Sunday, October 6, 2013

በኢትዮጵያ ሴቶችና ህፃናትም ነፃነት ይሻሉ!



ኦክቶበር 06, 2013
ሄለን ንጉሴ

ጦርነት ባለባቸው ሃገሮችና የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ ተብለው በሚመደቡ ሃገሮች እንዲሁም በዋናነት የመልካም አስተዳደር በሌለበባቸው እንደ ሃገራችን ኢትዮጵያ ባሉ ሃገራት ውስጥ ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር እየተጋለጡ ያሉት ሴቶችና ህፃናት መሆናቸው ጥናቶች ይጠቁማሉ።

በሃገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት ሃያ ሁለት አመታት ያለው የአምባገነንና ዘረኛ ቡድን ይህንኑ የሴቶችና የህፃናትን ጥቃት በሀገራችን በከፍተኛ ሁኔታ ጎላ ባለ መልኩ እንድናየው በማድረግ ሴቶች እህቶቻችንን ወደተለያዩ የአረብ ሃገራት ለግርድና በመሽጥ ሰብአዊ መብታቸው ተገፎ በየቤቱ ሲደበደቡ፤ የፈላ ውሃ በላያቸው ላይ ሲደፋ፤ ከፎቅ ሲወረወሩ፤ በየመንገዱ ሲዋረዱና በገዛ ሃገራቸው ኢምባሲ በር ላይ እየተጎተቱ የሚያስጥላቸው አጥተው ሲወሰዱ ሁላችንም በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ተመልክተናል። በሌላ መልኩ ደግሞ ሴቶች እህቶቻችን በሃገር ውስጥ በለጋ እድሜያቸው እየተመረጡ በዝግ የምሽት ክበባት ለባለስልጣናት ፍላጎት መጠቀሚያም እየሆኑ እንደሆነ መረጃ አለ።

ሴቶች እህቶቻችን ይሄ ሁሉ ግፍ የሚፈፀምባቸው በሃገራችን የመልካም አስተዳደር ችግር ምክንያት ትምህርታቸውን ተምረው በሃገራቸው እራሳቸውን ለመቻል የተመቻቸላቸው የስራ እድል ባለመኖሩ ሲሆን በዚህ ምክንያት የራሳቸውና የቤተሰቦቻቸው የመኖር ህልውና በእነርሱ ጫንቃ ላይ ስለሚያርፍ በመሰደድ ኑሮን ለማሸነፍ ይህንኑ መንገድ እየመረጡ ይገኛሉ።

ሌላው በጣም የከፋውና  የሚያሳዝነው ወያኔ ምንም የማያውቁ ህፃናት ልጆችን ሳይቀር የዋጋ ተመን አውጥቶ እንደሸቀጥ በጨረታ ለአለም ገበያ እየተሸጡ ወደ ባእድ ሃገር ይላካሉ ከነዚህ ህፃናት ውስጥ ምናልባት እድለኛ ሆነው ደህና አሳዳጊ የገጠማቸው ህፃናት ያለባህል ወጋቸው እና ያለሃይማኖታቸው በባእድ ሃገር እንዲያድጉ ሲደረጉ አንዳንድ በጉዲፈቻ የተወሰዱ ህፃናት ልጆች ደግሞ በአሳዳጊዎቻቸው ክፉ በደል እየተፈፀመባቸው ይገኛሉ። በቅርቡ በአለምአቀፍ ሚዲያ ሁላችንም እንደሰማነው የ13 አመት ህፃን የሆነችው ሃና ከአሳዳጊዎቿ በደረሰባት ከፍተኛ በደል ሞታ መገኘትዋን  ሰምተናል።

የኢትዮጵያ ሴቶች እና ህፃናት በመልካም አስተዳደር እጦትና ወያኔ በሚያራምደው የዘር ማጥፋት ወንጀል በገዛ ሃገራቸው የአማራ ብሄር ተወላጅ በመሆናቸው ብቻ ተወልደው ካደጉበት ቀዬ ተሰደው ያለምንም መጠለያና ምግብ ሜዳ ላይ ተጥለው ያየነውም በእኛው ሀገር ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ሃገራችን አሁን ባለችበት ሁኔታ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት እንደሃገር እንኳን መቀጠል የማትችልበት ደረጃ ላይ ደርሳለች ህዝባችንም መቋቋም ወደማይችለው የኑሮ ውድነት ገብቶ የሚበላው አጥቶ የበይ ተመልካች ሆኗል:: የነገ ሃገር ተረካቢ የምንላቸው ወጣት ሴቶችና ወንዶች ልጆች በአደንዛዥ እፅ እና በአልኮል ፈዘውና ደንዝዘው በየሺሻ ቤቱና ጫት ቤት ውስጥ እጅና እግራቸውን አጣጥፈው በመቀመጣቸው ወላጆች ወጣቶችን የመጦር ግዴታ ውስጥ የገቡበት ዘመን ላይ እንገኛለን። የወያኔ ስርአት ከአንድ ብሄር የተውጣጡ ቡድኖች ብቻ ኢኮኖሚውን እንዲቆጣጠሩና ሌላውን ከጨዋታ ውጭ በማድረግ ብሄርተኝነትን እያስፋፉና ሃገሪቷን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እየዘረፉና ገንዘብ እያሸሹ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ እያሽመደመዱት ይገኛሉ። እንግዲህ ችግሮቹ ዘርፈ ብዙና ስፋት ያላቸው በመሆናቸው እንደዚህ ባጭሩ ተዘርዝሮ የሚያልቅ ባይሆንም መፍትሄ ግን ይሻል።

ሃገራችንን ከዚህ ሁሉ ችግር ነፃ ለማውጣት ያሉት የሰላም አማራጮች በሙሉ ለሃያ ሁለት አመታት ተሞክረው ተስፋ ያልሰጡ መሆኑ ይታወቃል፤ የሃገራችንን ህልውና  ለማቆየት ይህንን አምባገነን መንግስት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከስልጣን በማውረድ ስልጣኑን ለህዝብ ለማስረከብና ሃገራችን ህዝቦቿ በመረጡት መሪ እንድትተዳደር ለማድረግ የቀረው አማራጭና ያልተሄደበት መንገድ የትጥቅ ትግል ብቻ መሆኑን ግልፅ እየሆነ መጥቷል። ወያኔ እራሱ ስልጣን በወረቀት እንደማይገኝና የሚገባቸውም ቋንቋ ጦርነት ብቻ መሆኑን በተደጋጋሚ ነግረውናል። እንግዲህ ሃገራችንን እንደሃገር ለማቆየት የትጥቅ ትግሉ ግድ ይላል።

በመሆኑም የግንቦት7 ህዝባዊ ሃይል ደሙን አፍስሶ መተኪያ የማይገኝለትን ህይወቱን በመገበር የሃገሩን ህልውና ለማቆየት ጫካ ውስጥ ገብቶ መሬት ላይ ወርዶ ትግሉን በግምባር ቀደምነት ጀምሮልናል። የሃገራችን ኢትዮጵያን የነፃነት ቀን የምንናፍቅ ሁሉ ለዚህ ትግል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የምናደርገውን አስተዋጽዖ አስፈላጊ በመሆኑ ሁላችንም እየናፈቅን ያለነውን ነፃነት በቅርብ ለማግኘት እንድንችል የተጀመረውን ትግል የመቀላቀልና የማገዝ ሃላፊነት የሁላችንም በመሆኑ የተጀመረው ትግል ሳይቋረጥ ከዳር  ደርሶ የሴቶችና የህፃናት መብቶች እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በሃገሩ ላይ በነፃነት እንዲኖር የህግ የበላይነት እንዲከበር ሁላችንም ለትግሉ አጋርነታችንን ማሳየት አለብን::

እኔ ሴት ነኝ እናትም ሚስትም እህትም ነኝና ጦርነት ባልወድም ነፃነትንና እኩልነትን ከመፈለግና የሃገርን ደህንነት ከማስጠበቅ አንፃር ግን ሴቶችም ለትግሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረግ የምንችል መሆኑንና ከትግሉ ጎን በመቆም ደጀንነታችንን የምናሳይ መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ 

No comments:

Post a Comment