Thursday, October 24, 2013

ኦክቶበር 20, 2013 በኦስሎ ከተማ በላምፔዱሳ ጣሊያን ህይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን በተደረገ የሻማ ማብራት ሥነስርአት ላይ የተደረገ ንግግር


ሔለን ንጉሤ/ኖርዌ
ኦክቶበር 20, 2013

ዛሬ በዚህ ስፍራ የተሰባሰብንበት ዋና አላማ በቅርቡ በላምፔዱሳ በደረሰባቸው አደጋ በአሰቃቂ  ሁኔታ ህይወታቸውን ላጡ ከ300 በላይ የሚሆኑ ወገኖቻችን ለማስታወስና ሃዘናችንን ለመግለፅ ነው።  እነዚህ ስደተኞች የሊቢያ በረሃን አቋርጠው ሲመጡ ከበሽታው፤ ከረሃቡና ከጥማቱ፤ ከበረሃው ንዳድ፤ እንዲሁም ከመኪና አደጋ በተአምር አምልጠው ሊቢያ ሲደርሱ የሚጠብቃቸው እስር ነው እንግዲህ ከዚያ እስርቤት ተርፎ ወደ ጣሊያን ለመሄድ ሌላ ክፍያ ሌላ ስቃይ ይህን አልፈው ሲያበቁ ደግሞ የውሃ እራት እየሆኑ በዚህ ሁኔታ ብዙ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራዊያን ወገኖቻችን አጥተናል።

እነዚህ ወጣት የነገ ሃገር ተረካቢ የሆኑ ትውልዶች ለምን ይህንን አስቸጋሪ የስደት ህይወት መርጠው በየበረሃው በአሰቃቂ ሁኔት ይሞታሉ ወይም ለተለያየ አካላዊና ስነልቦናዊ ችግር እራሳቸውን ያጋልጣሉ ብለን ስንመለከት ሐገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አስርተ አመታት እንደዓለመታደል ሆኖ ሳይሆን ሆን ተብሎ በወያኔ ኢህሃዴግ በተቀነባበረ ሴራ ዜጎች ይገደላሉ፤ በገዛ ሃገራቸው እንደሰባተኛ ዜጋ ይቆጠራሉ፤ ጋዜጠኞችና ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በግፍ በየእስርቤቱ ይማቅቃሉ፤ የወያኔ አባል ካልሆኑ በስተቀር ዜጎች ተምረው የስራ እድል አያገኙም፤ የሃገሪቷ ኢኮኖሚ በTPLF ስር መውደቁ፤ ወጣት ሴቶች ለግርድና ወደ አረብ ሃገራት መሸጣቸው፤ የኑሮ ውድነቱ ከሰዎች አቅም በላይ በመሆኑ፤ ዜጎች በገዛ ሃገራቸው እየተፈናቀሉ መሆኑ፤ ብዙ ብዙ እጅግ በጣም ብዙ ችግሮችን መዘርዘር ይቻላል ባጠቃላይ የሰብአዊ መብት ጥሰቱ፡ የፖለቲካውና የኑሮ ሁኔታ ዜጎች በሃገራቸው እንዳይኖሩና ስደትን እንዲመርጡ አስገድዷቸዋል።

በዚህ አስከፊ የስደት ህይወት ደግሞ ዋናውንና አስቸጋሪውን ገፈት የሚቀምሱት ሴቶች እና ህፃናት ናቸው። ሴቶች እህቶቻችን በስደት ላይ እያሉ እንኳን በከፍተኛ ሁኔታ ፆታዊ ጥቃት ማለትም አስገድዶ መድፈር በተደጋጋሚ ይፈፀምባቸዋል፡ ከዚህም የተነሳ የስነልቦና ችግር ያጋጠማቸውና አእምሮአቸውን መቆጣጠር እስኪሳናቸው ድረስ አደገኛ የሆነ ችግር ውስጥ ይወድቃሉ። ህፃናትም እንዲሁ ምንም የማድረግ አቅምና ችሎታው ስለሌላቸው የሚደርስባቸው ችግር ይህ ነው ለማለት ያስቸግራል።

እንግዲህ  ይሄ ሁሉ ግፍና መከራ ውርደት እንዲሁም ታሪክን የማጉደፍ ሴራ እየተፈፀመብን ያለው ሆን ተብሎ በወያኔ/ ኢህሃዴግ በደደቢት በረሃ በተጠነሰሰ ፅንስ ነው በመሆኑም ሁላችንም ይህንን ግፈኛ ሥርአት ኢትዮጵያን የማጥፋት እኩይ ተግባሩን በአስቸኳይ ማስቆም ያለብን እኛው ስለሆንን አሁን በተለያየ አቅጣጫ በሃገር ቤትም ሆነ በውጭ ሃገር የሚደረገውን ትግል በመደገፍ ያልተደራጀን በመደራጀትና የትጥቅ ትግሉን ወደፊት በማራመድ ለነፃነትና ለዲሞክራሲ በምናደርገው ትግል በጋራ በሃገራችን ዘላቂ አስተማማኝ ለውጥ እንድናመጣ ጥሪዬን አቀርባለሁ።

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር

No comments:

Post a Comment