽ ቆይተውም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የተፈናቀሉ አማሮች ሰማያዊ ፓርቲ በስማችን አይነግድ የሚል ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ ብሎ በዜና ማሰራጫ የልጆች ጨዋታ አይነት ነገር ማቅረባቸውም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ሆኖ አልፏል።
በወጣት አመራሮች የተገነባው የሰማያዊ ፓርቲ አላማ የዜጎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ የተከበሩባት፤ ለሕዝብ ፍላጎት መሟላት በኃላፊነትና በተጠያቂነት መንፈስ የሚሰራ መልካም አስተዳደርና የህግ የበላይነት የተረጋገጠባት፤ የኢኮኖሚና ማሕበራዊ ብልፅግና የሰፈነባት፤ ለዜጎቿ ሁሉ አለኝታና መኩሪያ የሆነች፤ ለዓለም ሕዝብ መልካም ግንኙነት የበኩሏን አስተዋፅዖ የምታደርግ ኢትዮጵያን ማየት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ 

ወያኔ የሰማያዊ ፓርቲ ያቀረበውን ጥያቄ አንዱንም ሳይመልስ ሶስት ወራት ተቆጠሩ ፓርቲውም ጥያቄው ስላልተመለሰ በድጋሚ ለነሃሴ 25 ቀን 2013 ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ጠራ። የወያኔ መንግስት ይህንን ሰላማዊ ሰልፍ ታጣቂዎችን ቢሯቸው ድረስ በመላክ ለሰላማዊ ሰልፉ ያዘጋጁትን ቁሳቁስ ሁሉ በመዝረፍና የፓርቲው አመራሮችን ጨምሮ አባላቶችን ከቢሮ ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመውሰድ ሴቶችን ሳይቀር በአሸዋ ላይ በማንበርከክና በጭቃ ላይ እያንከባለሉ በመደብደብ ከሰው የማይጠበቅ ኢሰብአዊ ድርጊት በገዛ ሃገራቸው ተፈፀመባቸው ሰላማዊ ሰልፋቸውም በዚህ ሁኔታ በማፍያ የወያኔ መንግስት ተደናቀፈ፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ ይህንን ሁሉ መከራና እንግልት በመቋቋም ተስፋ ሳይቆርጡ ዳግም ለመስከረም 12 ቀን 2013 አ.ም ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ጠራ አሁንም ይህንን ሰላማዊ ሰልፍ እንደገና ለማደናቀፍ ሰልፈኞቹ ያሰቡበት ቦታ ደርሰው ድምፃቸውን እንዳያሰሙና ሌሎች ሰዎችም ወደ ሰልፉ እንዳይቀላቀሉ ፖሊሶች የሰልፉን መንገድ ዘግተው ሰልፉን አቆሙት እንግዲህ ወያኔ መንገዶች ሁሉ ሳይቀር ለተቃዋሚዎች ዝግ መሆናቸውንና እነርሱ በፈቀዱትና በፈለጉት መንገድ ብቻ ሁሉም መከናወን እንዳለት ያሳዩበት ሰላማዊ ሰልፍ ነበረ ለማለት ይቻላል፡፡ ሰልፈኞቹም በቆሙበት ቦታ ሆነው የፍትህ ያለ፤ የነፃነት ያለ እኩልነት እንፈልጋለን፤ የአስተዳደር ለውጥ እንፈልጋለን በማለትና የተለያዩ መፈክሮችን በማሰማት ስልፉን በሰላም አጠናቀቁ። 

እንግዲህ በሐገራችን ኢትዮጵያ ህዝብ በገዛሃገሩ እንደሰባተኛ ዜጋ ከተቆጠረና ሐሳብን በነፃነት የመናገር በጽሁፍ የመግለጽ መብት ከተገደበ፤ ህዝብ ድምፁን በሰላማዊ ሰልፍ ማሰማት ካልቻለ፤ ህዝቡ ከፍተኛ ወደ ሆነ የድህነት አዘቅት ውስጥ ከወረደ፤ ምሁራን ከሃገር እየተሰደዱ ከወጡ፤ ሴቶች ልጆች ለባርነት በየአረብ ሃገራቱ ከተሸጡ፤ ህፃናት ልጆች በጉዲፈቻ ስም እንደሸቀጥ ዋጋ ተተምኖላቸው እየተሸጡ ያሉበት፤ ዜጎች የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ በመሆናቸው ብቻ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ሜዳ ላይ የተጣሉበት፤ወጣት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በሱዳን ሊቢያ እየተሰደዱ ህይወታቸውን ያጡበት እንዲሁም የየሃገሩን እስርቤት ያጣበቡበት ባጠቃላይ በሃገራችን ህዝብ የተዋረደበትና የህግ የበላይነት የጠፋበት ዜጎች መንግስት አልባ ሆነው መኖር ከጀመሩ ከሁለት አስርት አመታት በላይ ተቆጠሩ።
የወያኔ መንግስት የሰላማዊ ትግል አማራጮችን ሁሉ እየዘጋ የተቃወመውን አሸባሪ፤ ልማት አደናቃፊ፤ ግንቦት 7 እያለ ንፁሃን ዜጎችን እስር ቤት በማጎር ማን አለብኝነቱን ገፍቶበታል ህዝቡም የመንግስት ለውጥ እንደሚፈልግ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ድምፁን እያሰማ ይገኛል፡፡ ለዚህም በቅርብ የሰማያዊ ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍን እንደ አብይ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን፡፡

በመሆኑም የሰላማዊ ትግሉ አማራጭ ላለፉት ሃያ ሁለት አመታት ተሞክሮ ያልተሳካ በመሆኑ ከዚህ በኋላ ወያኔ በሃገራችን ህልውና ላይ እያላገጠ የሃገሪቷን ሃብትና ንብረት እየዘረፈ ሌላ የስልጣን ዘመን እንዲጨምር እድል መስጠት የለብንም። ሃገራችን እንደ ሃገር እንድትቀጥል ከፈለግን የመንግስት ለውጥ ግድ ይላል!!! የወያኔን መንግስት በአስቸኳይ ለመጣል ያለውን ሁሉ አማራጭ በመጠቀም ትግሉን ወደ ተግባር የለወጡ ወገኖቻችንን አቅም በፍጥነት በማሳደግ የቻልንም በመቀላቀል ሁላቸንም እንደዜጋ ሃገር የማዳን ስራ በመስራት የሚጠበቅብንን ሁሉ መስዋእትነት ከፍለን ሃገራችንን ከወያኔ አገዛዝ ነፃ እንድናወጣ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ
እግዚአብሄር ሃገራችንን ይባርክልን

No comments:

Post a Comment