Sunday, October 27, 2013

ስሜ ናፈቀኝ



October 23, 2013 at 11:11am
ዕቃ ለማውጣት ቦሌ ወደሚገኘው የካርጎ ተርሚናል ሄጃለሁ፡፡ መቼም ዘመድ ውጭ ሀገርያለው ሰው ደጋግሞ የሚሄደው አንድም ለወዳጁ እድሜ ከጤና ለመለመን ቤተ ክርስቲያን፣ አንድም የተላከለትን ዕቃ ለመውሰድ ካርጎተርሚናል፣ አንድም የዓመት በዓል ብር ለመቀበል ባንክ ቤት ነው፡፡
ወረፋውን ጠብቄ መስኮቱ ጋ ደረስኩና ስሜን አስመዘገብኩ፡፡ እስክትጠራ ጠብቅ ተብዬምወንበር ፈልጌ ተቀመጥኩ፡፡ ከጎኔ አንድ ጎልማሳ ተቀምጦ ይቁነጠነጣል፡፡ አንዴ ፀጉሩን አንዴ ዓይኑን ያሻል፡፡ ኩኩሉ እንደሚልአውራ ዶሮ አንገቱን ከወዘወዘ በኋላ ወደ እኔ ዞር አለና ‹‹ስምህ ናፍቆህ ያውቃል›› አለኝ፡፡

ገረመኝና ‹‹ስሜማ አብሮኝ ነው የሚኖረው፤ ምን ብሎ ይናፍቀኛል›› አልኩት፡፡

‹‹ስምህን ሰጥተህ አታውቅም፤ አሁን ስምህን አልሰጠህም እንዴ›› አለኝ፡፡
ይበልጥ ግራ ገባኝና ‹‹እና ወሰዱት ማለት ነው›› አልኩት ሳቅ እያፈነኝ፡፡

‹‹ታድያስ፤ አሁንኮ ወሳኙ እነርሱ ጋር ያስመዘገብከው ስምህ እንጂ አንተ ጋ ያለውስምህ አይደለም፡፡ አንተ እገሌ መሆንህ ቁም ነገር የለውም፡፡ እነርሱ    ‹እ-ገ-ሌ› ብለው ሲጠሩህ ነው ሕይወትህየሚንቀሳቀሰው፡፡ እኔ አሁን ስሜ ናፍቆኛል፡፡ ስሜ ሲጠራ መስማት፣ ስሜ ሲጠራ አቤት ማለት ናፈቀኝ፡፡››
የእርሱን ስሰማ እኔም ስሜ ይናፍቀኝ ጀመር፡፡ ‹‹ትጠራላችሁ›› አይደል ያሉን፤እውነትም ስማችንን ወስደውታል ማለትኮ ነው፡፡ ካልጠሩን ቁጭ ብለን መቅረታችን ነው፡፡ የተጠሩት ደግሞ እየተፍነከነኩ ወደመስኮቱ እየተጠጉ ነው፡፡ ሰልፉ ሲረዝም፣ ጊዜው ሲሄድ፣ መቀመጥም ሲሰለቻችሁ ደግሞ ስማችሁ ይበልጥ ይናፍቃችኋል፡፡

‹‹እዚህ ብቻ ነው ወይስ ሌላውም ቦታ ወረፋ አለው›› አልኩት፡፡

‹‹ምን እዚህ ብቻ ኑሮህኮ እንደዚሁ ነው፡፡ ስም ትሰጣለህ፣ ትጠብቃለህ፣ ስምህንትናፍቃለህ፣ እድለኛ ከሆንክ ትጠራለህ፣ አቤት ትላለህ፣ ወደ ሌላው ምእራፍ ትሻገራለህ፡፡ እዚያም ስም ትሰጣለህ፣ ስምትናፍቃለህ፣ ትጠራለህ፣ አቤት ትላለህ፣ እንዲህ እያልክ ትኖራለህ፡፡ አቤት ካላልክ ደግሞ ችግር ነው፡፡ ያልፍሃል፡፡ አሁን ያሰውዬ ስልክ እያወራ አለፈው፡፡ ‹አቤት› ማለት ነበረበት፡፡ አሁን እንደገና ስሙ እየናፈቀው ነው፡፡ ያኛው ደግሞ ስሙቢናፍቀው፣ ቢናፍቀው የሚጠራው አጥቷል፡፡እየደጋገመ ‹ጥሩኝ እንጂ› ይላል፡፡‹ቆይ እንጠራሃለን› ይሉታል፡፡ አሁን አንተንበስልክ ጠርተውህ ነው አይደል የመጣኸው? አሁን ይኼ ጋቢ ነገርየለበሰው ሰው ለምን አትጠሩኝም ብሎ ነው ከክፍለ ሀገር የመጣው፡፡ ስሙ ናፍቆት፡፡ ልጁ ደውላ ዕቃ ልኬልሃለሁ አለቺው፡፡ እርሱካሁን አሁን ስሜ በስልክ ይጠራል ብሎ ቢጠብቅ ቀረበት፡፡ ስሙ ሲናፍቀው መጣና ‹እባካችሁ ጥሩኝ› አለ፡፡ እነርሱ ደግሞ‹ሀገርህ ተመለስና ስንጠራህ ትመጣለህ› ይሉታል፡፡ ስሙ የናፈቀው ሰው መች እንዲህ በቀላሉ ይመለሳል፡፡››

‹‹እውነትምኮ ስም የሚያስናፍቁ አሠራሮች ሞልተዋል›› አልኩት ለመጎትጎት

‹‹ቤት ለማግኘት ትመዘገባለህ፣ ስምህ ይናፍቅሃል፡፡ ጋዜጣ ላይ ወጣ፣ ተለጠፈ፣በሬዲዮ ተነገረ በተባለ ቁጥር ስምህን ማየት ትናፍቃለህ፡፡ እዚያ ዝርዝር ውስጥ ስታጣው ቅር ይልሃል፡፡ ስኳር ለማግኘትትመዘገባለህ፣ ከሻሂው ሱስ ይልቅ ስምህን የመስማት ሱስ ይይዝሃል፡፡ ሥራ ለማግኘት ትመዘገባለህ፣ እንጠራሃለን ስትባልትጠብቃለህ፤ ከዚያ ስልክ ባቃጨለ ቁጥር እመር ብለህ ትነሣለህ፤ የሆነ ሰው ስምህን ሲጠራው፣ አንተም አቤት ስትል ለመስማትትናፍቃለህ፡፡ ጓደኛህ ደውሎ በቅጽል ስምህ ከጠራህ ትናደዳለህ፡፡ አንተ የምትጠብቀው ‹አቶ እንትና ነዎት› ተብሎ ሲጠራ መስማትነዋ፡፡ ››

‹‹ቆይ ግን ለምን ይመስልሃል ስማችን እስኪናፍቀን የምንደርሰው››

‹‹አንደኛ ለምዶብናል፡፡ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ስም ጠሪ መምህር ተመድቦ ስም መጥራትተለምዷል፡፡ ዕድር ላይ ይጠራል፤ ፍታት ላይ ይጠራል፤ ዕቁብ ላይ ይጠራል፤ ቡና ለመጠጣት ይጠራል፤ እሥረኛ ለመጠየቅ ይጠራል፤ቪዛ ለመጠየቅ ይጠራል፤ ስም መጥራት ባህላችን ሆኗል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ስማቸው የሚጠራና የማይጠራ ስላሉ ነው፡፡ ስማቸውሊጠራ የሚችል፣ ስማቸው የማይጠራና ስማቸው ሳይጠራ እንደተጠራ የሚቆጠሩ አሉ፡፡ ስማቸው ሊጠራ የሚችለው እንደእኔና አንተ ያሉት ናቸው፡፡ ዕድል ካለህ ስምህ ይጠራል፡፡ ስማቸው የማይጠራው ደግሞ አንዳች ምክንያት የሚኖራቸው ናቸው፡፡ ስማቸውመጠራት የማያስፈልጋቸው ደግሞ ጉዳያቸው በውስጥ የሚያልቅላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ስማቸው የወርቅ ቁልፍ ነው፤ ብዙቢሮዎችን ይከፍታል፤ ወይም ደግሞ የወርቅ ቁልፍ ያንጠለጠለ ስም የሚያውቁ ናቸው፡፡ አንዳንዴኮ ስምን መናፈቅ ይሻላል፡፡ ጭራሽስምህ ይጠፋልኮ››

‹‹አንተ ዋናው ክፉ አትሥራ እንጂ ስምህ ቢጠፋ ምን ችግር አለው? ከባሰ በሕግ መጠየቅ ነው››

‹‹ኖ ኖ ኖ ኖ ኖ እንደዚያ አይደለም፤ ስምህ ከነ ጭራሹ ከመዝገብ ላይ ይጠፋልእንጂ፤ ስምህ አልተመዘገበም፤ ‹ዳታ› ውስጥ የለም፡፡ ኮምፒውተር ውስጥ አልገባም፤ መዝገብ ላይ አልተገኘም፤ ፋይሉ ጠፍቷል፤ትባላለህ፡፡ አንዳንዱ ስምማ ይገርምሃል እንደ ቁልፍ ማንጠልጠያ ወልቆ የሚጠፋ ነውኮ የሚመስለው፤ በተመዘገበበት ቦታአታገኘውም፡፡ አሁን የእኔ ስም ዕድር ልከፍል ከሄድኩ አንደኛ ነው የሚጠራው፤ ስኳር ልወስድ ከሄድኩ ግን ጭራሽ ሳይጠራ ሊቀርይችላል፡፡ ለክፍያና ለመዋጮ ብቻ የታደሉ ስሞች አሉ፡፡ ለመቀበል ብቻ የታደሉ ስሞችም አሉ፡፡ ሁለቱንም ስሞች በየመዝገባቸውነው የምታገኛቸው፡፡ አንተ አንዴ እንኳን ስምህ አልጠራ ብሎህ እየናፈቀህ አንዳንድ ሰዎች ሁለትና ሦስት ጊዜ ስማቸው ሲጠራ ስታይ፣ስም የሌለህ ሁሉ ይመስልሃል፡፡››

‹‹ግን ለሥራና ለስም የታደሉ ሰዎች የሉም››

‹‹ሞልተው፤ አሁን እኛ ሀገር ሊቅ፣ ሳይንቲስት፣ እውነተኛ ነጋዴ፣ ባለሞያ፣ ሥራፈጣሪ፣ ገበሬ፣ ምናምን ለስም ያልታደሉ ናቸው፡፡ ስማቸውን የደመወዝ መክፈያና ግብር ሰብሳቢ ብቻ የሚያውቀው፤ አርቲስት፣ዘፋኝ፣ ቀልደኛ፣ ደግሞ ለስም የታደሉ፡፡ እስኪ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የአንድ ሳይንቲስት ቤት ዓመት በዓል ሲያከብር አይተህ ታውቃለህ? የአንድ የረዥም ርቀት አሽከርካሪ ቤት ገብቶ ኑሮውን ሲያስቃኝ አይተህ ታውቃለህ? እነዚህ ለስም ያልታደሉ ናቸው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ሥራውን የሠሩት፣ የደከሙት፣ የለፉትስማቸው ሳይጠራ መጨረሻ ላይ የሚጨመሩ ቅመሞች ስማቸው ሲጠራ ትሰማለህ፡፡›› 

ይህንን እያወራልኝ በድምጽ ማጉያ ስም መጥራት ተጀመረ፡፡ አምስት ሰዎች ተጠሩ፡፡አብሮኝ የነበረው ሰው ግን አልተጠራም፡፡ በድምጽ ማጉያው ‹መሐሪ ተሾመ› የሚል ስም ሲጠራ ከእኛ ፊት ለፊት ባለው ወንበር ላይየተቀመጠው ሰው ‹ወንድ ከሆንሽ መሐሪ አስቻለው ብለሽ አትጣሪም›› አለ፡፡

‹‹መሐሪ አስቻለው ብሎ መጣራት የወንድነት መለኪያ ሆነ እንዴ›› አልኩት

‹‹መሐሪ አስቻለው እኔ ነኛ››

©ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት የወጣ ነው

No comments:

Post a Comment