የሰው ልጅ የብሶቱ መጠን
ከጥግ ሲደርስ አዳማጭ፤ አማራጭ ሲያጣ፤ ግራ ሲገባው ሁሉም ነገር ከአቅሙ በላይ ሲሆን ሲያቅተው፤ የብሶቱ ፅዋ ሞልቶ ሲገነፍል የሚያሰማው
የመጨረሻ የጣር ድምፅ እሪታ ነው። እሪታ የሰው ልጆች ከፍተኛ በደል ሲፈፀምባቸው የሚያሙት ድምፅ በመሆኑ በቸልታ ሊታይ የማይገባ
እጅግ በጣም ከባድና አደገኛ ነገር መሆኑንም እሪታ ሰሚዎቹ ቢያስተውሉና የህዝቡን ድምፅ ቢሰሙ የተሻለ ይሆናል። ሐገራችን ላለፉት
ሃያ ሶስት አመታት በአምባገነኖች አገዛዝ ስር በብሶት ሰንሰለት ታስሮ የኖረው ህዝብ ዛሬ ሚያዝያ 26, 2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ
የእሪታ ድምፁን ከፍ አድርጎ አሰምቷል የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ!!

በሐገራችን እጅግ በርካታ እሪ የሚያስብሉ ከፍተኛ ችግሮች ያሉ ቢሆንም እንደምሳሌ አድርገን ጥቂቶቹን እንኩዋን ብንወስድ የኑሮ ውድነቱ ከሰዎች አቅም በላይ በመሆኑ እናቶች ልጆቻቸውን መመገብና ማስተማር ባለመቻላቸው በልመና ስራ ተሰማርተው ይገኛሉ፤ ወያኔ የመብራት አቅርቦት በሃገር ውስጥ ሳያዳርስ ከተሞች መብራት በፈረቃ እያገኙ ለነጅቡቲ የመብራት አቅርቦት ስምምነት ማድረጋቸው በራሱ ለህዝቡ ያለውን ንቀትና ምን ያህል ለሃሪቷ ጥላቻ እንዳላቸው ያስመሰከሩበት ነው። በሌላ በኩል የሰው ልጅ ያለ ውሃ አቅርቦት እንዴት ህይወቱን ይገፋል ብለው እንዳሰቡ ባናውቅም ውሃ በሃገሪቱ ውስጥ የለም ቢኖርም እርሱም እንደ መብራቱ ሁሉ በፈረቃ በአስራ አምስት ቀን አንድ ቀን ወይንም በሳምንት አንድ ቀን እንደሚመጣ ነዋሪዎች ይናገራሉ ውሃ ፍለጋ ሰው ጀሪካን ይዞ ሲንከራተት ቀኑን ሙሉ እንደሚውልና ውሃ ጥበቃ ህዝቡ እንቅልፍ መተኛት እንዳቃተው ይታወቃል ሌላው መንገድና ትራንስፖርት ለአንድ ሃገር እድገት መሰረታዊ ነገሮች ቢሆኑም ገዢው ፓርቲ ያለፕላንና ያለረዢም ጊዜ እቅድ በሚሰራቸው መንገዶችና በሚያፈርሳቸው መንገዶች በልማት ሰበብ ህዝቡ ለመንገድና ለትራንስፖርት ችግር በማጋለጥ እንዲማረር አድርገውታል።
መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ
እንደማይገባ በህገ መንግስቱ በግልፅ ተደንግጎ የተቀመጠ ቢሆንም ገዢው ቡድን እጁን በማስረዘም የሃይማኖት ተቋማቱን ደጅ በመድፈር
ጣልቃ እየገባ ካድሬዎቹን በሃይማኖት ተቋማቱ በማሰማራት ክርስቲያን ሙስሊሙን እያሸበረ ይገኛል። ሌላው እጅግ በጣም የሚገርመው ወያኔ
ለትምህር የሚሰጠው ዋጋ ዜሮ መሆኑ ነው ዜጎች በከፍተኛ ተቋማት በዮኒቨርሲቲ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው ኮብልስቶን ድንጋይ መንገድ
ላይ እንዲያነጥፉ ይገደዳሉ ያው ተምረው የቀን ሰራተኛ ይሆናሉ ማለት ነው ለስርአቱ አባልና ታማኝ እስካልሆኑ ድረስ መማር ዋጋ እንደሌለው እና ስራ የማግኘት እድላቸው
ህልም እንደሆነም ተማሪዎቹ ይናገራሉ። የተማረ ሃይል የሃገር ሃብት በሆነበት በዚህ ዘመን ወያኔ በተቃራኒው የተማረ መጥላቱ አለመማሩንና
የተማረ ዜጋ በሃገሪቱ እንዳይኖር እያደረገ ያለውን ጥረት ያሳየናል በአንፃሩ የነሱ ልጆች የሚማሩበትን ደግሞ ከሁላችንም የተሰወረ
አይደለም ይሄ በዘር ላይ ያተኮረ ፖለቲካ የትም የማያደርስ መሆኑንም ማወቅ አላባቸው።
ሌላውና አደገኛው የሰው
ልጆች የመፃፍና ሃሳብን በነፃነት የማንሸራሸር ችሮታ ከመንግስታት የሚሰጥ ስጦታ ወይንም መመሪያ ሳይሆን እንዲሁ በፀጋ ተፈጥሮ
የቸረችን ልዩ ችሮታችን ነው ወያኔ ይህንን የእግዜር ስጦታ ሳይቀር በመገደብ እኔ የምለውን
ብቻ እንደገደል ማሚቱ አስተጋቡልኝ እንጂ እናንተ የምትናገሩትም ሆነ የምታስቡት ሁሉ ወንጀል ነው በማለት የሰዎችን ነፃ አስተሳሰብ
የሚያስተናግደው በማእከላዊና በቅሊንጦ፤ በዝዋይ እስርቤቶች ከሆነ አስርተ አመታት ተቆጥረዋል። ሃሳባቸውን በነፃነት በብእር ያሰፈሩ
ደግሞ እንዲሁ የመፃፍ መብታቸው ተገድቦ ብዙዎች በየእስርቤቱ እየማቀቁ ይገኛሉ።
በቅርቡ ወጣት የዞን9 ጦማሪያን
ስለሚያገባን እንጦምራለን ብለው የሀገራቸውን ጉዳይ ቢጦምሩ በደረሰባቸው የደህንነቶች ወከባና ማስፈራሪያ መጦመራቸውን ለሰባት ወራት
ካቆሙ በኋላ እንደገና እንጦምራለን ብለው ብእራቸውን ማንሳታቸውን ባሳወቁ ማግስት ሁሉም ከያሉበት በተመሳሳይ ሰዓት በደህንነቶች
ተይዘው ሃገር የማሸበር ስራ እየሰራችሁ ነው ለሁከት እና ለአመፅ ህዝብ እያነሳሳችሁ ነው በሚል ክስ ተመስርቶባቸው አሰነባበታቸው
እንዴት እንደሆነ ባናውቅም ከታሰሩ ሰነባብተዋል።
ባጠቃላይ ይህንን ሁሉ ግፍና
በደል በጫንቃችን ተሸክመን እሹሩሩ እያልን ለሃያ ሶስት አመታት ስናባብል የኖርን የኢትዮጵያ ልጆች ዛሬ ያጎበጠንን የወያኔ ቀንበር
ከላያችን ለማውረድ የእሪታ ቀን አውጀን እሪ ብለን በአደባባይ ድምፃችንን ማሰማቱ ሲያንሰን ነው ሁላችንም የበደሉ ተጋሪዎች በመሆናችን
እኛም በያለንበት ለሃገራችን ትንሳኤና መልካም አስተዳደር ለማምጣት በሚደረገው ሰላማዊም ትግልም ሆነ ሁለገብ ትግል በአንድነት በመነሳት
አጋርነታችንን ለወገኖቻችን ለማሳየት እና አምባገነኖችን ከሃገራችን ለማስወገድና ለፍርድ ለማቅረብ በሚደረገው ትግል ሁሉ በጋራ እንታገል
እያልኩ እኔም ብሶቴን እሪሪሪሪሪሪ በማለት አሰማለሁ እሪሪሪሪሪሪሪሪሪሪሪሪሪሪሪሪሪሪሪሪሪሪሪሪሪሪሪ
ሄለን ንጉሴ/ኖርዌ
No comments:
Post a Comment